የመሲሁ አምላክነት በብሉይ ኪዳን ትንቢት

 ሰው ስለሆነው አምላክ!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን

የመሲሁ አምላክነት በብሉይ ኪዳን ትንቢት


ተወዳጅ የገፃችን ቤተሰዎች በክፍል ባለፉት ክፍሎች በአምላክ ሰው መሆን እና በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሄር ልጅነት ላይ የሚሰነዘሩ ጥያቄዎች መመለሳችን የሚታወስ ነው።፤ በአምላክም ሰው መሆን ላይ መተማመናችን የሚታወስ ነው ዛሬ ደግሞ የሚወለደው መሲህ አምላክ መሆኑን የሚጠቁሙ ምዕራፎችን በስፋት እንዳስሳለን።

እንደሚታወቀው ጌታችን ስለ እርሱ ኦሪት እና ነብየት እንደተነበዩ በብዙ ቦታዎች ላይ ተናግሯል(ማቴ 13:17

ሉቃ.24:44፤18:31፤1:70...ወዘተ)


ስለ መሲሁ መወለድ፣ ስለመሰቀሉ፣ ስለመሞቱ፣ ስለመነሳቱ በብሉይ ኪዳን በስፋት የተተነበየ እውነታ ነው። ለምሳሌ ስለ መወለዱ፦

"... ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።"

(ትንቢተ ኢሳይያስ 7:14)

ስለመሰቀሉ፦

መዝሙረ ዳዊት 22:15-18፤ ኢሳያስ 53 ትንቢተ ዳንኤል 9:25(መሢሕ ይገደላል)

ስለትንሳኤው፦

"...እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፥ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው፤"

(መዝሙረ ዳዊት 78:65)

ስለ እርገቱ፦

"...አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።"(መዝሙረ ዳዊት 47:5)

ዛሬ ላሳያችሁ የወደድኩት በትንቢተ ኢሳይያስ የተተነበየውን ትንቢት ይሆናል፦

"... ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።"(ትንቢተ ኢሳይያስ 9:6)

    ነብዩ ስለ ተወለደልን ህፃን የተናገረበት ክፍል ይህ ነው። ነብዩ ለወደፊት የሚፈፀመውን ጉዳይ ርግጠኛ በመሆን በእለቱ እንደተፈፀመ አድርጎ ተናገረ ይህም የሚያሳየው ነብያት ለመፈፀሙ ርግጠኛ የሚሆኑበትን ማለትም መፈፀሙ የማይቀርን ጉዳይ በአሉበት ሰአት እንደሚፈፀም የመናገራቸው ልማድ በመፅሀፍ ዘንድ ያለ ነው። ለምሳሌ፦

1➞"...ስለዚህ ሕዝቤ ወደ ምርኮ ሄዱ፥ ጌታን አላወቁትምና፤ ከበርቴዎቻቸውም ተራቡ፥ ሕዝባቸውም ተጠሙ።"

(ትንቢተ ኢሳይያስ 5:13)

እስራኤላውያን ወደ ምርኮ ሄዱ ብሎ በጊዜው እንደተፈጠረ በpresent perfect tense አድርጎ ይነግረናል። ነገር ግን መላውን ምዕራፍ ስንመለከት ይህ ጉዳይ ወደ ፊት የሚፈፀም ነው፦ (ቁጥር 5, 6ን እና 9ን ይመልከቱ)


2➞     "... የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ምድያምን በሔሬብ ዓለት በኩል እንደ መታው ጅራፍ ያነሣበታል፤ በትሩም በባሕር ላይ ይሆናል፥ በግብጽም እንዳደረገኦ ያነሣዋል።. . .28፤ ወደ አንጋይ መጥቶአል፤ በመጌዶን በኩል አልፎአል፤ በማክማስ ውስጥ ዕቃውን አኑሮአል፤ 

➞(ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ. 10:26-28)


      በዚህ ክፍል ላይ በ26 ላይ ወደፊት እንደሚፈፀም በሚገልፅ ግስ/በfuture tense ከጀመረ ቡሃላ በ28 ላይ በጊዜው የተፈፀመ አድርጎ በpresent tense ይናገራል ነገር ግን ይህ ቃል ወደፊት የሚፈፀም ነው።

