ክፍ. ፫ የኢየሱስ አምላክነት በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት(ዮሐ. 10:30)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን!
ለቀደመው ክፍል ፦[ (ክፍል ፪ [ የዮሐንስ ወንጌል5:58 ]
[ዮሐ10÷30 "እኔና አብ አንድ ነን"]
በዚህ ጥቅስ ኢየሱስ ከአብ ጋር አንድ ባሕርይ (essence) መሆኑን የሚክዱ አርዮሳውያን እና ኢየሱስ ከአብ ጋር አንድ ማንነት ነው የሚሉ ሰባልዮሳውያን ይረቱበታል። ሁለቱንም በቅደም ተከተል እንመልከታቸው።
1. አርዮሳውያን (የይሖዋ ምስክሮች) እና ሙስሊሞች " እኔ እና አብ አንድ ነን" የሚለውን የጌታ ንግግር "የአላማ አንድነት (unity of purpose) ነው በማለት ያስቀምጣሉ። ለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሌላ ቦታ የተናገረውን ጥቅስ እኔና አብ አንድ ነን ከሚለው ጋር በማነጻጸር ያቀርባሉ።
ዮሐ17÷20-21 " ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ።"
ዮሐ17÷22-23 "እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ።"
ይህን ጥቅስ በመያዝ ኢየሱስ ክርስቶስ "እሱና አባቱ አንድ እንደሆኑ ደቀ መዛሙርቱም አንድ እንዲሆኑ ጠይቋል"። ስለዚህ አብም፣ ኢየሱስ ክርስቶስም፣ ደቀ መዛሙርትም አንድ የሚሆኑት በአላማ(እቅድ) ነው የሚል ድምዳሜ ያቀርባሉ።
[ምላሽ]
√ በመጀመሪያ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር በዮሐ17÷20-23 ላይ ስለ አላማ አንድነት መናገሩ ዮሐ10÷30 ላይም እኔና አብ አንድ ነን ሲል የአላማ አንድነትን መናገሩ ነው የሚል አመክንዮ አይሰራም። እነርሱ መጀመሪያውኑ አብና ኢየሱስ ክርስቶስ ባሕሪያዊ አንድነት የላቸውም የሚል እምነት ስላላቸው ሁለቱንም ጥቅሶች ጠቅልለው የአላማ አንድነት በሚል ይወስዱታል። እኛ ግን አብና ኢየሱስ ክርስቶስ የአላማ አንድነት ብቻ ሳይሆን ባሕሪያዊ አንድነትም እንዳለቸው ስለ ምናምን ጥቅሶቹን እንደ አውዳቸው እንመለከታቸዋለን።
√ "እኔና አብ አንድ ነን" በሚለው ጥቅስ ውስጥ "አንድ" ተብሎ የተጠቀሰው የግሪክ ቃል ἕν(ሄን) በመጽሐፍ ቅዱስ ነጠላ አንድ ቁጥርን(ማቴ12÷21)፣ አንድ አላማን(1ቆሮ3÷8) ፣ አንድ ኀብረትን(ሮሜ12÷5) ፣ አንድ ማንነትን ( 1ቆሮ12÷12) በሚያመለክት ሁኔታ ተገልጿል። ስለዚህ አውዱን መሠረት በማድረግ ይፈታል። ዮሐ10÷30 ላይ "እኔና አብ አንድ ነን" የሚለው የጌታ ንግግር የኃይል ወይም የባሕርይ አንድነትን የሚገልጽ እንደሆነ ከዚህ በታች በተጠቀሱት ሀሳቦች ማረጋገጥ ይቻላል።
1.1 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "እኔና አብ አንድ ነን" ከማለቱ በፊት እንዲህ የሚል ቃል ተናግሮ ነበር።
ዮሐ10÷28 "በጎቼን ከእጄ ማንም አይነጥቃቸውም።"
ዮሐ10÷29 "ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም።"
እነዚህን ከተናገረ በኃላ "እኔና አብ አንድ ነን" በማለት የኃይል አንድነት እንዳላቸው ገለጸ። የትኛውም አካል ከእርሱና ከአባቱ በጎቹን ሊነጥቅ እንደማይችል በመግለጽ ከአባቱ ጋር እኩል ስልጣን እንዳለው ነገራቸው። ሁለቱም አካላት አብም ኢየሱስ ክርስቶስም የበጎቹ ጠባቂ(እረኛ) መሆናቸውን አሳይቷል። ይህንን ግልጽ ለማድረግ በዚው በምእራፍ 10 የተገለጹትን ሀሳቦች እንመልከት።
ዮሐ10÷16 "ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።"
በዚህ ጥቅስ ላይ "እረኛውም አንድ" በማለት የመንጋው ጠባቂ አንድ እንደሆነ ይገልጻል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ መልካም እረኛ እኔ ነኝ በማለት ይህ አንድ እረኛ እሱ እንደሆነ ያስረዳል።
ዮሐ10÷14 " መልካም እረኛ እኔ ነኝ"።
√ አስቀድመን እንደ ተመለከትነው "ከአባቴም እጅ ማንም አይነጥቃቸውም" ብሎ አብም የበጎቹ ጠባቂ እረኛ እንደሆነ ገልጾልናል። አብም ኢየሱስ ክርስቶስም እረኛ ከተባሉ፣ ደግሞም እረኛው አንድ ከሆነ አብና ኢየሱስ ክርስቶስ የተካከለ ስልጣን፣ ባሕሪያዊ አንድነት አላቸው ማለት ነው። በመሆኑም "እኔና አብ አንድ ነን" ሲል ይህን የሚያስረዳ ነው።
1.2 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "እኔና አብ አንድ ነን" ከማለቱ አስቀድሞ እንዲህ ብሎ ነበር።
ዮሐ10÷28 " እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም"
