ወላዲተ አምላክ
ወላዲተ አምላክ
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ : በወልድ : በመንፈስ ቅዱስ ስም!
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መሰረት አካላዊ ቃል እግዚአብሄር ወልድ ለሰው ልጆች ሁሉ ድህነት ሲባል ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው ሆኗል። (የዮሀንስ ወንጌል 1:1-4) ስለዚህ ከድንግል ማርያም የተወለደው አምላክ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሆነ ድንግል ማርያምን የአምላክ እናት እንላታለን!
የአምላክ እናት!
የአምላክ እናት (Theotokos) የሚለው የቃሉ ምንጭ (ጥንት የመጣው) ከግሪኩ Theotokos ትርጉሙም የእግዚአብሔር እናት፣ የአምላክ እናት አምላክን የወለደች ማለት ነው። ይህ ቃል የሚገልጸው ዋና ሃሳብም ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው የሆነውና የእኛን ባህርይ ከሀጥያት በስተቀር ተካፍሎ በስጋ የተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነው የሚለውን የክርስትና መሰረተ እምነት የያዘ እና መሰረት ያደረገ ነው። ይህ ስያሜም በአጽንኦት የሚገልጸው እመቤታችን ድንግል ማርያም የወለደችው ሕጻን "ዕሩቅ ብዕሲ" ሰው ብቻ አለመሆኑን ይልቁንም የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ መሆኑን ነው።
ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ተጸንሶ የተወለደው አዲስ "ወልድ" አይደለም ዘለዓለማዊውና ቀዳማዊው የእግዚአብሔር አብ የባህርይ ልጅ አካላዊ ቃል የሰውን ባህርይ ገንዘቡ አድርጎ ራሱ ሰው ሆነ እንጅ ለዚህም ነው በትንቢተ ኢሳይያስ 9:6 ላይ ከድንግል ማርያም የተወለደው ሕጻን ሃያል አምላክ እና ዘለዓለማዊ አምላክ ነው የሚለን። የእመቤታችን የአምላክ እናትነትን እዚህ ጋር መረዳት እንችላለን። ከእርሷ የተወለደው እርሱ ሰው የሆነ አምላክ ከሆነ እርሷ ደግሞ ሃያል አምላክ ለሆነው ለተወለደው ሕጻን እናት መሆኗ ግልጽ ነው። እርሱም አምላክ እንደመሆኑ እርሱን የወለደችው ወላዲተ አምላክ መባሏ ግድ ነው።
በ428 ዓም. ንስጥሮስ የስህተት አስተምህሮን ማስተማር ጀመረ ይህ የስህተት አስተምህሮው **ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ አትባልም ምክንያቱም እርሷ የወለደችው ሰውን ብቻ ነው ቡሀላም አካላዊ ቃል በጥምቀቱ አደረበት እንጅ ከእርሷ የተወለደው ሰው ነው ስለዚህ ወላዲተ ክርስቶስ ልትባል ትችላለች አምላክ ከሴት አይወለድምና** ብሎ ያስተምር ነበረ።
በዚህ አስተምህሮው 3 ክህደቶች ነበሩ፦
1➞ ክርስቶስ የአምላክ ማደሪያ (theophorus) አደረገው
2➞ ሁለት አካል ሁለት ባህርይ በማድረግ ተዋህዶን ካደ
3➞ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ አትባልም አለ።
ንስጥሮስ የድንግል ማርያምን የአምላክ እናት ያልተቀበለበት ምክንያት ቃል በጥምቀት አደረበት ብሎ ከድንግል የተወለደውን ዕሩቅ ብእሲ በማድረጉ ነው። እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባህርይ እንደሆነ ባለማመኑ ነበረ። ተዋህዶን በመካዱም ከማርያም የተወለደ የማርያም ልጅ ያደረው ቃል የእግዚአብሔር ልጅ እያለ ሁለት ማንነት እንዲኖረው አደረገ። ነገር ግን መፅሀፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ከፅንሰቱ ጀምሮ ቃል ስጋን ተዋህዷል። ለዚያም ነው ከእርሷ የተጸነሰው ጌታ መሆኑን ቅድስት ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የመሰከረችው የተወለደውም የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን መልዓኩ የመሰከረው።
በ431 በጉባኤ ኤፌሶን ይህ የክርስቶስን አምላክነት የሚያስክደውን የስህተት አስተምህሮ የቤተክርስቲያን አባቶች አወገዙት።
ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባህርይ እንደሆነ
ድንግል ማርያም የወለደቸው አምላክ መሆኑን ወላዲተ አምላክም እንደምትባል መፅሀፍ ቅዱስን ተቅሰው አጸደቁ!
