አፅናኙ መንፈስ ቅዱስ ነው! ክፍ 2

 

አፅናኙ መንፈስ ቅዱስ ነው። ክፍ. 2
በአብ ስም በወልድ ስም በመንፈስ ቅዱስ ስም አንድ አምላክ አሜን!

=>>> [ በክፍል አንድ ] ጽሁፍ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሌላ አጽናኝ  ይሰጣችኋል በማለት የተናገረው ስለ መሐመድ ሊሆን እንደ ማይችል በ 9 በቂ መክንያቶች ተመልከተናል። በዚህ ጽሁፍ ሙስሊሞች አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ለማለት የሚያቀርቧቸውን ሙግቶች በመመልከት በቂ መልስ እንሰጣለን።

=>>>የሙስሊሞች ሙግት (ቁጥር-1)
"በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አጽናኝ ተብሎ የተጠቀሰው በግሪኩ ጰራቅሊጦስ የሚል ሲሆን ትርጉሙ ወዳጅ ወይም ጠበቃ ማለት ነው። ወዳጅ ወይም ጠበቃ ደግሞ ቅርበት ያለውን አካል ለመግለጽ የምንጠቀምበት እንጂ ከአንድ አካል ፍጹም የማይነጠልን ነገር ለመግለጽ አንጠቀምበትም። በክርስትና አስተምህሮ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ የማይነጠል አምላክ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስም " ሌላ አጽናኝ" ብሎ ከራሱ ለይቶ ጠርቶታል። ዮሐ14÷15 ይሄ ደግሞ ፍጹም አይነጣጠሉም ከሚለው የሥላሴ አስተምህሮ ጋር አይሄድም"

=>>>ምላሽ (ቁጥር-1)
ሙስሊሞች ይሄን ሙግት ያቀረቡት የጌታችን ንግግር ለማን እንደ ተናገረ ካለ ማስተዋል ነው። እነርሱ እንዳሉት Παράκλητον(Parakletos) የሚለው የግሪክ ቃል ጠበቃ፣ ረዳት፣ ወዳጅ፣ አጽናኝ የሚሉ ትርጉሞች አሉት። ( Wiktionary,  Ancient Greek) ነገር ግን ጌታችን ጰራቅሊጦስ የሚለውን ቃል የተጠቀመው ለእራሱ ነው ወይስ ለደቀ መዛሙርቱ? የሚለውን አላስተዋሉም። ጌታችን ጠበቃ(ወዳጅ) ይሰጣቹኋል ያላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ነው። ስለዚህ አጽናኙ ጠበቃነቱ፣ ወዳጅነቱ፣ረዳትነቱ ለደቀመዛሙርቱ እና እሱን ለተከተሉት እንጂ ለራሱ ለኢየሱስ እንደሆነ የተነገረ አይደለም። ይህንን ለማረጋገጥ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረውን ቃል ማስታወስ በቂ ነው።

"አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፣ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና።"ማቴ10÷19-20

=>>>በዚህ ቃል ላይ እንደ ተገለጸው አሕዛብ፣ አላውያን ነገሥታት ይዘው በአስጨነቋቹ ሰአት የምትናገሩት እንዳታጡ ረዳት ሆኖ፣ ጠበቃ ሆኖ የሚናገርላቹ መንፈስ ቅዱስ(የእግዚአብሔር መንፈስ) ነው ብሏቸዋል።  "ሌላ አጽናኝ ይሰጣቹኋል" ዮሐ14÷16 የሚለው ቃል ሌላኛው አጽናኝ ከመሠጠቱ በፊት እሱ ራሱ (ኢየሱስ ክርስቶስ) አጽናኛቸው እንደ ነበረ የሚያሳይ ነው። ኢየሱስ ደሞ ሲያጽናና የነበረው ደቀ መዛሙርቱን ነው። በዚው በአስራ አራተኛ ምእራፍ ላይ ደቀ መዛሙርቱን በሚያጽናና ቃል አብዝቶ ሲናገራቸው እንመለከታለን። ለአብነት እነዚህን እንመልከት:-

" ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ።"(የዮሐንስ ወንጌል 14:18)

" ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ።"(የዮሐንስ ወንጌል 14:21)

በእነዚህ ጥቅሶች በግልጽ እንደ ተቀመጠው ኢየሱስ እወዳቹሃለው ብሎ ወዳጅነቱን፣ ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም ብሎ አጽናኝ መሆኑን አሳይቷቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱና የተከታዮቹ አጽናኝ፣ ወዳጅ ከነበረ ሌላኛው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስም ወዳጅ ወይም ረዳትነቱ ለደቀ መዛሙርቱ ነው። ለደቀ መዛሙርቱና ለተከተሉት የተነገረውን ቃል መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስ ረዳት(ጠበቃ) እንደሆነ  የተነገረ አድርገው  በመረዳት ያቀረቡት ሙግት ውድቅ ነው።

=>>>የሙስሊሞች ሙግት (ቁጥር-2)
በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተቀመጠው አጽናኙ የሚመጣው የኢየሱስን መሄድ ተከትሎ ነው። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር እያለ መንፈስ ቅዱስ በተለያዩ ሰዎች ውስጥ ነበረ። ለምሣሌ:- መጥምቁ ዮሐንስ፣ ቅድስት ኤልሳቤጥ፣ አረጋዊው ስምኦን! ሉቃ1÷15 ሉቃ1÷41 ሉቃ2÷25 አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ከሆነ ኢየሱስ እኔ ካልሄድኩ አይመጣም አይልም ነበር።

=>>>ምላሽ (ቁጥር-2)

መድኃኒታችን ክርስቶስ እርሱ ሲሄድ ስለሚልከው ሌላ አጽናኝ ሲናገር በምልዐት በአማኞች ሁሉ ላይ ስለሚወርደው መንፈስ ቅዱስ መናገሩ ነው፡፡ ይህ ማለት አስቀድሞ በጥቂት ሰዎች ላይ ሲሰራ በነበረውና በኋላ አምነው በተጠመቁ ሁሉ ላይ በሚወርደው መንፈስ ቅዱስ መካከል ልዩነት አለ ማለት አይደለም፡፡ ልዩነቱ ያው መንፈስ በምልዐትና በተወሰነ መጠን መውረዱ ብቻ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ዘመን የተሥፋው ቃል ያልደረሰበት፣ ጥል ሕያው የሆነበት፣ የእግዚአብሔር ልጅ ያልተገለጠበት፣ ቤዛነት ያልተፈፀመበት በመሆኑ በርካታ ውስንነቶች ነበሩት፡፡ ስለሆነም ጌታ እግዚአብሔር በዚያው ዘመን ሕዝበ እግዚአብሔር ከሆኑት እስራኤላውያን መካከል በነቢያትና በአንዳንድ ሰዎች ብቻ ለተወሰነ ሥራና አገልግሎት መንፈሱን በማውረድ አብሯቸው ይሰራ ነበር፡፡ ይህ አሰራር በተገለፀበት ሥፍራ ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ስለወረደባቸው ሰዎች እናነባለን፡፡ የአዲስ ኪዳኑ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ ግን አምነው በተጠመቁ ሁሉ ላይ የተገለጠ ነው፡፡ ይህም የተለየ ኩነት በመሆኑ አስቀድሞ ትንቢት ተነግሮለታል፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ ከመቶ ሃያው ቤተሰብ ጋር መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው በበዓለ ሃምሳ ቀን ይህ ምሥጢር ላልገባቸው አይሁድ ያደረገው ገለፃ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ "ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፡- አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ቃሎቼንም አድምጡ። ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፥ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤ ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው። እግዚአብሔር ይላል፡- በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ" (ሐዋ፡2÷15-18)፡፡ ይህ ትንቢት በእርግጥም ትንቢተ ኢዩኤል ምዕራፍ 2 ከቁጥር 28-32 በጉልህ ተፅፎ ይነበባል፡፡
ስለዚህም በሁለቱ ሁኔታዎች መካከል ማለትም በብሉይ ኪዳንና ጌታ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በሆነው የመንፈስ ቅዱስ መውረድ መካከል ያለው ልዩነት ግልፅ ነው፡፡ በአንዳንድ ቅዱሳን ላይ ለተወሰነ ሥራና ተልዕኮ መውረድና አምነው በተጠመቁ ሁሉ ላይ መውረድ በእጅጉ ይለያያል፡፡ የተጠቀሰው ትንቢትም "በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ" ያለው ለዚህ ነው፡፡ ትንቢቱ በተፈፀመበት ጊዜም የተከፋፈሉት የእሳት ልሳኖች በእያንዳንዳቸው ላይ እንደተቀመጡባቸው በቤቱ ውስጥ በነበሩት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ እንደሞላባቸው ነው የተፃፈው፡፡ አምኖ በጌታ ስም የተጠመቀ ሁሉ የዚህ ፀጋ ተካፋይ እንደሚሆን ከተሰጠውም ፀጋ የሚጎድል እንደሌለ የሚከተለው የመጽሐፍ ክፍል ግልፅ ያደርግልናል፡፡  "አጵሎስም በቆሮንቶስ ሳለ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፥ አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ። ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን? አላቸው። እነርሱም፡- አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት። እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ? አላቸው። እነርሱም፡- በዮሐንስ ጥምቀት አሉት። ጳውሎስም፡- ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝ

ብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ አላቸው። ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤ ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው በልሳኖችም ተናገሩ፥ ትንቢትም ተናገሩ። ሰዎቹም ሁሉ አሥራ ሁለት ያህሉ ነበር" (ሐዋ፡19÷1-7)
ይህ መንፈስ ቅዱስ ጌታ በአባቱ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ ለምዕመናን ሁሉ መሪ፣ አስተማሪና አጽናኝ ሆኖ የተሰጠ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ ያላደረበት ሰው አምኛለሁ ማለት አይችልም፡፡ ለዚህ ነው "ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ" ተብሎ የተፃፈው (1ቆሮ፡6÷19-20)፡፡ በሌላም ሥፍራ "ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ" የሚል ቃል አለ (ኤፌ፡4÷30)፡፡ እኒህ የጌታ ቃላት እንደሚነግሩን አምነው የተጠመቁ ሁሉ ማሕደረ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሆኑ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ጌታ ኢየሱስ እርሱ ከሄደ በኋላ ሌላ አጽናኝ፣ መሪና አስተማሪ የሚሆነው መንፈስ ቅዱስ እንደሚመጣ ለሐዋርያቱ የነገራቸው፡፡ ስለሆነም ጌታ በምድር ሳለና ከዚያ በፊት ባለው ዘመን በአንዳንድ ቅዱሳን ላይ ይወርድ የነበረውን የእግዚአብሔር መንፈስ በመጥቀስ ጌታ ካረገ በኋላ የሚመጣው ሌላ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ሳይሆን መሐመድ ነው ማለት ስህተት ብቻ ሳይሆን ቀልድም ይመስላልና ብታስቡበት አይከፋም እንላለን፡፡

=>>>የሙስሊሞች ሙግት (ቁጥር-3)

አጽናኙ የሰማውን እንጂ ከራሱ እንደ ማይናገር ተገልጿል።
" ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።"
(የዮሐንስ ወንጌል 16:13)

በሥላሴ ትምህርት ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ራሱን የቻለ አምላክ ነው። ይህ ከሆነ መንፈስ ቅዱስ ከራሱ መናገር ይችላል ማለት ነው።ስለዚህ ከራሱ አይናገርም የሚለው ስለ መንፈስ ቅዱስ የተነገረ አለመሆኑን ያሳያል

