አምላክ እንዴት ሰው ይሆናል?

 " በአምላክ ሰው መሆን ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች... "


    አንድ አምላክ በሚሆን በአብ፡በወልድ፡በመንፈስ ቅዱስ ስም!

    ስለአምላክ ሰው መሆን በምንናገርበት ጊዜ ከሙስሊም ወገኖች ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል ለዛሬ ጌታ በፈቀደ መጠን ፦

 ➊፦ አምላክ እንዴት ሰው ይሆናል?

 ➋፦ #እግዚአብሔር_ሰው_አይደለሁም_ብሎ የለምን? የሚሉትን የምንመለከት ይሆናል።

♦ ➊፦  አምላክ እንዴት ሰው ይሆናል?

     በመጀመሪያ ይኼ ጥያቄ ፍልስፍና አዘል ነው። አምላክን ሰው የመሆን ነገር እንደዚህ እና እንደዛ ብለን አስረድተን የምንጨርሰው አይደለም ምክንያቱም ከእኛ አእምሮ በላይ ነው። ለዛም ነው የአምላክ ሰው የመሆን ነገር ምስጢር የተባለው።

    ሲቀጥል ይኽን ጥያቄ ለሚጠይቁ ወገኖች እኛም መልሰን ጥያቄ እንጠይቅ ፦ አምላክ ሰው እንዳይሆን ምን ያግደዋል? እግዚአብሔር አምላካዊ ባህሪውን #ሳይለቅ ስጋን ቢዋሐድ ችግሩ ምኑ ላይ ነው? ለእኔ ችግሩ አይታየኝም ችግር የሚኖረው አምላካዊ ባህሪውን ትቶ ሰው ሲሆን ነው። የሙስሊሞችም ቅድመ ግንዛቤ ይኼው ይመስላል ለምን እንደዚህ እንዳልኩ ምክንያቴን ላቅርብ ፦

     ለእናንተም ደርሷችሁ ከተመለከታችሁት አንድ ሰሞን በፌስቡክ መንደር ይዞር የነበረ " የአመቱ ምርጥ ምላሽ" የተሰኘ አጭር ፅሁፍ ነበረ። ፅሁፉ ሙሐመድ ነጃድ የተባለ ጠያቂ  ለጠየቀው ጥያቄ የዶክተር ዛኪር ናይክን መልስና የያዘ ነበር። የፅሁፉን ሀሳብ በአጭር ሲቀመጥ፦

   ጠያቂው፦ " ፈጣሪ የሰውን ቅርፅ ሊይዝ ለምንድን ነው የማይችለው?" ብሎ ለዛኪር ጥያቄ ሲያቀርብ

    የዛኪር መልስ፦ " አምላክ ሰው መሆን ይችላል ግን ሰው ሆነ ማለት የአምላክነቱ ቀረ ማለት ነው። ሰው የመጀመሪያና የመጨረሻ ያለው ነው ፈጣሪ ግን መጀመሪያና መጨረሻ የሌሉው ነው... " የሚል ነበር። 

     በዛኪር መልስ ለዚህ ለአምላክ ሰው መሆን የሙስሊሞች ምልከታ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ይቻላል።አብዛኞቹ ሙስሊሞች የእርሱ አድናቂ ስለሆነ ሀሳቡን ያለምንም ጥያቄ እንደሚቀበሉት እርግጠኛ መሆን ይቻላል ። ዛኪር አምላክ ሰው ሆነ የሚለውን የተረዳው አምላክነቱን ትቶ ሰው መሆን ወይንም ከአምላክ ወደ ሰውነት መለወጥ በሚል ነው። እኛ ግን በክፍል ሁለት ላይ እንደተመለከትነው አምላክ ሰው ሆነ ስንል ዘእንበለ ውላጤ (ያለመለወጥ) ነው በዛው ላይ ከነምሳሌው ጭምር ተመልከተናል። እዛ ከቀረበው ምሳሌ ለመጨመር ያክል ቅዱስ ቁርባንን እናንሳ።  ቅዱስ ቁርባን በቅዳሴው ላይ ፍፁም ወደ ጌታ ስጋ እና ፍፁም ወደ ጌታ ደም ይለወጣል ይህንን ውላጤ ወይንም መለወጥ(ጠብቆ ይነበብ) እንለዋለን። የአምላክ ሰው መሆን ግን ከዚህ የተለየ ነው። አምላክ ሰው ሆነ ስንል ከአምላክ ወደ ሰው ፣ ከፍፁም የአምላክ ባህሪይ ወደ ሙሉ በሙሉ ሰው ባህሪይ ተለወጠ ብለን አይደለም  ያለመለወጥ የስጋ ባህሪይን ገንዘቡ አደረገ ፣ ተዋሐደ ብለን እንጂ።