"...ስለዚህም አንድ ክርስቶስ አንድ ገዢ እንደሆነ እናምናለን። ያለ መቀላቀልም ይህን ተዋህዶ እናስተምራለን ቅድስት ድንግልም እግዚአብሔርን የወለደች እንደሆነች እናምናለን። የእግዚአብሔር ቃል ስጋን ተዋህዶ ሰው ሆኗልና ከእርሷ የነሳውንም ስጋ ከተጸነሰበት ቀን ጀምሮ ከእርሱ(ከቃል) ጋር አንድ ባህርይ አድሮጎታልና። (ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ ሃይማኖተ አበው ቁ. 25
✅ድንግል ማርያም የወለደችው አምላክ ለመሆኑ መፅሀፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ!
በትንቢት፦
"...ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።"(ትንቢተ ኢሳይያስ 9:6)
በዚህ የትንቢት ቃል መሰረት የሚወለደው ሕፃን ሃያል አምላክና ዘለዓለማዊ እንደሆነ ይነግረናል። ይህን ህፃን የወለደችው ደግሞ ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤ ስለዚህም የተወለደው ዘለዓለማዊ አምላክ ከሆነ ድንግል ማርያምን የሃያሉ እና የዘለዓለማዊው አምላክ እናት ናት ማለቱ ስህተቱ ምን ላይ ነው?!
2➞"...መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ ... ስለዚህ ደግሞ #ከአንቺ_የሚወለደው_ቅዱስ_የእግዚአብሔር_ልጅ_ይባላል።"✝➞(የሉቃስ ወንጌል 1:35)
በዚህ የመልዓኩ ቃል እንደምንረዳው ከድንግል ማርያም የተወለደው የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ ማነው ስንል ከአብ ጋር የተካከለው ኢየሱስ ነው፦(የዮሀንስ ወንጌል 5:18) ስለዚህም መልዓኩ ከእርሷ የሚወለደው አምላክ መሆኑን ነግሮናልና እርሷም የአምላክ እናት መሆኗን ነግሮናል።
3➞ "... በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት እንዲህም አለች... የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?"✝➞(የሉቃስ ወንጌል 1:43)
ቅድስት ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ ድንግል ማርያም የአምላክ እናት መሆኗን መሰከረች። ከዚህ በላይ ምን ምስክር አለ?!
✅የቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች አስተምህሮ ስለ ወላዲተ አምላክ፦
1➞ቅዱስ ሄሬንዮስ (189 ዓም)
ድንግል ማርያም ለቃሉ ታዛዥ በመሆኗ አምላክን እንደምትወልድ ከመልዓኩ ቅዱስ ገብርኤል የምስራችን ተቀበለች።
✝📖Against Heresies, 5:19:1
"... ይህ የሆነው እግዚአብሔር በነብዩ "እነሆ ድንግል ትጸንሳለች፣ ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል ይህም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው።" ተብሎ የተነገረው ይፈፀም ዘንድ ነው።ይህም በአንድ በኩል ለአባቶቻችን የተሰጠው ተስፋ መፈፀሙን የሚያሳይ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅ ከድንግል መወለዱን ግልፅ በሆነ ሁኔታ የሚያስረዳ ነው። መናፍቃን እንደሚሉት ድንግል ማርያም #የወለደችው_ዕሩቅ_ብእሲ[ሰው ብቻ] ሳይሆን #አካላዊ_ቃል(logos) የተዋሃደውን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን በግልፅ ይናገራል።
