የመሲሁ አምላክነት በብሉይ ኪዳን ትንቢት ክ.፫


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን

የመሲሁ አምላክነት በብሉይ ኪዳን ትንቢት!


ዳንኤል በራዕይ ያየው የሰው ልጅ!

   በብሉይ ኪዳን ስለ መሲሁ ኢየሱስ ክርስቶስ የተተነበዮ ትንቢቶችን መመልከታችን ይታወሳል ባለፉት ሶስት ክፍሎችም የሚመጣው መሲህ እራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ተመልከተናል፤ ዛሬ ደግሞ ነብዩ ዳንኤል በራዕይ ያየውን የሰው ልጅ የተባለውን እንመለከታለን።


"...በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ #የሰው_ልጅ_የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።  ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ #ሁሉ_ይገዙለት_ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው። (ትንቢተ ዳንኤል ምዕ. 7:13-14)


የምንመለከታቸው ዋና ዋና ነጥቦች!

➞#የሰው_ልጅ_የሚመስል_ከሰማይ_ደመናት_ጋር_መጣ

➞ #ሁሉ_ይገዙለት_ዘንድ

➞ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።


~~~~✝


➞#የሰው_ልጅ_የሚመስል_ከሰማይ_ደመናት_ጋር_መጣ


ይህ ቃል የሚጠቁመን ነብዩ ዳንኤል በራዕዩ የተመለከተው አካል የሰው ልጅ የሚመስል እንደነበረና ይህም የሰው ልጅ ከሰማይ ደመናት ጋር በዘመናት ወደሸመገለው ይመጣል እያለ ይነግረናል። የሰው ልጅ የተባለው አካል ፍጡር እንዳልሆነ በዚሁ አውድ ላይ ካለው ➞*በደመናት ጋር መጣ* የሚለውን ቃል በብሉይ ኪዳን ያለውን ምልከታ እናስፋ፦


"...ይሹሩን ሆይ፥ በሰማያት ላይ ለረድኤትህ፥ #በደመናትም_ላይ_በታላቅነት_እንደሚሄድ_እንደ_እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም።(ኦሪት ዘዳግም ምዕ. 33:26)

"...ስለ ግብጽ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን #ደመና እይበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል።"(ትንቢተ ኢሳይያስ 19:1)


በእነዚህ የመፅሀፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደምንረዳው በደመናት የሚመጣ እራሱ እግዚአብሔር ነው፤ በመፅሀፍ ቅዱስም ይህ ክብር የተሰጠው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው። በአዲስ ኪዳን ስንመጣ ጌታችን እራሱን የሰው ልጅ እያለ ሲጠራ እንመለከታለን ለምሳሌ፦

"... የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።"(የማቴዎስ ወንጌል 12:8)

ይህ የሰው ልጅ እያለ እራሱን የሚጠረው በስጋ ከሰው የተወለደው እግዚአብሔር ስለሆነ ነው ይህንን የምናውቀው ደግሞ *የሰንበት ጌታ* በመሆኑ ነው።

በተጨማሪም ለፍርድ በደመና እንደሚመጣ፦


"... የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ #የሰው_ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር #በሰማይ_ደመና_ሲመጣ_ያዩታል፤"➞(የማቴዎስ ወንጌል 24:30)


እንዲሁም፦ 

