የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት...
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ ፡ በወልድ ፡ በመንፈስ ቅዱስ ስም!
ሰላም ለእናንተ ተወዳጅ የገጻችን ቤተሰበሶች እንደምን አላችሁ? " እግዚአብሔር ይመስገን" ብለን ስሙን እንዲናመሰግን የፈቀደልን አምላክቻን የተመሰገነ ይሁን ለዛሬ " የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት" በሚል ዙሪያ ሙስሊሞች የሚያነሷቸውን ሙግቶች እንመለከታለን። ሙግቱ በተደጋጋሚ የሚነሳ በመሆኑ ከነፍፃማው ተመልሶ እንዳይነሳ ለማድረግ ሰፋ አድርገን ተመልክተነዋልና ሀሳብዎትን ሰብሰብ አድርገው ያንብቡ!
ሙስሊሞች የኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅነት በሚቃወሙ ጊዜ ከሚያነሷቸው የሙግት ሀሳቦች መካከል ሶስቱን በዚህ ፅሁፍ የምንመለከት ይሆናል በቀጣይ ጌታ ቢፈቅድ አራተኛውን ይዘን እንቀርባለን። ሙግቶቹ እንደሚከተለው ይቀርባሉ ፦
❌ ➊፦ በመፅሀፍ ቅዱስ "የእግዚአብሔር ልጅ" የተባለው ኢየሱስ ብቻ አይደለም ስለዚህ ሌሎች በተባሉበት መንገድ ኢየሱስም ልጅ ተብሏል
❌ ➋፦ መውለድ እንስሳዊ ባህሪይ እንጂ አምላካዊ ባህሪይ አይደለም
❌ ➌፦ ኢየሱስ እግዚአብሔር ወይንስ የእግዚአብሔር ልጅ?
~~~
❌ ➊፦ በመፅሀፍ ቅዱስ "የእግዚአብሔር ልጅ" የተባለው ኢየሱስ ብቻ አይደለም ስለዚህ ሌሎች በተባሉበት መንገድ ኢየሱስም ልጅ ተብሏል።
እውነት ነው በመፅሀፍ ቅዱስ "የእግዚአብሔር ልጅ" የተባለው ኢየሱስ ብቻ አይደለም። " የእግዚአብሔር ልጅ" የተባሉትን እንደምሳሌ ብንጠቆስ፦
#መላእክት፦
“ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ።”— ኢዮብ 1፥6
“እግዚአብሔርን በሰማይ የሚተካከለው ማን ነው? ከአማልክትስ ልጆች እግዚአብሔርን ማን ይመስለዋል?”— መዝሙር 89፥6
#መንገዳቸውን በቃል ኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉ፦
#እስራኤላውያን ፦ “በልቅሶ ወጡ እኔም በማጽናናት አመጣቸዋለሁ፤ በወንዝ ዳር በቅን መንገድ አስኬዳቸዋለሁ፥ በእርሱም አይሰናከሉም፤ እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፥ ኤፍሬምም በኵሬ ነውና።”— ኤርምያስ 31፥9
#ንጉስ_ዳዊት፦ መዝሙር 89
²⁶ እርሱ፦ አባቴ አንተ ነህ፥ አምላኬ የመድኃኒቴም መጠጊያ ይላል።²⁷ እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁ፥ ከምድር ነገሥታትም ከፍ ይላል።
#ንጉሱ_ሰሎሞን ፦ “እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ክፉ ነገርም ቢያደርግ፥ ሰው በሚቀጣበት በትርና በሰው ልጆች መቀጫ እገሥጸዋለሁ፤” — 2ኛ ሳሙኤል 7፥14
#በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በእርሱ መንፈስ(በመንፈስ ቅዱስ) ለሚመሩ፦
ሮሜ 8
¹⁴ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና።¹⁵ አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና።
እግዚአብሔር አባት እሆናቸዋለሁ ያላቸውን እና ልጅ ተብለው የተጠሩትን ለምሳሌ ያህል በጥቂቱ ተመለከትን። ሁሉም እስካሁን የተዘረዘሩት ግን አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር የእነርሱ ልጅነት #በጸጋ የተገኘ እንጂ በአካላዊ መወለድ ከአብ የተገኙ ሁነው አይደለም።
በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ለሚጠመቁት እንዳውም ልጅነትን የሚሰጣቸው እራሱ ነው፦
ዮሐንስ 1