የዚህ አይነት ሌሎች ብዙ ትንቢቶች ቢኖሩም ለአስተዋይ ይህ በቂ ነው።


     ይህን ካየን እስኪ ይህን ትንቢት ስለጌታችን እንዴት እንደሚተነብይ እንመልከተው።


(ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ. 9)

----------

1፤ ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም። በመጀመሪያው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አቃለለ፤ በኋለኛው ዘመን ግን በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል።

2፤ በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።

3፤ ሕዝብን አብዝተሃል፥ ደስታንም ጨምረህላቸዋል፤ በመከር ደስ እንደሚላቸው፥ ሰዎችም ምርኮን ሲካፈሉ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል። 4፤ በምድያም ጊዜ እንደ ሆነ የሸክሙን ቀንበር የጫንቃውንም በትር የአስጨናቂውንም ዘንግ ሰብረሃል። 

5፤ የሚረግጡ የሰልፈኞች ጫማ ሁሉ፥ በደምም የተለወሰ ልብስ ለቃጠሎ ይሆናል፥ እንደ እሳት ማቃጠያም ሆኖ ይቃጠላል።


✅አውዳዊ ፍቺ ከእነ ፍፃሜው!


     ከቁጥር አንድ ጀምረን ስናነበው እግዚአብሔር የአህዛብን ገሊላ እንዳከበረ የሚናገር ነው፤ ይህም በዮርዳኖስ ማዶ የነበረውን የአህዛብን ገሊላ በመተው እስራኤልን ብቻ ለድህነተ አለም በመምረጥ ለ5500 ዓመት ያህል ቢኖርም ነገር ግን በኋላኛው ዘመን እንዳከበራቸው ይናገራል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወቅቱ የነበሩት የአይሁድ ሊቃውንት ባልጠበቁት ሁኔታ ከተናቀው የገሊላ ግዛት ነበር የመጣው፡፡ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶ እኛን አከበረ፤ ለዚህም በወንጌላቱ ላይ ምስክርነት አለ፦



    "... በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ #ገሊላ ከተማ፥ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።(የሉቃስ ወንጌል ምዕ. 1:26-27)


     ኢየሱስ ክርስቶስ የእናቱ የዘር ግንድ የሚመዘዘው ከዳዊት ወገን ቢሆንም እርሷ እስራኤላዊ ብትሆንም ነገር ግን ከገሊላ ከተማ የተገኘች ነበረችና የአህዛብ ገሊላን አከበረ ተባለ። 

     ...ቁጥር ሁለት ላይ እንደምንመለከተውም"በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።"ይላል አዎ አለም ሁሉ በጨለማ በዲያቢሎስ ቅኝ ግዛት ነበረች ነገር ግን የጌታ መወለድ ለዚህ ሁሉ መፍትሄ ነበረ ለዚህ ሁሉ ደስታና ፍስሃ ነበረ።

የዚህ ትንቢት ፍፃሜ ማግኘቱን ወንጌላዊው እንዲህ አስቀምጧል፦ "... በነቢዩም በኢሳይያስ። የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ የባሕር መንገድ፥ በዮርዳኖስ ማዶ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው"

➞(የማቴዎስ ወንጌል 4:14-16)


     እንግዲህ የዚህን ትንቢት መግቢያ ከተመለከትን የተወለደውን ህፃን ወደሚያብራራልን ክፍል እናምራ።



➫ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 9)

6፤ ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።


כִּי־יֶ֣לֶד יֻלַּד־לָ֗נוּ בֵּ֚ן נִתַּן־לָ֔נוּ וַתְּהִ֥י הַמִּשְׂרָ֖ה עַל־שִׁכְמֹ֑ו וַיִּקְרָ֨א שְׁמֹ֜ו פֶּ֠לֶא יֹועֵץ֙ אֵ֣ל גִּבֹּ֔ור אֲבִיעַ֖ד שַׂר־שָׁלֹֽום


6-kî-  ye·leḏ  yul·laḏ-  lā·nū,  bên  nit·tan- lā·nū,  wat·tə·hî  ham·miś·rāh  ‘al-  šiḵ·mōw;  way·yiq·rā  šə·mōw  pe·le  yō·w·‘êṣ  ’êl gib·bō·wr,  ’ă·ḇî·‘aḏ  śar-  šā·lō·wm.