"... ኢየሱስም። እኔ ነኝ፤ #የሰው_ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ #በሰማይም_ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ። ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና። ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል? #ስድቡን_ሰማችሁ፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም ሁሉ። ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት።➞(የማርቆስ ወንጌል ምዕ. 14:62-64)


በዚህ ክፍል ላይ ጌታችን *የሰው ልጅ ... በደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ* ብሎ እርሱ በብሉይ ኪዳንም የተተነበየለት መለኮት የሆነው መሲህ መሆኑን፤ እግዚአብሔር መሆኑን ስለገለጠለትና ስለ ገባው ነው ሊቀ ካህኑ * #ስድቡን_ሰማችሁ * ሲል የምናደምጠው። ጌታችን በነበረበት ጊዜ የነበሩ አይሁዶች እንደ ስድብ( Blasphemy ) የሚቆጥሩት ምን ሲያደርግ ነው ብለን ምልከታችን ወደ ወንጌላት እናዙር፦

➞ በመጀመሪያ ስድብ(blasphemy) የምንለው "The act of claiming the attributes of a deity." ምንጭ፦ www.wiktionary.org 

ስለዚህ ስድብ(blasphemy) ማለት እራስን አምላክ ማድረግ ነው።

እስኪ የአይሁዶችን ምልከታ እንመልከት፦ 


"... ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን። #አንተ ልጅ_ኃጢአትህ_ተሰረየችልህ_አለው።

#ከጻፎችም_አንዳንዶቹ በዚያ ተቀምጠው ነበር በልባቸውም። ይህ ሰው ስለ ምን እንደዚህ ያለ #ስድብ ይናገራል? #ከአንዱ_ከእግዚአብሔር_በቀር_ኃጢአት_ሊያስተሰርይ_ማን_ይችላል? ብለው አሰቡ።"(የማርቆስ ወንጌል ምዕ. 2:5-7)

   ጻፎችም በንግግራቸው ትክክል ናቸው ምክንያቱም ኃጢያትን ይቅር ማለት የሚችል በደልን የሚደመስስ 

ማንም ሳይሆን እግዚአብሔር ብቻ ነው ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር መሆኑ ስላልገባቸው እንደ ፍጡር ስለቆጠሩት ተሳደብክ ሲሉት ይደመጣል። (በዚህ ንግግራቸው አይሁድ እግዚአብሔርን ተሳድበሃል ያሉት እሱ እግዚአብሔር መሆኑን በተግባሩ ስላሳያቸው  ነው።)


"...አይሁድም። ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ #ስለ_ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን #ራስህን_አምላክ_ስለ_ማድረግህ_ነው እንጂ ብለው መለሱለት።"(የዮሐንስ ወንጌል 10:33)

በዚህ ክፍል ላይ ደግሞ ጌታችን ለአይሁድ *እኔ እና አብ አንድ ነን* ባለ ጊዜ አይሁድ እርሱን ለመውገር ድንጋይ ያነሱ ሲሆን ምክንያታቸው ደግሞ በእነሱ እሳቤ "እኔ አብ አንድ ነን" ብሎ አምላክነቱን መግለጡ እንደ ስድብ ቆጠረውታል ፤ ነገር ግን ጌታችን በእውነትም እነሱ እንዳሰቡት ሳይሆን አምላክ ነው።


ስለዚህ በሁሉም ክፍሎች ስንመለከት የኢየሱስ ክርስቶስን ንግግር እንደ ስድብ የሚቆጥሩት #እራሱን_ከእግዚአብሔር_ጋር_አንድ_አድርጎ_ሲናገር_ብቻ_ነው። ወደ ማርቆስ ወንጌል ምዕ. 14:62-64 ስንመለስ ሊቀካህናቱ የኢየሱስን ንግግር እንደስድብ የቆጠረው ጌታችን በዳንኤል ላይ ያለውን ጠቅሶ በመናገሩ ምክንያት ነው፤ በዳንኤል ላይ ያለው በደመና መምጣት የእግዚአብሔር ክብር ብቻ ስለሆነም ነው።

 