=>>>ምላሽ (ቁጥር-3)
አንቺው ታመጪው አንቺ ታሮጪው አሉ! ራሳቸው ስለ ሥላሴ የተሳሳተ  hypothesis ሰጥተው እራሳቸው Conclusion(ድምዳሜ) ላይ ደርሰዋል። ስለ ሥላሴ ያላቸው እውቀት በብዥታ ውስጥ እንዳለ ይህ አባባላቸው ይመሰክራል። በመሠረቱ ከላይ  ያለው ጥቅስ እነርሱ ካሉት በተቃራኒ የሥላሴን አስትምህሮ የሚያጸና ነው።

ይህ የመንፈስ ቅዱስ "የሚሰማውን ይናገራል" መባል ከተልዕኮው ጋር ያለውን ዝምድና የሚያሳይ መሆኑን ያለመገንዘብ ያመጣው የአስተሳሰብ ግድፈት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሥላሴ አነዋወር ውስጥ ከአብ የሚሰርፅ (የሚወጣ) መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህንኑም "ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል" የሚለው ቃል ያስረዳል (ዮሐ፡15÷26)፡፡ አብ የሥላሴ ልባቸው በመሆኑ የንግግር ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ ቃል የተባለው ክርስቶስ እንኳ "ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ" ሲል ከአብ ልብነት የተወለደ አካላዊ ቃል መሆኑን እየነገረን ነው (ዮሐ፡16÷28)፡፡ በሥጋ ተገልጦ ሰዎች እያዩትና እየዳሰሱት ሲያስተምር አጠንክሮ የሚናገረው "እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ፣ ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደ ሆነች አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ" በማለት ነበር (ዮሐ፡12÷49-50)፡፡ ይህ ከአብ ተቀብሎ የመናገር ዘይቤ እንደ ተራ መልዕክተኛ መልዕክትን በጆሮ ሰምቶ የማድረስ አካሄድ የሚመስላቸው ወገኖች ሲሰናከሉ እናያለን፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን ይህን ሁኔታ ተመሳሳይ መደናገር ውስጥ ለነበረው ለደቀመዝሙሩ ለፊልጶስ በሰጠው ማብራሪያ ላይ ግልፅ አድርጎታል፡፡ "እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል" በማለት (ዮሐ፡14÷10)፡፡
ሥላሴ በሕላዌ አንድ በቅዋሜ ሦሥት መሆናቸውን መረዳት ከእንዲህ ያለው መወዛገብ ያድናል፡፡ ጌታ ኢየሱስ "አብን አሳየንና ይበቃናል" ብሎ ጥያቄ ላቀረበው ፊልጶስ በመደነቅ ነበር የተናገረው፡፡ "አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ አብን አሳየን ትላለህ?" የሚለው ቃል ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡፡ ጌታ ይህን ብቻ ብሎ አላቆመም "እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል፤ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ" ሲልም አክሏል (ዮሐ፡14÷9-11)፡፡ በሕላዌ አንድ መሆን ማለት አንዱ በሌላው ውስጥ ሕልው ሆኖ መኖር፣ መታየት ወይም መገለጥ ማለት ነው፡፡ የአካል ሦሥትነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በሕልውና የሚገናዘቡበት ሁኔታ ነው ክርስቶስን "እኔን ያየ አብን አይቶአል" ደግሞም "እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ" ያሰኘው፡፡ እንግዲህ ጌታ ኢየሱስ የሚናገረውን ሁሉ ከአብ የሰማውን እንደሆነ መናገሩን በዚህ መንገድ ከተረዳነው የመንፈስ ቅዱስም "የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና" የሚለውን ቃልም በተመሳሳይ መንገድ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ኃይለ ቃል ቀጥሎ ያሉትን ጥቅሶች ልብ ማለትም ጠቃሚ ነው፡፡ "እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና፤ ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ" ይላል ቃሉ (ዮሐ፡16÷14-15)፡፡ መንፈስ ቅዱስ "ከራሱ አይናገርም የሚሰማውን ይናገራል እንጂ" ከተባለና ክርስቶስ ደግሞ "የሚነግራችሁ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ነው ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነውና ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ" ካለ የሁለቱም የንግግር ምንጭ አብ መሆኑን እንገነዘባለን ማለት ነው፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ" ይበል እንጂ ልክ እንደ መሐመድ በየዕለቱ ወይም በየሳምንቱ አሊያም በሆነ ጊዜ ልዩነት የሚቀበለው ቃል አልነበረም፡፡ "አብ የምናገረውን ሰጠኝ" ሲል በውስጡ ሕልው ሆኖ ያለው አብ ተናገር ያለውን መናገሩን መግለፁ ነው፡፡ ይህም አንድ ሰው በልቡ ያሰበውን በቃሉ እንደሚናገር ዓይነት ነው፡፡ በሥላሴ አኗኗር ውስጥ የአብ ከዊን ልብነት፣ የወልድ ከዊን ደግሞ ቃልነት ነው፡፡ ስለሆነም በአብ ልብነት የታሰበው በእርሱ ቃልነት መነገሩን ሊገባቸው በሚችል ቀላል አገላለፅ መጠቀሙን ከማሳየት የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ የወልድ ከዊን ቃልነት ነው ስንል የሥላሴ ቃላቸው፣ መናገሪያቸው ወልድ ነው ማለታችን ነው፡፡ ክርስቶስ ስለ መንፈስ ቅዱስ "ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል" ሲል በእኔ ቃልነት በመጠቀም ይነግራችኋል ማለቱ ነው፡፡ "ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው ስለዚህ ለእኔ ካለው ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ" ሲልም የንግግሩ ምንጭ የአብ ልብነት መሆኑን መጠቆሙ ነው፡፡ በአብ ልብነት የሚታሰበው ሁሉ የቃል ገንዘብ በመሆኑ "ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው" አለ፡፡ እንግዲህ መንፈስ ቅዱስ "በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ" (ሐዋ፡13÷2) ብሎ ሲናገር፣ በአማኞች ውስጥ ሆኖ ወደ እውነት ሲመራ (ዮሐ፡16÷