1➫ሕፃን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፦


በዚህ ቃል መሰረት ህፃን እንደተወለደልንና ወልድ እንደተሰጠን ይነግረናል። ይህም ቃል በአዲስ ኪዳን 


"...የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው።...

ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።(የሉቃስ ወንጌል ምዕ. 2:7-11)

   ይህም ወልድ በሌሎች ትንቢቶችም እና በተፈፀሙበት ቦታ እንደምንረዳው እወጣጡ ከቤቴልሄም የሆነ ነው። እርሱም ከቤተልሄም የሚመጣው የሚወለደው በትንቢት ልኡለ ባህሪ ቅዱስ አምላክ እንደሆነ የተነገረ ጉዳይ ነው። ልጁ የተወለደው ከቤቴልሄም ነውና። ትንቢቱም ይህ ነው።➫" አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።"(ትንቢተ ሚክያስ 5:2-3)


   በዚህ ትንቢት እንደምንረዳው የሚወለደው ልጅ፤ ከቤተልሄም የሚመጣው ህፃን ልኡለ ባህሪ ዘለአለማዊ ንግስና ያለው ነው ይህም ቃል በቅዱስ ገብርኤል ብስራት ወቅት ፍፃሜውን አግኝቷል።

"... እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤"

(የሉቃስ ወንጌል 1:32) አወጣጡም ከዘለአለም የሆነ አልፋና ኦሜጋ ያለና የነበረ ነው።


2➫አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፦ 

    ይህ አለቅነት በጫንቃው ነው ማለት ሁሉ ለእርሱ እንደሚገዛ እና በእርሱ የማስተዳደር ስር ስለሚሆነው ስለዚህም ጉዳይ ነብየ እግዚአብሔር ዳንኤል እንዲህ አለ፦


"... በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው። (ትንቢተ ዳንኤል ምዕ. 7:13-14)


      እንግዲህ ይህ የሰው ልጅ የተባለ የሚወለደው ህፃን ነው እርሱም አለቅነት በጫንቃው ስለሆነ ግዛት እና ክብር ተሰጠው፤


ተሰጠው ሲልም እነሆ እግዚአብሔር አብ ለወልድ ሁሉን ማስረከቡን ያሳያል። 


3➫ስሙም ድንቅ(פֶּ֠לֶא) መካር(יוֹעֵץ֙)

    በመጀመሪያ እነዚህ  ስሞች  የማዕረግ ስሞች ናቸው፤ ይህ ማለት ባህርያቱን የሚገልፁ ናቸው። ለምሳሌ፦ ጌታ፣ አምላክ፣ የሚሉት የያህዌህ የማዕረግ ስሞቹ ናቸው እነርሱም ጌትነቱን፣ አምላክነቱን እና የሁሉ ጌታ መሆኑን የሚገልፁ ናቸው። እነዚህም በኢሳይያስ 9:6 ላይ የተጠቀሱ ስሞች የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ባህርያት የሚገልፁ ስሞች ናቸው። 


1-መካር፦ መካርነቱም ድንቅ ነው ለዚያም ድንቅ መካር አለው። መካር የሚለውን ቃል ይዘን ወደ ዕብራይስጡ ስንሄድ  yaw-ats' ያውአተስ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል እናገኛለን ትርጉሙም  to advise, give counsel. ማለት ነው።( https://biblehub.com/hebrew/3289.htm )

 በአማረኛው ደግሞ በሚናገረው ቃል ዓላማ ያለው አቅጣጫ የሚመራ የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡

➫ይህ ቃል በመጸሀፍ ቅዱስ ላይ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ስም ሆኖ እናገኘዋለን ለምሳሌ፦

"... ይህም ደግሞ #ድንቅ_ምክር ከሚመክር በግብሩም ማለፊያ ከሆነው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ወጥቶአል።"(ትንቢተ ኢሳይያስ 28:29)