¹² ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት ሁሉ ግን 👉 #የእግዚአብሔር_ልጆች የመሆን መብት ሰጣቸው።¹³ እነዚህም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ፣ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።
ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ የሚሆኑበትን ስልጣን እየሰጣቸው ሁሉም ከኢየሱስ ጋር በልጅነት አንድ ናቸው ብሎ ማለት ቂልነት ነው።
የኢየሱስ ልጅነት ግን ከላይ ከዘረዘርናቸው የተለየ ነው የእርሱ ከጊዜ ዘኋላ የተገኘ ወይንም በጸጋ የተቀበለው ልጅነች አይደለም። በቅድመ አለም በረቂቅ ውልደቱ ከአብ የተገኘ እንጂ። የእርሱ ልጅነት የተለየ መሆኑን እንመልከት፦
📌 የኢየሱስ ልጅነት እኛ በጸጋ ከተቀበልነው የተለየ መሆኑን እንድንረዳ ከሚያደርጉን ነገሮች መካከል የኢየሱስ ልጅነት በብሉይ ኪዳንም የተመሰከረለት መሆኑ አንዱ ነው፦
“የእግዚአብሔርን ሕግ ዐውጃለሁ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤”— መዝሙር 2፥7
“ወደ ሰማይ የወጣ፣ የወረደስ ማነው? ነፋስን በእጁ ሰብስቦ የያዘ ማነው? ውሆችንስ በመጐናጸፊያው የጠቀለለ ማነው? የምድርን ዳርቻዎች ሁሉ የወሰነ ማነው? ስሙ ማን ነው? የልጁስ ስም ማን ይባላል? የምታውቅ ከሆነ እስቲ ንገረኝ!”— ምሳሌ 30፥4
ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ ልጅነቱ እየተመሰከረለት የመጣ ከኢየሱስ ውጭ አንድስ እንኳን ይኖር ይሆን?
📌 ኢየሱስ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ነው፦
“ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ እቅፍ ያለው #አንድያ_ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው።”— ዮሐንስ 1፥18 (በተጨማሪም ዮሀ 1:14 ፣ 3:16 ፣ 18 ፣ 1ኛ ዮሀ 4:19ኝን ይመልከቱ)
በመፅሀፍ ቅዱስ አንድያ ልጅ በሚል የተተረጎመው የግሪክ ቃል "monogenes" ሲሆን ወንጌላዊው በዚህ ቃል የኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅነት ለመግለፅ ሲያውለው ከኢየሱስ ውጭ ያለ ልጅነት ግን በዚህ ቃል በፍፁም አልተገለፀም ። ይኼም የኢየሱስ ልጅነት ከእኛ የተለየ እንደሆነ በግልፅ ያሳየናል።
📌 የኢየሱስ ልጅነት በብሉይ ኪዳን ተልከው ከነበሩ ነብያት የተለየ እንደሆነ እራሱ በግልፅ ነግሮናል፦
ማቴዎስ 21
³³ “ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ አንድ የወይን ዕርሻ ባለቤት ነበረ፤ በዕርሻው ዙሪያ አጥር አጠረ፤ ለወይኑ መጭመቂያ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ለጥበቃ የሚሆን ማማ ሠራ፤ ከዚያም ዕርሻውን ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።³⁴ የመከር ወራት ሲደርስ፣ ፍሬውን ለመቀበል አገልጋዮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላካቸው።³⁵ “ገበሬዎቹም አገልጋዮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት።³⁶ እርሱም ከፊተኞቹ የሚበልጡ ሌሎች አገልጋዮቹን ላከ፤ ገበሬዎቹም ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው።³⁷በመጨረሻም፣ 👉‘#ልጄን_ያከብሩታል’ በማለት ልጁን ላከ።³⁸ “ነገር ግን ገበሬዎቹ #ልጁን_ባዩት_ጊዜ፣ ‘👉 #ይህማ_ወራሹ ነው፤ ኑ፣ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ።³⁹ ይዘውም ከወይኑ ዕርሻ ውጭ አውጥተው ገደሉት።
ኢየሱስ ግልፅ በሆነ ምሳሌው የእርሱ ልጅነት በብሉይ ኪዳን ሲላኩ ከነበሩት ነብያት የተለየ እንደሆነ እንዲህ አስተምሮናል እያለ ነብያት(ለምሳሌ ዳዊት) ልጅ በተባለበት ሁኔታ ነው ልጅ የተባለው እንዴት ማለት ይቻለናል?