    ወንጌላዊው ዮሀንስ " ቃልም ስጋ ሆነ" ብሎ ለተጠራጣሪዎች ክፍተትን ትቶ አላቆመም ከአምላክነት ወደ ሰውነት ተለወጠ ብለው ተጠራጣሪዎች እንዳይስቱ መንገድ ሲዘጋ "ጸጋንና እውነትን ተመልቶ በእኛ #አደረ" ብሎታል። በዚህ ጥቅስ በትንሹ ሁለት ኑፋቄዎች ይረታሉ።

    የመጀመሪያው ይሄ ተለወጠ የሚለው ነው። አለመለወጡን ቅዱስ ዮሀንስ አደረ በማለት አምላክነቱን ትቶ ሰው አለመሆኑን አስረዳን።

    ሁለተኛው ደግሞ የንስጥሮስ ኑፋቄ "ወልድ ከማርያም በተወለደው ስጋ ላይ አደረ  " የሚለው ነው። ይህን ክህደት ቅዱስ ዮሀንስ " ስጋ ኮነ" በማለት የኢየሱስ ሰው መሆን ዘእንበለ ህድረት መሆኑን አስረዳ።

   ስናጠቃልል አምላክ ሰው ሆነ ስንል አምላክነቱን ትቶ ስላልሆነ የአምላክ ሰው መሆን ጥያቄ ሊፈጥርብን አይገባም።

📌➋፦#እግዚአብሔር_ሰው_አይደለሁም_ብሎ የለምን?

     ሙስሊሞች በብሉይ ኪዳን የሚገኙትን ዘኁልቁ 23:19ኝን እና ትንቢተ ሆሴ 11:9ን በመጥቀስ እግዚአብሔር ሰው አይደለሁም ስላለ ሰው ሊሆን አይችልም ይሉናል።

    በመጀመሪያ እስኪ የጥቅሱን አውድ እንይ እና ቀጥለን ከዛው ከብሉይ ኪዳን እግዚአብሄር በሰው አምሳል የተገለፀበትን እንመለከታለን።ዘኍልቁ 23፥19

“ ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው  አይደለም ፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም ። እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን?”

በዚህ ጥቅስ ውስጥ እግዚአብሔር ጊዜው ሲደርስ ሰው አልሆንም የሚል ሽታው እንኳን የለም ውድ አንባቢያን እናንተ ይታያችኋልን ❓። ከዛ ይልቅ ይህን ንግግር በተናገረበት ጊዜ እግዚአብሔር ሰዋዊ አካልም ሆነ የሰው ባህሪይ እንደሌለው የሚያስረዳ ነው። በዚህ ጥቅስ ውስጥ የሰው ባህሪያት ተጠቅሷል። ሰው ይፀፀታል ፡ ሐሰትን ይናገራል ፡ አደርገዋለሁ ያለውንም ላይከውን ይችላል እኒህ የሰውኛ ባህሪያቶች ናቸው።

እግዚአብሄር ግን አድርገዋለሁ ያለውን ሳያደርግ ፡ ሳይፈፅም አይተወውም።

“ # የሠራዊት # ጌታ # እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል፦ እንደ# ተናገርሁ # በእርግጥ # ይሆናል፥ እንደ አሰብሁም እንዲሁይቆማል።”— ኢሳይያስ 14፥24

    እግዚአብሔር የእውነት አምላክ ነው እንጂ የሀሰት አይደለምና ሐሰትንም አይናገርም።

“ # እግዚአብሔር # የእውነት # ዳኛ ነው፥ ኃይለኛም ታጋሽም ነው፥ሁልጊዜም አይቈጣም።”— መዝሙር 7፥11

“በእጅህ ነፍሴን እሰጣለሁ፤ # የእውነት # አምላክ አቤቱ፥ ተቤዥተኸኛል።”— መዝሙር 31፥5

   ጠቅለል ስናደርገው የዘኁልቁ ጥቅስ እግዚአብሄር እንደሰው እንደማይዋሽ ፡ እንደማይፀፀት እና እፈፅማለሁ ያለውን ሳይፈፅም እንደማይተው የሚያስረዳ እንጂ ሰው አልሆንም የሚል አንድምታ የለውም።

    ሆሴዕ 11:9

“እኔ አምላክ ነኝ እንጂ #ሰው #አይደለሁምና፥ #በመካከልህም ቅዱሱ #ነኝና #የቁጣዬን #መቅሠፍት #አላደርግም፥ኤፍሬምንም አጠፋ ዘንድ አልመለስም፤ በመዓትም አልመጣም።”

     እንደላይኛው ጥቅስ በዚም ውስጥ እግዚአብሄር ሰው አልሆንም የሚል ፈፅሞ የለውም። ጥቅሱ የሚናገረው የእግዚአብሄር ቁጣ የችኮላ እንዳልሆነ፡ እግዚአብሔር የምህረት እንጂ የጥፋት አምላክ እንዳልሆነ ነው።

