ምስጢረ ሥጋዌ
ክፍል ፪
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ ፡ በወልድ ፡ በመንፈስ ቅዱስ!
በክፍል አንድ አምላክ ለምን ሰው ሆነ የሚለውን መመልከታችን የሚታወስ ነው። ዛሬ ደግሞ፦
አምላክ ሰው ሲሆን *ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ* ሆነ ወይስ *አንድ አካል ሁለት ባህርይ* ??(የካቶሊኮች ግራ መጋባት) የሚለውን እንመለከታለን።
አምላክ ሰው የሆነበት ሁናቴ ተዋህዶ ይባላል።
ተዋህዶ ማለትም ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ ማለት ነው።
ከተዋሕዶ በፊት ሁለት ባሕርያት ሁለት አካላት ነበሩ፡፡
ሁለት አካል የተባሉት መለኮታዊ አካልና ስጋዊ አካል ናቸው። መለኮታዊ አካል የምንላቸው የማይዳሰሰውን፣ የማይጨበጠውን፣ እሳታዊውን አካል ነው። ስጋዊ አካል የምንለው ደግሞ የሚዳሰስ የሚጨበጥ፣ ግዙፍ፣ ውሱን ናቸው። ሁለት ባህርይ የተባሉት ደግሞ መለኮታዊ ባህርይ እና ስጋዊ ባህርይ፦ ፊተኛ እና ኋለኛ፣ ዘለዓለማዊነት፣ ፈጣሪነት፣ ሁሉን ቻይነት፣
ስጋዊ ባህርይ፦ መራብ መጠማት መሞት መድከም የሚስማማው ነው። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ተዋህደው አንድ አካል አንድ ባህርይ ሆነዋል።
ከሁለት አካል አንድ አካል ሲባል ረቂቅ መለኮት ርቀቱን ሳይለቅ፣ ግዙፍ ሥጋ ግዙፍነቱን ሳይለቅ ማለትም ግዙፍ ሥጋ ረቂቅ መለኮትን ግዙፍ ሳያደርገው፣ ረቂቅ መለኮት ግዙፉን ሥጋ ሳያረቀው በመጠባበቅ (በተዐቅቦ) ተዋሐዱ ማለት ነው፡፡ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ማለት ደግሞ መለኮት የእርሱ ያልሆነውን የሥጋ ባሕርይ ባሕርዩ አድርጎ፣ ሥጋም የእርሱ ያልሆነውን የመለኮት ባሕርይ ባሕርዩ አድርጎ ተዋሐዱ ማለት ነው፡፡
ለዚህም ምሳሌ የሚሆነን አንድ ቅዱስ አባት(ቅዱስ ቄርሎስ) የሰጠውን ምሳሌ እንመልከት፦ ብረት ከእሳት ጋር ሲገባ ከእሳት ሲዋሃድ መጠኑን ቅርፁን ወርዱን ቁመቱን ሳይለቅ የእሳቱን ሀብት ወርሶ ሙሉ ሁለንተናው ፍፁም እሳት እንደሚሆን፤ እሳትም የእሳትነቱን ባህርይ ሳይተው በብረቱ መጠን የብረቱን ቅርፅ እንደሚይዝ ኋላም አንጥረኛ በመዶሻ ሲያለዝበው በመጋዝ ሲተረትረው በብረትና በእሳት መካከል ምንም ልዩነት እንደማይታይ መለወጥ ኅድረት የሌለበት የመለኮትና የትስብዕት ተዋህዶ እንደዚህ ነው።
ይህ ተዋህዶም፦
➞ያለመለወጥ
ይህም በቃና ገሊላ ውኃ ወደ ወይን ጠጅ እንደተለወጠው ሳይሆን የመለኮትነቱ አካል፣ ባሕርይ ወደ ትስብዕት አካል፣ ባሕርይ ሳይለወጥ፣ የትስብዕትም አካል፣ ባሕርይ ወደ መለኮትነት ሳይለወጥ ነው በተዋሕዶ አምላክ ሰው፣ ሰውም አምላክ የሆነው፡፡
ለዚህም ምሳሌ፦ ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ መለኮትነት ወደ ስጋ እንዳልተለወጠ ኢየሱስ ክርስቶስ በባህር ልብ ውስጥ ያለውን ሲያውቅ እንመለከታለን(ማቴ. 17:27)
እንዲሁም ስጋ ወደ መለኮትነት እንዳልተለወጠ የምንመለከተው መለኮት በለበሰው ስጋ ሲራብ ሲጠማ ስናይ ነው፦ (ማቴ. 4:24...)