📌 በተጨማሪም የኢየሱስ ልጅነት ከሁሉ የተለየ መሆኑን የምንረዳው ከእግዚአብሔር ዘንድ በሆነው ተአምራዊ ምስክርነቱ ነው፦
ማቴዎስ 3
¹⁶ ኢየሱስም እንደ ተጠመቀ ከውሃው ወጣ፤ ወዲያውኑም ሰማይ ተከፍቶ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድበት አየ።¹⁷ እነሆ፣ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።
“እርሱ እየተናገረ ሳለ፣ ብሩህ ደመና ሸፈናቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ ተሰማ።”— ማቴዎስ 17፥5
ማቴዎስ 16
¹⁶ ስምዖን ጴጥሮስም፣ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት መለሰ።¹⁷ ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ብፁዕ ነህ፤ ይህን የገለጠልህ በሰማይ ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም አይደለም።
በእነዚህ ጥቅሶች እንደምንመለከተው እግዚአብሔር የኢየሱስን ልጅነት ሲመሰክር በተአምራት በታጀበ መልኩ ነበር። እዚች ላይ ሙስሊሞችን አንዲት ጥያቄ እንጠይቅ ፦ የኢየሱስ ልጅነት እንደሌሎች ከነበረ የእርሱን ልጅነት ለመመስከር ተአምር መከሰቱ #ለምን አስፈለገ? ለቅዱስ ጴጥሮስስ ከአምላክ የሆነ መገለጥ #ለምን አስፈለገው?
ከእግዚአብሔር አብ እና ከሐዋርያት ምስክርነት ወጥተን በጊዜው የነበሩትስ ሰዎች ምን አይነት ምልከታ ነበራቸው? የሚለውን እንመልከት፦
⭕፦ አይሁዳዊያን፦ በጊዜው የነበሩ አይሁዳዊያን እነርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ቢባሉም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ማለቱ ሊገድሉት ይሞክሩ ነበር፦
ማቴዎስ 26
⁶³ ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም፣ “በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ ንገረን” አለው።⁶⁴ ኢየሱስም፣ “አንተው ራስህ ብለኸዋል፤ ነገር ግን ለሁላችሁም ልንገራችሁ፤ ወደ ፊት የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው።⁶⁵ በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ፣ “በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሮአል፤ ከዚህ ሌላ ምን ምስክርነት ያስፈልገናል? በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል መናገሩን እናንተው ራሳችሁ ሰምታችኋአል፤
“አይሁድም፣ “እኛ ሕግ አለን፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ስላደረገ በሕጋችን መሠረት መሞት አለበት” አሉ።”— ዮሐንስ 19፥7
ሙስሊሞች በሚሉት ሂሳብ ከሆነ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ማለት የሚያስቆጣ አይደለም እና #ለምን ሊገድሉት ፉለጉ?
⭕ የአጋንንቶች ጩኸት፦ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር በሚያልፍበት መንገድ በአጋንንት ተይዘው የነበሩ ሁለት ሰዎች ኢየሱስ ሲያዩ ያደረባቸው አጋንንት ልፈፋውን ጀምሯል።
ማቴዎስ 8
²⁸ ባሕሩን ተሻግሮ ጌርጌሴኖን ወደሚባል አገር እንደ ደረሰ፣ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከሚኖሩበት የመቃብር ቦታ ወጥተው ተገናኙት። በዚያ መንገድ ሰው ማለፍ እስከማይችል ድረስ እጅግ አደገኞች ነበሩ።²⁹ እነርሱም “የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፤ ከእኛ ምን ጕዳይ አለህ? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን መጣህን?” እያሉ ጮኹ።³⁰ ከእነርሱ ትንሽ ራቅ ብሎ፣ የብዙ ዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር።
የለፈፈው ኢየሱስ ሲያይ እንደሆነ ልብ በሉ። የኢየሱስ ልጅነት እንደማንም ከሆነ ከሐዋርያቱ በላይ የኢየሱስ መኖር አጋንንቱን #ለምን እንደዛ አደረገው?
⭕ የሰይጣን ፈተና፦ ሰይጣን ኢየሱስን ሊፈትን ወደተራራ ወስዶ ያለው ቢኖር " የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ " የሚል ነው።
““የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ራስህን ወደ መሬት ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤ “ ‘እግርህ በድንጋይ እንዳይሰናከል፣ በእጃቸው ያነሡህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል።’ ””— ማቴዎስ 4፥6
የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነቱ እንደማንም ከሆነ #ለምን በዚህ ጠርቶ መፈተን አስፈለገው?