✝📖ቅዱስ ሄሬንዮስ በእንተ መናፍቃን መፅ. 3 ምዕ.16 ቁ.2
2➞ቅዱስ አትናቴዎስ (365 ዓም)
➞ ገብርኤል ለዘካርያስ እንደነገረው፣ እንዲሁ #ለወለዲተ_አምላክ ለድንግል ማርያም እንደነገራት
✝📖ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ፣ ትምህርት በእንተ አርዮሳውያን፣ ክፍል 3፣ ቁጥ. 14)
"... እንዲሁም ዩሀንስ ገና በማህጸን ሳለ የአምላክን እናት የድንግል ማርያምን ድምፅ በሰማ ጊዜ በደስታ ዘለለ.." ✝📖 ዝኒ ከማሁ ቁ. 14)
3➞ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም በ 350 ዓም
እግዚአብሔር አብ ከሰማይ ሆኖ ስለ ልጁ ምስክርነትን ሰጠ። መንፈስ ቅዱስም በእርግብ አምሳል ሆኖ ምስክርነቱን ሰጠ። መልዓኩ ቅዱስ ገብርኤልም ለድንግል ማርያም የምስራቹን ዜና በማምጣት ምስክርነቱን ሰጠ። ድንግሊቱ #የአምላክ_እናትም_መሰከረች።
✝📖Catechetical Lectures 10:19
4➞ቅዱስ አግናጥዮስ፦ በ2 ተኛው ክፍለ ዘመን በፊት
ቅዱስ ጴጥሮስም ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሯል። እርሱም የቅዱስ ጴጥሮስ ምሰክርነት እንደሚገልጸው ከድንግል ማርያም የተወለደው #ያው የእግዚአብሔር ልጅ ነው።
✝📖ቅዱስ አግናጥዮስ ምዕ. 12
ከጥንት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ትምህርት በትንሹ አሳየን እንጅ ሁሉንም ብንጠቅስ ቦታም አይበቃን ነገር ግን መታወስ ያለበት ትልቅ ጉዳይ ከኤፌሶን ጉባኤ በፊት ንስጥሮስም "ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ አትባልም" የሚለውን ምንፍቅና ከማንሳቱ በፊት ያሉ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች የድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክነት ከመፅሀፍ ቅዱስ ተነስተው ያስተምሩ ነበረ። ስለዚህም ይህ በኤፌሶን ጉባኤ የመጣ አዲስ አስተምህሮ ሳይሆን ከሀዋርያት ጀምሮ የነበረ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ነው።
በመናፍቃን የሚነሱ ጥያቄዎች፦
❓1- የኢየሱስ ክርስቶስ ስጋ ከሰማይ የመጣ ነው። ስለዚህም ስጋን ከእሷ ስላልነሳ የአምላክ እናት አትባልም! እሱም እናት የለውም!
ይህን ሙግት ያነግቡ ዘንድ መነሻ የሚያደርጉት የመፅሀፍ ቅዱስ ቃል
"... #ሥጋዬን_የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።. . #ከሰማይ_የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በልተው እንደ ሞቱ አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል
➞(የዮሐንስ ወንጌል 6:56-58)
የሚለውን መነሻ በማድረግ ሲሆን **እግዚአብሔር ስጋን ከሰማይ አዘጋጅቶ ከስጋዋ ሳይካፈል ልክ ውሃ በቧንቧ ውስጥ እንደሚያልፍ እንዲሁ ሁኖ ተወለደ እንጅ ከእርሷ ምንም አልነሳም** ይላሉ። ይህ ምንፍቅና በታሪክ ዶሴቲኮች የሚባሉ መናፍቃን ያስተምሩት የነበረ ትምህርት ሲሆን ምንም አይነት የመፅሀፍ ቅዱስ ድጋፍ የለለውና ከመፅሀፍ ቅዱስ ጋርም የሚጋጭ ነው።