   እግዚአብሄር ምህረቱን የበዛ ታላቅ እና ገናና አምላክ እንጂ ለጥፋት የፈጠነ አምላክ አይደለም።

“አባቶቻችን በግብጽ ሳሉ ተኣምራትህን አላስተዋሉም፥የምሕረትህንም ብዛት አላሰቡም፤ በኤርትራ ባሕር ባለፉ ጊዜ ዐመፁብህ።”— መዝሙር 106፥7

    እግዚአብሔር አምላክ ምንም እንኳን ብንበድልም መአቱ የፈጠነ አይደለም እና ታግሶ የንስሐን ጊዜ ይሰጠናል ያንን የንስሐ ጊዜ ተጠቅመን  ወደ እርሱ ብንመለስ ይቅር የሚል መሐሪ አምላክ ነው።

  “አምላክህ እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ነውና አይተውህም፥ አያጠፋህምም፥ ለአባቶችህም የማለላቸውን ቃል ኪዳኑን አይረሳም።”— ዘዳግም 4፥31

   የሆሴ ጥቅስ እንግዲህ የሚናገረው ይህን ነው።ከዚህ ባለፈ እግዚአብሔር ሰው የመሆኛው ጊዜ ከመድረሱ በፊት ሰው እንዳልሆነ መናገሩ ስህተት አይደለም ምክንያቱም ኦሪት ዘኁልቁ የተጻፈው  በግምት በ15BC ወይም በ14BC ነው የዛን ጊዜ ደግሞ አዎ እውነት ነው እግዚአብሔር ወልድ ሰው አልሆነም ነበር። ኢየሱስ በመጀመሪያ በአካላዊ ቃል ይኖር የነበረ አምላክ እንጂ ሰው አልነበረም ። እኒህ ሁለት ጥቅሶች 5500 ዘመን ከተፈፀመ በኋላም ኢየሱስ ሰው እንዳይሆን የሚከለክሉ አይደሉም።

መዋሸት ሀጢአት ነው ፡ ቃልን አለመጠበቅ ሀጢአት ነው ኢየሱስ ደግሞ በምድር ይመላለስ በነበረበት ጊዜ ከሀጢአት የነፃ ቅዱስ ሆኖ ነበር። ስለዚህ እኒህ በተደጋጋሚ የሚነሱ ሁለት ጥቅሶች በየት ብለው ይሁን በየትም ኢየሱስ አምላክ ከመሆን አያግዱትም ማለት ነው።

    እስኪ ደግሞ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር በአምሳለ ሰው የተገለፀበትን ቦታ እንይ፦

እግዚአብሔር ሰው የመሆኛው ሰአት ከመድረሱ በፊት በዛው በብሉይ ኪዳን በሙሴ መፅሀፍት ውስጥ ለተለያየ ሰው በሰው አምሳል እየተገለፀ ታይቷቸዋል። እነዚያ የተነሱት ነጥቦች እነርሱ

እንደሚሉት ቢሆኑ ኖረ ሙሴ በአንድ እራስ ሁለት ምላስ በሆነ ነበር ግን አይደለም።

ለምሳሌ፦

    ለአብርሃም የተገለጠበትን መመልከት ይቻላል፦

ዘፍጥረት 18

¹ በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት።² ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፤ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፥ ወደ ምድርም ሰገደ፥እንዲህም አለ፦3 አቤቱ፥ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ፤”

  ሊቃውነተ ቤተክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ሰው ሆኖ እንደሚቀድሰን የሚያጠይቅ ነው የሚሉለትን አንድ ጥቅስ እንጨምር

   ዘፍጥረት 32

²⁴ ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስከ ንጋት

ድረስ ይታገለው ነበር።²⁵ እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ ያዕቆብም የጭኑ ሹልዳ ሲታገለው ደነዘዘ።²⁶ እንዲህም አለው፦ ሊነጋ አቀላልቶአልና ልቀቀኝ። እርሱም፦ ካልባረክኸኝ አልለቅቅህም አለው።²⁷ እንዲህም አለው፦ ስምህ ማን ነው? እርሱም፦ ያዕቆብ ነኝ አለው።²⁸ አለውም፦ ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል፤ ከእግዚአብሔር ከሰውም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና።²⁹ ያዕቆብም፦ ስምህን ንገረኝ ብሎ ጠየቀው። እርሱም፦ ስሜን ለምን ትጠይቃለህ? አለው። በዚያም ስፍራ ባረከው።³⁰ ያዕቆብም፦ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሰውነቴም ድና ቀረች ሲል የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል ብሎ ጠራው"

እኒህ ሁለቱን መጥቀስ ብቻ በቂ ይመስለኛል።

ስናጠቃልለው በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ወልድ እንደሚወለድ፡ እንደሚመጣ የሚያሳይ ጥቅስ እንጂ እግዚአብሔር ሰው አይሆንም የሚል ፈፅሞ የለም!!!

              ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

         ©✞ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ

Comments

Popular posts from this blog

ዕቅበተ እምነት

ወላዲተ አምላክ

መልስ ለወሒድ ዑመር