13)፣ ከሐዋርያቱ ጋር በአንድ ላይ ሲፈቅድ (ሐዋ፡15÷28)፣ ተላልፈው ለተሰጡት የሚናገሩትን ሲሰጥ (ማቴ፡10÷20)... በዚህ ሁሉ መንገድ እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሰራ የአንዱ አምላክ ረቂቅ አሰራርን እየተመለከትን ነው ማለት ነው፡፡ ይህን ሁኔታ በዚህ መንገድ ከተረዳነው የሙስሊም ወገኖች የማቀራረብ ስልት ውኃ የማይቋጥር ሙግት መሆኑ ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡ እስካሁን ዘርዘር አድርገን ያየናቸው ነጥቦች ከሙስሊም መምህራኖች ለሚቀርቡ መከራከሪያዎች መልስ ለመስጠት ያህል እንጂ "ሌላው አጽናኝ" ተብሎ የተጠቀሰው መሐመድ እንዳልሆነ በቀላሉ ለማሳየት የማይቻል ሆኖ አይደለም፡፡ "ሌላው አጽናኝ" መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ያለመገንዘብ በእኩለ ቀን ፀሐይ አትታየኝም የማለት ያህል ይሆናል፡፡ ታዲያ በየት አልፎ አጽናኙ መሐመድ ሊሆን ይችላል?

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!


አፅናኙ ማነው? [ ክፍል ሶስት ]
______________✝
       ለማንኛውም አስተያየት፦
[ ዐቃቢያነ እምነት ዘኦርቶዶክስ ]

ለቴሌግራም ቻናላችን፦
[ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ]
      

Comments

Popular posts from this blog

ዕቅበተ እምነት

ወላዲተ አምላክ

መልስ ለወሒድ ዑመር