በመካርነቱ ድንቅ የሆነ እርሱ እግዚአብሔር አምላክ ነው፤ ለዚህም ድንቅ መካር ተሰኝቷል። ስለዚህ ይህ የተወለደ ህፃን እግዚአብሔር ለመሆኑ ጥርጥር የለውም።


2➫ኃያል አምላክ፦

   በሁለተኛ ደረጃነትም የተወለደው ህፃን ሃያል አምላክ ነው። በእብራይስጥም ኤል ጊቦር ( גִּבּוֹר אֵל) (The mighty God)፦ እንግዲህ በዚህ ቃል መሰረት የምንረዳው የሚወለደው ህፃን የአማልክት አምላክ የሆነ ሃያል አምላክ ነው። በብሉይ ኪዳን ስንመለከት ይህንው ስም እግዚአብሔር ሲጠራበት እናገኛለን፦

    "...እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፥ #ታላቅ_አምላክ_ኃያልም የሚያስፈራም፥ በፍርድ የማያደላ፥ መማለጃም የማይቀበል ነውና እናንተ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ፥ ክእንግዲህ ወዲህም አንገተ ደንዳና አትሁኑ።"(ኦሪት ዘዳግም 10:16-17) ሃያል አምላክ ማለት ከሁሉ በሃይሉ የበረታ የአማልክት አምላክ የጌቶች ጌታ ማለት ነው። ጌታችንም ከእነዚህ ትንቢቶች ባለፈ በአዲስ ኪዳን የአማልክት አምላክ የጌቶች ጌታ መሆኑ እንዲሁ ተጠቅሷል።"... እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም #የጌቶች_ጌታና_የነገሥታት_ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።"(የዮሐንስ ራእይ 17:14) የተወለደው ህፃን ቅድመ ዓለም የነበረው የነገስታት ንጉስ ሃያሉ አምላክ ለመሆኑ በቂ ማስረጃችን ይህ ነው።


3➫የዘላለም_አባት (אֲבִיעַ֖ד)አቢ አድ

 ከዚህ ቃል እንደምንረዳውም የተወለደው ህፃን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘለአለማዊ እንደሆነ ነው። ለምሳሌ፦ አንድ ሰው *የውሸት አባት* ቢባል ያ ሰው ውሸታም ነው ማለት ነው። ስለዚህ የተወለደው መሲህ ከጌዜ ቡሃላ የመጣ ካለመኖር ወደ መኖር የመጣ ሳይሆን ዘላለማዊ ነው"... አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው።"(የዮሐንስ ወንጌል 8:58) እንዲሁም ብዙ ማስረጃዎች አሉን


4➫የሰላም አለቃ (The Prince of Peace)( שַׂר שָׁלֹם )(ሳር ሻሎም)፦


 የሰላም አለቃ የሚል ሰላምን የሚሰጥ የሰላም አስገኝ ማለት ነው።

ለዚህም ራሱ ነብዩ በምዕራፍ 26 እንዲህ ይላል፦"12፤ አቤቱ፥ ሥራችንን ሁሉ ሠርተህልናልና #ሰላምን_ትሰጠናለህ።"

(ትንቢተ ኢሳይያስ 26:12፤)__የሚገርመው ኢየሱስ ሰላም ራሱ ከእርሱ ነው የሚወጣው እርሱ የሰላም ባለቤት ነውና፣ከእርሱ እየወጣ በእርሱ ፈቃድ የሚሰጥ መሆኑን ይህ ትንቢት ይነግረናል፡፡ሰላምን ሊሰጡ የሚችሉ ቢኖሩም ፍጹም ሰላምን የሚሰጠው እውነተኛው አምላክ እርሱ እግዚአብሔር የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

"...ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ #ሰላሜን_እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።"(የዮሐንስ ወንጌል 14:27)


በመጨረሻም ይህ በቤተልሄም የተወለደው መሲህ/ንጉስ፤ ንጉሳችን ሰላምን ሰጪያችን ፈጣሪያችን እርሱ እራሱ ያህዌ እግዚአብሄር መሆኑን አረጋግጠናል።



ወስብሀት ለእግዚአብሄር 

         ©✞ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ

Comments

Popular posts from this blog

ዕቅበተ እምነት

ወላዲተ አምላክ

መልስ ለወሒድ ዑመር