የመሲሁ አምላክነት በብሉይ ኪዳን ትንቢት ክፍል ፪

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን


የመሲሁ አምላክነት በብሉይ ኪዳን ትንቢት ክፍል ፪

 የምንመለከተው ትንቢት

 ➞"አወጣጡ ከዘለዓለም የሆነ...(ትንቢተ ሚክያስ 5:2)


              አወጣጡ ከዘለዓለም የሆነ...


ይህ ትንቢት አምላክነቱን እንዴት እንደሚገልፅ አብረን እንመልከት

"...አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል። "(ትንቢተ ሚክያስ 5:2)

       ይህ ትንቢት በብሉይ ኪዳን ካሉ የመሲሁን መምጣትና የመሲሁን አምላክነት ከሚናገሩ ትነቢቶች መካከል አንዱ ነው። የሚወለደውም ከቤተልሔም ነው። አመጣጡም ከዘለዓለም ነው። 

*ከ'-ዘለዓለም* የሚለው ቃል የሚጠቁመን ነገር ቢኖር በexistence ደረጃ ዘለዓለማዊ ወይም ከዘለአለም እንደነበረ ነው። ስለዚህ ከቤተልሄም የሚወለደው መሲህ ካለመኖር ወደ መኖር የመጣ/የተፈጠረ ሳይሆን በቅድምና ያለ ዘለአለማዊ ነው፤ ለዚህም ዋና ማስረጃችን በብሉይ ኪዳን *ከ'-ዘለዓለም* የሚለው ቃል ለእግዚአብሔር ለያህዌ ሲነገር እንመለከታለን፦ 

      "...ዙፋንህ ከጥንት ጀምሮ የተዘጋጀ ነው፥ አንተም *ከ'-ዘለዓለም* ነህ። "(መዝሙረ ዳዊት 93:2)

ያህዌህ በንግስናው ኣለም ሳይፈጠር ያለ *ከ'-ዘለዓለም* ነው ይህም ዘለዓለማዊ አምላክነቱን የሚያመለክተን ነው። 

በሚክያስ ትንቢት መሰረት ደግሞ ይህ ወደ እስራኤላውያን የሚመጣው እራሱ እግዚአብሔር ነው፦

"...እነሆ፥ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፥ ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይረግጣል።"(ትንቢተ ሚክያስ 1:3)

      እንዲሁም የእስራኤል ገዢም እራሱ እግዚአብሔር ያህዌህ ነው፦ "...ሰባሪው በፊታቸው ወጥቶአል፤ እነርሱም ሰብረው ወደ በሩ አልፈዋል፥ በእርሱም በኩል ወጥተዋል፤ ንጉሣቸውም በፊታቸው አልፎአል፥ እግዚአብሔርም በራሳቸው ላይ ነው።"(ትንቢተ ሚክያስ 2:13)

    ✅ስለዚህ መደምደሚያችን፦ የሚመጣው መሲህ ዘለዓለማዊ አምላክ ነው፤ ዘለዓለማዊ አምላክ ደግሞ እግዚአብሔር ያህዌህ ነው። የሚመጣው የእስራኤል ገዥ ቀድሞም ገዢ የነበረው ገዢም የሚሆነው እግዚአብሔር ነው፤ የሚወለደውም ከቤተልሄም ነው።


በወንጌላት የተቀመጠው ፍፃሜው፦

በወንጌል እንደምንመለከተው መሲሑ ጌታ በተወለደ ጊዜ ሰብአ-ሰገል ሊሰግዱለት በመጡ ሰዓት ንጉስ ሄሮድስም ይህ መሲህ የት እንደሚወለድ የካህናት አለቆችን ጠይቆ ነበረ መልሱም፦


"...ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር፤ የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው። እነርሱም። አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት።