➞ያለመመለስ
የመለኮትና የትስብዕት ተዋሕዶ ያለመመለስ ነው፡፡ የሙሴ በትር እባብ ከሆነች በኋላ ተመልሳ በትር እንደሆነችው መመለስ የሌለበት ነው፡፡ ይህ ማለት መለኮት(ቃል) በተዋህዶ ስጋ ከሆነ ቡሃላ ከሞቱ ወይም ከእርገቱ ቡሃላ ይህ ተዋህዶ ፈርሶ ሰውነትም መለኮትም ወደ ነበረበት አይለያዩም ማለት ነው። ከሞቱ ቡሃላም ይሁን ከትንሳኤውም ቡሃላ በተዋህዶ እንዳለ ማስረጃችን መፅሀፍ ነው፦
(የዮሐንስ ወንጌል ምዕ. 21)
3፤ ስምዖን ጴጥሮስ። ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ አላቸው። እነርሱም። እኛም ከአንተ ጋር እንመጣለን አሉት። ወጥተውም ወደ ታንኳይቱ ገቡ በዚያችም ሌሊት ምንም እላጠመዱም። 4፤ በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም።
5፤ ኢየሱስም። ልጆች ሆይ፥ አንዳች የሚበላ አላችሁን? አላቸው። የለንም ብለው መለሱለት። 6፤ እርሱም። መረቡን በታንኳይቱ በስተ ቀኝ ጣሉት ታገኙማላችሁ አላቸው። ስለዚህ ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ ሊጐትቱት አቃታቸው።
➞ያለመቀላቀል
ይህም ወተትና ቡና ሲቀላቀሉ ሌላ ሦስተኛ መልክ ያለው ነገር እንደሚሰጡት ሳይሆን መለኮትና ትስብዕት የተዋሐዱት በመጠባበቅ (በተዐቅቦ) ነው፡፡
➞ያለማደር
የመለኮትና የትስብዕት ተዋሕዶ ያለማደር (ዘእንበለ ኅድረት) ነው፡፡ ሰይፍ በሰገባው፣ ዳዊትም በማኅደሩ እንደሚያድር መለኮትም በሥጋ ላይ አደረበት የሚል የንስጥሮስ ክህደት በተዋሕዶ ዘንድ የተወገዘ ነው፡፡
➞ያለመደራረብ
የመለኮትና የትስብዕት ተዋሕዶ ልብስ በልብስ ላይ እንደሚደረበው ወይም እንጀራ በእንጀራ ላይ እንዲሚደራረበው ሳይሆን ያለመደራረብ ነው፡፡
➞ያለመለያየት
የተዋሕዶ ምስጢር ሥጋና ነፍስ ተዋሕደው ኖረው በሞት ሰዓት እንደሚለያዩትም ሳይሆን ያለመለያየት ነው፡፡ ስለዚህም ነገር ሊቁ ቅዱስ አዮክንድዮስ “ሥጋ በሠራው ሥራ ሁሉ መለኮት አንዲት ሰዓት ስንኳን በማናቸውም ሥራ ከእርሱ እንዳልተለየ እናምናለን፤ ጌታችን መድኃኒታችን ሰው በሆነ ጊዜ መለኮቱን ከሥጋ ጋር በተዋሕዶ አንድ እንደ አደረገ እናምናለን፡፡ መለኮትም ከትስብእት ጋር ከተዋሐደ በኋላ ከሥራ በማናቸውም ሥራ አንድነታቸው ፈጽሞ አልተለየም፤ መለየት የለባቸውምና፤ ለመለኮት ጥንት እንደሌለው ከትንሣኤው በኋላ ለትስብእትም እንዲሁ ፍጻሜ የለውም፡፡” በማለት ተናግሯል፡፡ )ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አዮክንድዮስ 44፡4-5)
እንደተመለከትንው ተዋሕዶ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የመሆን ምስጢር ነው፡፡
🏁...በዚህም አስተምህሮ የጥንት አባቶችን(Early church father) ያስተማሩትን ከሃይማኖተ አበው ቀንጨብ አድርገን ጠቅሰን እንመለከት፦
ቅዱስ ቴዎዶስዮስ፦
“ከተዋሕዶ በኋላስ ሁለት ባሕርይ አንልም፤ እንደ ንጹሐን አባቶቻችን ክርስቶስ (መለኮትና ትስብእት) በአንድ አካል ሁለተኛ የሌለው አንድ እንደሆነ እንናገራለን እንጂ፡፡” ➞ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎዶስዮስ 82፡37)
ቅዱስ ቄርሎስም፦
“የሥጋ ገንዘብ ለቃል የቃል ገንዘብ ለሥጋ ሆነ”
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