የዘላለም ሕይወትን የሚሰጥ አምላክ ብቻ ነው። አብም ወልድም የዘላለም ሕይወትን ይሰጣሉ። ይህም በስልጣን አንድ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።
ዮሐ5÷21 " አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል።" ይህን የሥልጣን አንድነትን ለመግለጽ እኔና አብ አንድ ነን አለ።
1.3 ሌላኛው ኢየሱስ ክርስቶስ "እኔና አብ አንድ ነን" ሲል የአላማ አንድነትን እየገለጸ እንዳልሆነ የሚያሳየን ለአይሁድ ግብረ መልስ የሰጠው ምላሽ ነው። አይሁድ "እኔና አብ አንድ ነን" የሚለው የጌታችንን ንግግር በሚገባ ተረድተውታል። ለዚህም ነው "ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ አደረክ" ብለው በድንጋይ ሊወግሩት የተነሱት። ዋናው ነጥብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የአይሁድ አረዳድ ትክክል አይደለም ብሎ አስተባበለ? የሚለው ነው። በጭራሽ አምላክ ነኝ ማለቴ አይደለም ብሎ አላስተባበለም። ይልቁንም ከራሳቸው መጽሐፍ ካስረዳቸው በኃላ እንዲህ አላቸው።
ዮሐ10÷36 " የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን። ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?"
እንግዲህ እናስተዋል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ያላቸው "እኔና አብ አንድ ነን" ሲሆን በዚህ ጥቅስ እንደ ተጠቀሰው "የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ" በማለት እኔና አብ አንድ ነን የሚለውን "የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ" በማለት ገልጾታል። አይሁድ ደግሞ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ሲል "አምላክ" ነኝ እያለ እንደሆነ ይረዱት ነበር። ስለዚህም እኔና አብ አንድ ነን ሲል አምላክ ነኝ ማለቱ እንደሆነ እያስረገጠላቸው ነው።
ዮሐ5÷18 " ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር።"
ጌታችን እኔና አብ አንድ ነን ሲል የአላማ አንድነት እየገለጸ ከሆነ አይሁድ ወደ ለየለት ግራ መጋባት ሊከት ይሆን "እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እግዚአብሔርን ይሳደባል ትሉኛላቹ" ብሎ የወቀሳቸው? በጭራሽ አይደለም። ይልቁንም "እኔና አብ አንድ ነን" ሲል የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ማለቱ እንደሆነ በመግለጽ አምላክነቱን ለአይሁድ አሳውቋቸዋል።
2. ሰባልዮሳውያን ( የሐዋርያት ቤተክርስቲያን) አማኞች ደግሞ ሌላኛውን ጽንፍ ይዘው "ኢየሱስ እና አብ አንድ ማንነት" አላቸው ለማለት ይጠቅሱታል። ይህ ግን ስህተት ነው!
2.1 ἐγὼ καὶ ὁ Πατὴρ ἕν ἐσμεν የሚለው የግሪክ ዓ.ነገር ( I and the Father are one) የሚል የእንግሊዘኛ ትርጉም አለው። በዚህ ጥቅስ ላይ I
(እኔ) የሚለውና Father(አባት) የሚሉት ሁለት ስሞች and( እና) በሚል አያያዥ ቃል ከመያያዛቸውም በላይ Father(አባት) ከሚለው ስም በፊት [the] አርቲክል ገብታለች። ይህም እኔ ያለው አካልና አባት የተባለው ሁለት ማንነት መሆናቸውን ያሳያል።
2.2 በተጨማሪም [are one] የሚለው ሁለት ማንነቶች መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ምክንያቱም [are] የሚለው ግስ ከአንድ በላይ የሆኑ ነገሮችን ለመግለጽ የምንጠቀምበት ነው። ከሁሉም በላይ ግን አብና ወልድ ሁለት የተለያዩ ማንነት እንደሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች በግልጽ የሰፈረ ነው፦
2ኛዮሐ1÷9 " ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።"
ዮሐ16÷28 " ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ።"
በቀጣይ ክፍል አራት [ የዮሐንስ ወ. 20:28 ]ን የምንመለከት ይሆናል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ክፍል አራት [ የዮሐንስ ወ. 20:28 ]
ክፍል አምስት [ የሐዋርያት ስራ 20:28 ]
ክፈል ስድስት [ ሮሜ :5 ]
ለማንኛውም አስተያየት፦
[ ዐቃቢያነ እምነት ዘኦርቶዶክስ ]
https://t.me/akabianement
ለቴሌግራም ቻናላችን፦
[ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ]
https://t.me/ekbetemnet
Comments
Post a Comment