➞የማቴዎስ ወንጌል ምዕ. 2 ቁ.3-6


ሄሮድስ መሲሁ የት እንደሚወለድ በጠየቃቸው ሰዓት የካህናት አለቆች መልስም መፅሀፍትን ገልጠው መሲሁን የሚወለደው ከቤተልሄም እንደሆነ ተናግረዋል፤ ይህ የተናገሩትም ከሚኪያስ ትንቢት የሚገኘውን በቀጥታ ጠቅሰው ነው። አሁን ወደ ተነሳንበት እንመለስና አይሁዳውያን በሙሉ የሚክያስ ትንቢት ለመሲሁ ነው ካሉና መሲሁ መለኮታዊ ባህርይ ያለው እራሱ እግዚአብሔር ከሆነ፤ የትንቢቱ ተፈፃሚነት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነውና በቤተልሄም የተወለደው(ሉቃስ 2:4-7) ኢየሱስ ክርስቶስ ዘለዓለማዊ አምላክ ነው።


➞"ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል!"(ትንቢተ ሚልክያስ 3:1)



    "...እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፤ እናንተም የምትፈልጉት #ጌታ በድንገት #ወደ_መቅደሱ ይመጣል፤ የምትወዱትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። "(ትንቢተ ሚልክያስ 3:1)


በዚህ ትንቢት የምንመለከታቸው ዋና ዋና ነጥቦች፦

✅ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል

✅ የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ  ይመጣል!

___

✅ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል።

የሚመጣው ጌታ በቅድሚያ መንገዱን የሚያስተካክልና የሚጠርግ መልክተኛን ይልካል። ይህ ቃል በሌሎች የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችም ያለ ነው ለምሳሌ፦

(ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ. 40:3-5)

"...አዋጅ ነጋሪ ቃል። #የእግዚአብሔርን_መንገድ_በምድረ_በዳ_ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ። ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል፤ #የእግዚአብሔርም_ክብር_ይገለጣል፥ #ሥጋ_ለባሹም_ሁሉ_በአንድነት_ያየዋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና። 


የዚህ ቃል የአዲስ ኪዳን ፍፃሜ ስንመለከት በፊቱ የሚላከው መንገድ ጠራጊ መጥምቁ ዩሀንስ ነው። እንመልከተው፦ 


በመጥምቁ ዮሀንስ አንደበት፦


"... እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ፦ የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና፦ እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት። ዮሐንስ መልሶ፦ እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው። ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ። በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። #አንድ_ሰው_ከእኔ_በኋላ_ይመጣል፥ #ከእኔም_በፊት_ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ፦ መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፦ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።” ➞(ዮሐንስ 1፡23-34)


✅ፈሪሳውያን ዮሀንስን ማንነቱን በጠየቁት ጊዜ እርሱ በኢሳያስ ትንቢት ያለውን "የጌታን መንገድ አቅኑ እያለ

የሚያውጀው እርሱ... በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እንደሆነ ይነግረናል። ትንቢቱም ከላይ የጠቀስንው ሲሆን፦

(ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ. 40:3-5)

"...አዋጅ ነጋሪ ቃል። #የእግዚአብሔርን_መንገድ_በምድረ_በዳ_ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ። ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል፤ #የእግዚአብሔርም_ክብር_ይገለጣል፥ #ሥጋ_ለባሹም_ሁሉ_በአንድነት_ያየዋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና። 


 ታዲያ መጥምቁ ዮሀንስ የማንን መንገድ ነው የጠረገው?


ይህ ግልፅና እና ግልፅ ነው ከምንባቡ እንደምንረዳው የእግዚአብሔርን ነው። ከቁጥር 5 ላይም እግዚአብሔር እንደሚገለጥ ተተንብይዋል የሚገለጠውንም የእግዚአብሄር መንገድ የሚጠርገው መጥምቁ ዮሀንስ ነው።

በሚልኪያስ ያለውንም ትንቢት ስንመለከት 

➞*መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል* ብሎ እግዚአብሔር እራሱ የተናገረ ሲሆን መንገድ የሚጠረግለትም እግዚአብሔር እንደሆነ ግልፅ ነው።

በአዲስ ኪዳንም ስንመጣ እራሱ ቅዱስ ዮሀንስም የእግዚአብሔር ወልድ የኢየሱስ ክርስቶስን መንገድ እንደሚጠርግ የተናገረውን እንመልከት፦ 

"... እናንተ። እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፥ ነገር ግን። #ከእርሱ_በፊት_ተልኬአለሁ እንዳልሁ ራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ።"

(የዮሐንስ ወንጌል 1:28)