"...ነፍስን ስጋን ተዋህዶ ሰው የሆነ እግዚአብሔር ቃል አንድ አካል አንድ ባህርይ እንደሆነ እንናገራለን...ነገር ግን እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ አንድ እንደሆነ ብንናገርም ወዲህም ከእኛ ባህርይ የተገኘ ስጋ ያለመለየት በማይመረመር ተዋህዶ ከቃል ጋር አንድ መሆኑን እኛ እናውቃለን ስጋ የመለኮትን ባህርይ እንዳልለወጠ መለኮትም እንዲሁ የስጋ ባህርይ አልለወጠም እርሱ ሰው የሆነ አምላክ ነው።
➞ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ምዕ. 67 ቁ. 30
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ፦
“ሁሉን የፈጠረ ነው፤ ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ፤ ሰውም ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከተወለደ በኋላ እግዚአብሔር ቃል ነውና እርሱ መቸም መች አንድ ነው፤ የመለኮቱ ባሕርይ ወደ ሰውነቱ ባሕርይ አልተለወጠም፤ የሰውነቱ ባሕርይም ወደ መለኮቱ ባሕርይ አልተለወጠም፤ ደንግል ማርያም አንድ አካል ሆኖ ወለደችው እንጂ፤ ሰብአ ሰገልም አንድ ባሕርይ ሁኖ ሰገዱለት እንጂ፡፡” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ 60፡17)
በማለት አንድ አካል አንድ ባህርይ መሆኑን አስተምረዋል ማለት ነው።
ስለዚህ ቃል ስጋ የሆነበት ምስጢር ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ ሲሆን ይህም ተዋህዶ ይባላል። ነገር ግን በካቶሊካውያን እምነት መሰረት አምላክ ሰው ከሆነ ቡሃላ አንድ አካል ሁለት ባህርይ ይላሉ ። ይህም መፅሀፍ ቅዱሳዊ መሰረት የሌለው ትምህርት ባህርያተ መለኮት እና ባህርያተ ስጋ በተዋህዶ አንድ አይደሉም፤ አምላክ ስጋ ከሆነ ቡሃላ የሚሰራቸው ስራዎች ይህ የመለኮት ይህ የስጋ እየተባለ የሚከፈል ነው ይህ ምንፍቅና የተነሳው በፖፕ ሊዮን በ4ኛው ክፍለ ዘመን ነው እንጅ ከላይ ባየንው ለሀዋርያት ቅርብ በነበሩት አባቶች እንዲሁም በመፅሀፍ ቅዱስ ድጋፍ የለውም።
🏁... ከተዋህዶ በኋላም አንድ አካል አንድ ባህርይ ለመሆኑ የመፅሀፍ ቅዱስ ማስረጃዎች አሉን፦
1➞"... በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።
"...ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው። "✅(ትንቢተ ዳንኤል 7:13-14)
የሰው ልጅ የተባለው እግዚአብሔር ወልድ ሲሆን ግዛቱም ዘለአለማዊ ነው። ነገር ግን ዘለአለማዊ ግዛት ለአምላክ ሆኖ ሳለ የሰው ልጅ መባሉ አንድ አካል አንድ ባህርይ ከተዋህዶ ቡሃላ መሆኑን ያመለክተና።
2➞"... በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።"(የሐዋርያት ሥራ 20:28)
እግዚአብሔር ረቂቅ መንፈስ ነው ደም የለውም ነገር ግን መለኮት በተዋሃደው ስጋ ደም ስላለው ቤተ ክርስቲያንን #እግዚአብሔር_በደሙ_ዋጅቷቷል።
(ሁለት ባህርይ ቢሆን ኖሮ በደሙ ዋጃት የሚባለው መለኮት ሳይሆን ስጋ ነበረ ነገር ግን አንድ አካል አንድ ባህርይ ስለሆነ መለኮት የስጋን ያለመቀላቀል ገንዘቡ ስላደረገ የእግዚአብሔር ደም ሊለው ችሏል)
3➞"... ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ።"(የዮሐንስ ራእይ 1:18)"... ሞቶ የነበረው ሕያውም የሆነው ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል።"(የዮሐንስ ራእይ 2:8)