በመጀመሪያ መፅሀፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው ክርስቶስ ስጋውን ከሰማይ ይዞ የመጣ ሳይሆን የድንግል ማርያምን ስጋን ነሥቶ የተወለደ ነው፦
"... ይህም ወንጌል #በሥጋ_ከዳዊት_ዘር_ስለ_ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።"
(ወደ ሮሜ ሰዎች 1:3-4)
"... የአብርሃምን ዘር #ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም።"(ወደ ዕብራውያን 2:16)
ስጋው ከድንግል ማርያም ሳይሆን ከሰማይ ነው የሚሉ ሰዎች ከቅዱሳት መፅሀፍ ጋር ይጣላሉ። የድንግል ማርያምን ስጋ ባይዝ ኖሮ የአብርሃምን ዘር #ይዟል አይባልም ነበረ።
2ተኛ ደግሞ አካላዊ ቃል የስጋን ባህርይ ገንዘብ አድርጎ እግዚአብሔር ደም አለው ተብሎ ተጠቅሶ እናገኛለን።
"...በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ..."(የሐዋርያት ሥራ 20:28)
ይህ ቃል እንደሚነግረን እግዚአብሔር በደሙ ቤተ ክርስቲያንን ዋጅቷታል። ነገር ግን በዚህ ተነስተን መለኮት በመለኮትነቱ ደም አለው አንልም። ይልቁንም አምላክ በተዋሃደው በስጋው ደም ዋጃት ይባል።
በተመሳሳይም በዩሀንስ ወንጌል 6:56-58 ባለውም ከሰማይ የመጣው አካላዊ ቃል በተዋህዶ ገንዘቡ ባደረገው ሰውነት የህይወት እንጀራ ይባላል።
እንጅ ተቃዋሚዎች እንደሚስቱት ስጋውን ከሰማይ ይዞ መጣ የሚል አንድምታ የለውም ምክንያት በቅዱሳት መፃህፍት እንደተነገረው ክርስቶስ የአብርሃምን ዘር (የድንግል ማርያምን ስጋ) ይዞ(ከስጋዋ ስጋን ነስቶ) የተፀነሰ የተወለደም ነው።
ከሰማይ መጣሁ ማለቱ ቅድመ ዓለም በዙፋኑ ይኖርበት የነበረውን መናገሩ እንጅ ስጋዬን ከሰማይ ነው የሚል አይደለም። በተዋህዶ የከበረ አንድ አካል አንድ ባህርይ ስለሆነም ከድንግል ማርያም በስጋ የተወለደው አምላክ ከሰማይ የመጣ የህይወት እነጀራ ነው እንላለን፦
(የዮሐንስ ወንጌል ምዕ. 6: 35፣ 48)
"...ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም።
❓2- የክርስቶስ አምላክነት ከድንግል ማርያም ከተወለደ ወዲህ አይደለም ስለዚህም የአምላክ እናት አትባልም፤ እርሷ የወለደችው ስጋውን ነውና።
በመናፍቃን ቤተ እምነት ውስጥ የተለያዩ የእምነት አቋሞች ይጋኛሉ አንዳንዶቹ ድንግል ማርያምን የናቁ መስሏቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋውን ከሰማይ ነው ይዞት የመጣው የሚል ምንፍቅና አላቸው።(ከላይ መልስ የተሰጠበት) አንዳንዶች ደግሞ በስጋ ከድንግል ማርያም እንደተወለደ በማመን የአምላክ እናት አይደለችም የሚለውን የንስጥሮስን ምንፍቅና ያነግባሉ።
እስኪ ጥያቄን እንጠይቃቸው፦
➞ኤልሳቤጥ የጌታዬ እናት ያለቻት የአምላካችን የክርስቶስ ጌትነት ከድንግል ማርያም ከተወለደ ቡሃላ የመጣ ነውን? ሉቃስ 1:43
➞ ከእርሷ የተወለደው የእግዚአብሔር ልጅ ነው ከተባልን የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ከእርሷ ከተወለደ ቡሃላ ነውን? ሉቃስ 1:35
➞እርሷ የወለደችው ሃያል አምላክና ዘለዓለማዊ አምላክ ነው ከተባለ የአምላክነቱ ጅማሬ ከእርሷ ቡሃላ ነውን? ትንቢተ ኢሳይያስ 9:6
እኒህን ጥያቄዎች አሰላስሉ!
"ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ድንግል ማርያምን **የአምላክ እናት** ስትል ስግው ቃል(ሰው የሆነውን አምላክ) ወልዳዋለች ማለት እንጅ የመለኮት መገኘት ከማርያም ነው እያለች አይደለም። በፍፁምም አትልም።" [ቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳ በNature of christ መፅሀፍ ገፅ 14]
ምክንያቱም "... የመለኮቱ መገኘት ከእመቤታችን ከተወለደ ወዲህ አይደለም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አለም ሳይፈጠር የነበረ ጥበብ ነው እንጅ የማይታመመው እርሱ ከባህርየ መለኮቱ ሳይለወጥ ሕማም የሚሰማውን ስጋን ተዋሐደ።"✝➞ሃይማኖተ አበው ምዕ. 66 ክ. 3
የአምላክ እናት የሚለውን ሃሳብ ለመረዳት
ከድንግል ማርያም የተወለደውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት መረዳት ያስፈልጋል። ድንግል ማርያም አምላክ ሰው ሲሆን ማለትም በሥጋዌ ጊዜ የፀነሰችው ቡሃላም የወለደችው ዕሩቅ ብዕሲ ሳይሆን ከፅንሱ በፊት ቅድመ ዓለም የነበረውን አምላክ ነው።
አካላዊ ቃል ሰው ሲሆንም ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህር አንድ ባህርይ ሆኖ ነው። አንድ አካል አንድ ባህርይ ማለትም አንድ ማንነት ማለት ነው። አንድ ማንነት ካለው የእግዚአብሔር ልጅ ሌላ የሰው ልጅ ሌላ ብለን ሁለት ማንነት ልንሰጠው አይገባም መፅሀፍ ቅዱስ እንደሚለን የእግዚአብሔር ልጅ( አምላክ) ከእርሷ ከድንግል ማርያም ተወልዷል። ስለዚህም የአምላክ እናት ስትባል መለኮት ከፀንሷ ጀምሮ የተገኘ ለማለት ሳይሆን በስጋ የወለደችው አምላክ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅን ነው ማለት ነው።
✅ማጠቃለያ፦
ወላዲተ አምላክ የሚለው መጠሪያ መሰረት ያደረገው የክርስቶስ አየሱስን አምላክነት ነው። ይህን መጠሪያ የተጠቀምነው በራሳችን ፈቃድ አይደለም ይልቁንም ከመፅሀፍ ቅዱስ ጀምሮ ሃዋርያትና በየዘመኑ በተነሱ ቅዱሳን አባቶች ሲነገር የነበረ የቤተ ክርስቲያን እውነታ ነው። ይህን ቃል ለድንግል ማርያም በመጠቀማችን በድንግል ማርያም ክብር የምንጨምረው ነገር የለም። እርሱን ለመውለድ ስትመረጥ ከብራለችና። ባንጠቀመውም የምንቀንሰው አንዳች ቅንጣት የለም። ነገር ግን እርሷን ወላዲተ አምላክ ማለት ስህተት ነው ካልን ከክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የወንጌል አስተምህሮ ጋር እንጋጫለን ትልቅ ምንፍቅናም ውስጥ እንገባለን ምክንያቱም ከእርሷ የተወለደው የእግዚአብሔር ልጅ አምላክ አይደለም ማለታችን ነውና። መንፈስ ቅዱስም በኤልሳቤጥ ላይ ሞልቶባት የጌታ እናት ያለችው ስህተት ነው ማለታችን ነው ይህም ደግሞ መንፈስ ቅዱስን መስደብ ነው።
✝__ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነው ቅድመ ዓለም የነበረው ዘለዓለማዊው አምላክ አለምን ለማዳን ሲወድ ከእርሷ ብፅዕት ቅድስት ከምትሆን ከድንግል ማርያም ተወልዷልና የአምላክ እናት ትባላለች!__✝
ማጣቀሻ መፃህፍት
➞ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ (2008)፣ መድሎተ ጸድቅ ቅፅ. ፩
➞ pope shenoda(1986). Nature of christ
➞ ኤራቅሊስ ዘተዋህዶ(2012)፣ ቅድስት ድንግል ማርያም በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ(የትርጉም ስራ)
በሌላ ርዕስ እስከምንገናኝ ሰላም ለሁላችን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ወለወላዲቱ ድንግል!
ወለመስቀሉ ክቡር!
ይቆየን!
©✞ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ👇
Comments
Post a Comment