ስለዚህ በስጋ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን መንገድ የሚጠርገው ቅዱስ ዮሀንስ ነው መንገድ የሚጠረግለት ደግሞ አምላካችን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ምከንያቱም እግዚአብሔር በሚልክያስ መልክተኛው መንገድን #በፊቴ ያስተካክላል ብሎ የተናገረ ሲሆን እራሱ ቅዱስ ዮሀንስም በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት መንገድን እንደሚጠርግ መስክሮ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር መሆኑን ገልጿል።

በተመሳሳይም በትንቢት መንገድ የሚጠረግለት እግዚአብሔር ነው፦"... የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና። "

(ትንቢተ ኢሳይያስ 40:5)

መጥምቁ ዮሀንስ በዮሀንስ ወንጌል 1:30 እንደተናገረው "... አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ይሆናል።"(የዮሐንስ ወንጌል 1:30) *ከእኔም በፊት ነበርና* የሚለው ሊሰመርበት ይገባል ምክንያቱም በስጋ በመወለድ ጌታችን ኢየሱስ ከመጥምቁ ዮሀንስ በ6 ወር ይዘገያል። ነገር ግን ይህ ምን ይጠቁመናል ቢሉ በአምላክነቱ ቅድመ ዓለም ያለ ቀደማዊ ያለና የሚኖር አምላክ መሆኑን በመንፈስ ቅዱስ መመስከሩ ነው።


በመቀጠል የምንመለከተው የትንቢቱ ክፍል ደግሞ

   

➞የምትፈልጉት #ጌታ(ha adon)፦ ጌታ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል הָאָד֣וֹן ሲሆን ሲነበብም ha adon ይሆናል።(The Lord) ይህ  ቃል በብሉይ ኪዳን ለእግዚአብሔር ጌትነት ብቻ የዋለ ሆኖ እናገኘዋለን ለምሳሌ፦

"... በዓመት ሦስት ጊዜ በአንተ ዘንድ ያለው ወንድ ሁሉ በጌታ(הָאָדֹ֥ן)(The Lord) በእግዚአብሔር ፊት ይታይ።"

(ኦሪት ዘጸአት 23:17)

እንደምንመለከተው ha adon(The Lord) የሚለው መጠሪያ የእግዚአብሔር ነው። ስለዚህ የሚመጣው እግዚአብሔር ወልድ እንደሆነ አረጋገጥን ማለት ነው

➞ሶስተኛው ደግሞ ወደ *መቅደሱ* የሚለውን ቃል እንመልከት በenglish to his temple መቅደሱ የሚለው የባለቤትነቱን ወይም መቅደሱ የእርሱ ገንዘቡ እንደሆነ አመልካች ነው። ማወቅ ያለብን ጉዳይ የትኛውም ፍጡር የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ባለቤት አይደለም። 

መቅደሱ የእርሱ እንደሆነ እግዚአብሔር ይናገራል፦


"...ሰንበታቴን ጠብቁ፥ #መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። "(ኦሪት ዘሌዋውያን 19:30)

"...ቤተ መቅደስህ (Your temple) ቅዱስ ነው በጽድቅም ድንቅ ነው። በምድር ዳርቻ ሁሉና በሩቅ ባሕር ውስጥ ላሉ ተስፋቸው የሆንህ፥ አምላካችንና መድኃኒታችን ሆይ፥ ስማን።"

(መዝሙረ ዳዊት 65:5)

ስለዚህም የሚመጣው የመቅደሱ ባለቤት እግዚአብሔር ነው።

✅ማጠቃለያ፦ በሚልክያስ ትንቢት የሚመጣው የቃል ኪዳን መልክተኛ/መሲህ እግዚአብሔር መሆኑን በጠራ በተብራራ ማስረጃ ተመልከተናል፤ በአዲስ ኪዳን ስንመጣ ደግሞ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሀንስ ስለሚመጣው መሲህ አምላክነት ገልፆልናል። ስለዚህም የመጣው መሲሁ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ተመለከትን ማለት  ነው።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

Comments

Popular posts from this blog

ዕቅበተ እምነት

ወላዲተ አምላክ

መልስ ለወሒድ ዑመር