ስለዚህ የሰው ልጅ የተባለው እራሱ እግዚአብሔር ነው፤ ስጋን ተዋህዶ ከሰው ስለተወለደ የሰው ልጅ ይባላል። ታዲያ ይህ የሰው ልጅ እግዚአብሔር ከሆነ እና የሸመገለውም እግዚአብሔር ከሆነ እንዴት ወደ እግዚአብሔር መጣ ተባለ ቢሉ በስላሴ አስተምህሮ አብ እግዚአብሔር ነው ወልድ እግዚአብሔር ነው መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው። ይህን በምስጢረ ስላሴ ማየታችን ይታወሳል። ስለዚህም በዘመናት የሸመገለው እግዚአብሔር ሆኖ የሰው ልጅ የተባለውም እግዚአብሔር ከሆነ፤ እግዚአብሔር በአካል ከአንድ በላይ መሆኑንም ያሳየናል።


        ➞ #ሁሉ_ይገዙለት_ዘንድ

የራዕዩ ሁለተኛው ክፍል ስለ መሲሁ አምላክነት የሚጠቁመን ይህ ነው። አህዛብ #ሁሉ የሚገዙለት ማነው?

 #ሁሉ የሚገዙለት እግዚአብሔር ነው መፅሀፍ ቅዱስም ምስክር ነው፦ 


"... አሕዛብ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ መንግሥታትም ለእግዚአብሔር ይገዙ ዘንድ።"(መዝሙረ ዳዊት 102:22)

✅ስለዚህ አህዛብ ሁሉ የሚገዙለት እራሱ እግዚአብሔር ነው። በተጨማሪ *ይገዙለት ዘንድ* የሚለው ቃል ለአምልኮተ እግዚአብሔር የሚቀርብ መሆኑን እንመልከተው፦ 


የዳንኤል ትንቢት በአራማይክ ቋንቋ እንደመፃፉ መጠን#ይገዙለት የሚለው ቃል “ይፕላኹን” יִפְלְח֑וּן ይላል፡፡ የቃሉን መነሻ ግስ ስንመለከተው “ፕላኽ” ሲሆን ይህም ቃል ለፈጣሪ ብቻ የሚደረግን አምልኮ የሚያሳይ ቃል ነው። ለምሳሌ በዛው በዳንኤል ትንቢት ላይ

"...የዚያን ጊዜም ንጉሡ አዘዘ፥ ዳንኤልንም አምጥተው በአንበሶች ጕድጓድ ጣሉት፤ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም። ሁልጊዜ #የምታመልከው_አምላክህ እርሱ ያድንህ አለው። "➞(ትንቢተ ዳን


ኤል 6:16)

የምታመልከው የሚለው ቃል ይፕላኹኒ ሲሆን ለአምላክ ብቻ የሚገባ አምልኮ መሆኑን እንመለከታለን ስለዚህ ዳንኤል 7፡13-14  ላይ የተጠቀሰው “የሰው ልጅ” የተባለው አካል ለፈጣሪ ብቻ የሚገባውን አምልኮ የሚቀበል ነው።


  ➞ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።


        እንደምናውቀው ዘላለማዊ ግዛት ያለው መንግስቱ የማይጠፋ እግዚአብሔር ብቻ ነው[በየትኛውም እምነት የሚታመንም ጉዳይ ነው]

       በዛው በትንቢተ ዳንኤል ላይ የንጉሱን ምስክርነት እንመለከታልን ንጉሱም እንዲህ አለ፦"... በመንግሥቴ ግዛት ሁሉ ያሉ ሰዎች በዳንኤል አምላክ ፊት እንዲፈሩና እንዲንቀጠቀጡ አዝዣለሁ፤ #እርሱ_ሕያው_አምላክ_ለዘላለም_የሚኖር_ነውና፤ #መንግሥቱም_የማይጠፋ_ነው፥ #ግዛቱም_እስከ_መጨረሻ_ድረስ_ይኖራል። "(ትንቢተ ዳንኤል 6:26)

በዚህም የምንረዳው ዘላለማዊ ግዛት ያለው መንግስቱ የማይጠፋ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ይህ የሰው ልጅም  እግዚአብሔር መሆኑ በማያሻማ መልኩ በዳንኤል ራዕይ ተረድተናል።

የሚነሱ ጥያቄዎች ከነመልሳቸው፦

1-የሰው ልጅ የሚመስል የተባለው የልዑሉ ቅዱሳን እንጅ መሲሁ አይደለም!

መልስ፦ በዚህ ክፍል ላይ የሰው ልጅ የሚመስለው የልዑሉ #ቅዱሳን ናቸው የሚል ሽታውም የለም። የሰው ልጅ ተብሎ በነጠላ ማንነት የተቀመጠውን ለቅዱሳን ነው ማለት የለየለት ክህደት ነው። ይህን ለማለት የሚያስደፍራቸውም በቁጥር 22 ላይ ያለው ቃል ነው  ነገር ግን "...የልዑሉቅዱሳን መንግሥቱን ይወስዳሉ፥እስከ ዘላለም ዓለምም መንግሥቱንይወርሳሉ።➞(ዳንኤል 7፥18) 