የሰይጣን ምስክርነት በቂ እና ታማኝ ባይሆንም ሰይጣን የእግዚአብሔር ልጅ የሚለውን ሌሎች ከሚሉት የተለየ ክብር ያለው እንደሆነ ተረድቷል።
ማጠቃለያ፦ እስካሁን " #ለምን?" በማለት የጠየቅናቸው ጥያቄዎች ሊኖራቸው የሚችለው መልስ አንድ እና አንድ ኢየሱስ ከሁላችን የተለየ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ስለሆነ ነው።
ከዚህ በላይ በተዘረዘሩ እና ከሌሎች ካልተጠቀሱ ማስረጃዎች እንደምንረዳው ኢየሱስ የእግዚአብሔር ብቸኛ ልጅ ፣ ከአካሉ አካልን ፣ ከባህሪው ባህሪውን ነስቶ ፣ እንዲህ ልንለው በማንችለው ከሰው ልጅ በላይ በሆነ ልደቱ ከአብ የተወለደ ነው!!።
❌ ➋፦ መውለድ እንስሳዊ ባህሪይ እንጂ አምላካዊ ባህሪይ አይደለም።
ይህንን ሙግት የሚያነሱት ታላላቅ መምህራን የተባሉ መሆናቸው መምህራኖቹን እንድንታዘብ ያደርገናል። በዚህ ሙግት የሚታዩ ሁለት ድክመቶች አሉ፦
፩፦ ከላይ ባየነው መሰረት ኢየሱስ ከአብ የተወለደው ቅድመ አለም የሆነ ልደት ነው። "ቅድም አለም" ልደት ማለት አለም ሳይፈጠር በፊት ማለት ነው። አለም ወይንም የሰው ልጅ ከመፈጠሩ በፊት የተወለደውን ውልደት እንዴት አድርገን ነው ሰውኛ ባህሪይ ስለሆነ አይቻልም የምንለው? አስቡት ኢየሱስ ከአብ ሲወለድ የሰው ልጅ ወይንም የሰው ባበህሪይ የለም። የሰው ባህሪይ በሌለበት ሰዎኛ ነው ማለት በእውነት የዋህነት ነው።
፪፦ ሁለተኛው ድክመታቸው ደግሞ የኢየሱስን ልደት ከሰው አወላለድ ጋር ተመሳሳይ አድርጎ ማቅረቡ ነው። ምን ለማለት ነው? እንደምናውቀው የሰው ልጅ ወይንም የፍጡራን ዘር የመተካት ሂደት በሁለት ተቃራኒ ፆታ አማካኝነት የሚከናወን ነው። ያ ማለት ዘሩ የሚገኘው በወንዱና የሴቲቱ ዘር አማካኝነት ነው ማለት ነው። የኢየሱስ ውልደት ግን ከዚህ የተለየ ነው ምክንያቱም ውልደቱ ቅድመ አለም ያለ እናት ከአባት ብቻ የከናወነ ነው። ያለ ተቃራኒ ፆታ የሆነን ውልዴት እንዴት ሁኖ ነው የሰውኛ ባህሪይ ነው ማለት የሚቻለው? እንደምናየው ውልደቱ ከሰው ባህሪይ ውጭ የሆነ ነው።
❌➌ ፦ ኢየሱስ እግዚአብሔር ወይንስ የእግዚአብሔር ልጅ?
እንደ እውነቱ ይኼን ጥያቄ ስለጠየቁት ብቻ እንመልሳለን እንጂ ከጥያቄ ጎራ የሚመደብም ሁኖ አይደለም። ለመመለስ ያህል ግን በመጀመሪያ ስለ ሥላሴ ማወቅ ይገባል። በሥላሴ ሶስት አካላት እንዳሉ እስከተረዳን ድረስ ጥያቄው ጥያቄ አይሆንም። "የእግዚአብሔር ልጅ" በምንልበት ጊዜ እግዚአብሔር የሚለው አብን የሚያመለክት እንደሆነ መረዳት ያሻል ስለዚህ ኢየሱስ ከሶስቱ አካላት አንዱ እንደመሆኑ እግዚአብሔር ሲሆን የአብ ልጅ እንደመሆኑ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅ እንለዋለን። ወይንም በሌላ አባባል ጥያቄያቸውን ስናቀርበው " ኢየሱስ እግዚአብሔር ወይንስ የአብ ልጅ?" የሚል ነው ይሄ ደግሞ ምንም ጥያቄ የሚያስነሳ አይደለም።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
©✞ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
Comments
Post a Comment