ቅድመ ዓለም የነበረው እግዚአብሔር እንደሆነ የታወቀ የእግዚአብሔር አኗኗር ዘለዓለማዊ፤ ከ-ዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ያለ ነው። ይህም አምላክ በራዕየ ዮሐንስ ላይ ሞቼ ነበርሁ፣ ሞቶ የነበረው ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ያለሁት እያለ ይናገራል። ስለዚህ ዘለዓለማዊ አምላክ ሞቻለሁኝ ተነስቻለሁም ካለን መለኮት በተዋሐዳው ሰውነት መሞቱ ልብ እንላለን።
4➞"... ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር።"(የዮሐንስ ወንጌል 5:18)
ማነው እራሱን ከአብ ጋር ያስተካከለ? ኢየሱስ ክርስቶስ በአይናችን አይተን የምንዳስሰው ኢየሱስ እግዚአብሔር አባቴ ነው ብሏል፤ አባቱም ልጄ ነው ብሏል(ማቴ. 3:16)
ከድንግል የተወለደውን ኢየሱስ አብ ልጄ ነው አለንጅ በእርሱ ውስጥ ያለው ቃል ልጄ አላለም፤ ነገር ግን አብ ስጋና መለኮትን በተዋህዶ አንድ አድርጎ አዋህዶ የምወደው ልጄ ብሎ መሰከረ።
5-"... ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ ሲያገኘውም። አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?አለው። 36፤ እርሱም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? አለ። 37፤ ኢየሱስም። አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው አለው።
38፤ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ አለ፤ ሰገደለትም።
➞(የዮሐንስ ወንጌል 9)
እዚህ ጋር ጌታ ባነጋገሩ አንድ አካል አንድ ባህሪ መሆኑን እንመለከታለን። ይህም በጌታ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ልጅ እንዲያምን እና በፊቱ ያለው የሚያየው የሚዳስሰው እንደሆነ ይመልስለታል፤ እንጅ በእኔ ውስጥ ያለው መለኮት የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብሎ አልመለሰለትም። ስለዚህ ስጋ በተዋሃደው መለኮት(ቃል) የእግዚአብሔር ልጅ ነው እንጅ መለኮቱ ብቻ የእግዚአብሔር ልጅ የሚባል ሂሳብ የለም።
6-"...የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።"
(የማቴዎስ ወንጌል 12:8)
የሰው ልጅ የተባለው ማነው ስንል ስጋን የተዋሃደው እግዚአብሔር ወልድ ነው። ይህንም የምናውቀው የሰንበት ጌታ በመሆኑ ነው። ሰንበትን ለእራሱ ፈጥሮ ሊከብርባት ጌታ ሊሆንባት ያዘጋጃት እግዚአብሔር ነው። ይህ የሰንበት ጌታም የሰው ልጅ ተብሏል። አንድ አካል አንድ ባህርይ ባይሆን ኖሮ ስጋ በተዋሃደው መለኮትነትን ገንዘቡ ባያደርግ ኖሮ የእግዚአብሔር ልጅ የሰንበት ጌታዋ ነው ወይም ቃል የሰንበት ጌታዋ ነው ባለን ነበረ። ነገር ግን ትስብእት የመለኮትን ባህርይ ገንዘቡ ስላደረገ ትስብእት በተዋሃደችው መለኮት የጌቶች ጌታ ናት።
~~~
ለአብነት ይህንን ጠቀስን እንጅ ሁሉንም የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ንግግር ብንመለከት ቃል ስጋ ከሆነ ቡሃላ አንድ አካል አንድ ባህርይ መሆኑን ይነግረናል።
በቀጣይ ፅሁፋችን ደግሞ የሙስሊሞችን ጥያቄ ለመመለስ እንሞክራለን!(እግዚአብሔር ለምን ሰው አይደለሁም አለ?) ➞ትንቢተ ሆሴዕ11:9
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ወለወላዲቱ ድንግል!
ወለመስቀሉ ክቡር!
ይቆየን!
01/10/2012 ተጻፈ
Comments
Post a Comment