ይህ ቃል የሚነግረን ምንድነው ብንል መሲሁ ዳግም ተመልሶ ሲመጣ ቅዱሳኑ ሁሉ መንግስቱን እንደሚያወርሳቸው እየተናገረ ነው። (ማቴዎስ 25:34)

እሚገርመው ነገር ደግሞ የአይሁድ ሊቃውንት የኢየሱስ ክርስቶስን መሲህነት ባያምኑም ትንቢቱ ለመሲህ እንደሆነ ያምናሉ፦

“R. Alexandr said: “R. Y’hoshu’a ben Levi explained:- ’If they will be righteous, [the Messiah will come] on the clouds of heaven (Daniel 7.13); if they will not be righteous, [he will come] as a poor man riding upon an ass (Zech 9.9)'”]


“ረቢ እስክንድር እንዲህ አለ፡- “ረቢ የሆሹኣ ቤን ሌዊ እንዳብራራው፦  “ጽድቅን ካደረጉ [መሲሁ] በሰማይ ደመና ይመጣል (ዳንኤል 7፡13)፤ ጽድቅን ካላደረጉ ጎስቋላ ሰው ሆኖ በአህያ ይመጣል (ዘካርያስ 9፡9)፡፡”

 ➞B. Sanh 98a ምንጭ

ስለ እውነትነቱ በማስፈንጠሪያው ገብተው ይመልከቱ

ታዲያ በአይሁድ ሊቃውንትም ለመሲሁ እንደሆነ በተጨባጭ ተነግሮ ለመሲሁ አይደለም ማለት የለየለት ክህደት ነው።


2-“የሰው ልጅ የሚመስል” የተባለው ኢየሱስ ነው ቢባል እንኳን አሁንም ፍጡር ከመሆን የዘለለ ማንነት የለውም ምክንያቱም በሃረጉ ውስጥ “ተሰጠው” የሚል ሃይለ–ቃል አለ፤ ሰጪው ደግሞ“በዘመናት የሸመገለው"አብ ነው፤አንዱ አምላክ ለኢየሱስ የአባቱን ዙፋን ሰጥቶታል።


መልስ፦ 


      እኛ ስለ ኢየሱስ ስናምን አምላክ ብቻም  ብለን ሳይሆን ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ነው። እንደ አምላክነቱ ፍጥረትን ለእርሱ በራሱ ፈጥሮ ያስተዳድራል ግዛቱም ዘለዓለማዊ ነው፣ ሰው እንደመሆኑ ደግሞ "ተሰጠው" ተባለ።


    በዳንኤል የተጠቀሰው *የሰው ልጅ* መንግስቱ ምንድነው? ብንል ዘለዓለማዊ ነው። ዘለዓለማዊ ግዛት ደግሞ የእግዚአብሔር ነው። ማንኛውም ፍጡር ደግሞ ዘላለማዊ ወይም መለኮታዊ መንግስት የለውም ሲጥል ኢየሱስ የሚነግሰው በዳዊት ዙፋን ላይ ነው። 

     "...እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤"

(የሉቃስ ወንጌል 1:32)

    በዚህ በዳዊት ዙፋን ላይም ዘለዓለማዊ መንግስት ያለው እግዚአብሄር ዙፋኑን ሊያደላድል ነው። በዳዊት ዙፋን ላይም ኢየሱስ ክርስቶስ ወራሽ ሆኖ ይነግሳል። ወራሽነቱም በተዋሃደው የዳዊትን ዘር ከድንግል ማርያም በተወለደው በስጋው ነው። አምላክ ስጋን ተዋህዶ ዘለዓለማዊ መንግስቱን ሲያደላድል እንመለከታለን። ተሰጠው ሲባልም ይህ በዳዊት ዘር በመሆኑ የሚገኘውን የዳዊትን ዙፋን ነው። እግዚአብሄር አብ ለወልድ የዳዊትን ዙፋን ሰጥቶታል ነገር ግን አምላክ በመሆኑ ንግስናው ዘላለማዊ ነው።

✅ማጠቃለያ፦ ነብዩ ዳንኤል በራዕይ ያየው *የሰው ልጅ* መለኮታዊ ክብር ሁሉ ያለው እና አምላክ የሆነ ነው። አህዛብ ሁሉ የሚያመልኩት እና ዘለዓለማዊ ግዛትና የማያልፍ መንግስት ያለው ነው። እርሱም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

         ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

    ©✞ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ 

Comments

Popular posts from this blog

ዕቅበተ እምነት

ወላዲተ አምላክ

መልስ ለወሒድ ዑመር