ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም

        አንድ አምላክ በሚሆን በአብ ፡ በወልድ ፡ በመንፈስ ቅዱስ ስም!


     የክርስቶስን ስቅለት የሚክዱ ተቃዋሚዎች ተቃውሟቸውን ለማጠናከር በማሰብ ከሚጠቅሷቸው የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ የኢየሱስ ንግግር የሆነው " ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝም" የሚለው ይገኝበታል። ጥቅሱ እንደዚህ ይነበባል፦


      ዮሐንስ 7

¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

³³ ኢየሱስም፦ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ ወደ ላከኝም እሄዳለሁ።³⁴ ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አለ።

     ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነውን ደግሞ 👇

    “ኢየሱስም ደግሞ፦ እኔ እሄዳለሁ ትፈልጉኛላችሁም በኃጢአታችሁም ትሞታላችሁ እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አላቸው።”— ዮሐንስ 8፥21

   ሙስሊሞች እኒህንና እና ከእነዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን ጥቅሶች በመጥቀስ የኢየሱስን ስቅለት ለማስተባበል ይሞክራሉ። ይህን ሙግታቸውን አስገራሚ የሚያደርገው ግን ሙሉ ወንጌሉ ይቅርና በምዕራፉ ለራሱ ኢየሱስ እንደሚሰቀል የሚናገር መሆኑ ነው።  እንደሚሰቀል በሚናገርበት ምዕራፍ አልሰቀልም ስለማለቱ ማስረጃ መፈለግ ቂልነት ነው።

    ኢየሱስ እንደሚሰቀል እንዲህ ነግሯቸዋል፦

    “ስለዚህም ኢየሱስ፦👉 #የሰውን_ልጅ_ከፍ_ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ እኔ እሆን ዘንድ አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ።”— ዮሐንስ 8፥28

    ይሄ ንግግር እነርሱ ከሚጠቅሱት ጥቅስ ትንሽ ወረድ ብሎ የተነገረ ሲሆን ኢየሱስ በራሱ አንደበት እንደሚሰቀል የተናገረበት ቦታ ነው።

    ኢየሱስ እንደሚሰቀል ከተናገረ " ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝም" ሲል ምን ማለቱ ነው? የሚለውን እንይ፦

     በመጀመሪያ ይሄ ንግግር ከዕርገቱ ብኋላ ስላለው ጊዜ የሚያመለክት እንጂ አይሰቀልም የሚል እሳቤ ፈፅሞ የለውም። ምክንያቱም ኢየሱስን በአትክልት ስፍራው አይሁዶች አግኝተውታል።

       ኢየሱስ የሚሄደው ወዴት ነው? የሚለውን ማወቅ ወሳኝ ነገር ነው። ኢየሱስ አመጣጡ ከላይ የሆነ ሰማያዊ ነው የሚሄደውም ይኖርበት ወደነበረው ወደ ሰማይ ወደ አብ ቀኝ ነው። በመፅሀፍ ሰፍሮ እንደምናገኘው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ያረገው ፡ በአብ ቀኝ የተቀመጠው ደግሞ ከስቅለቱ እና ከትንሳኤው በኋላ በዕርገቱ  ነው። ከዕርገቱ ብኋላ አይሁዶች ቢፈልጉትም አያገኙትም እርሱም ወዳለበት ሊሄዱ አይችሉም ለምን? ምክንያቱም በኃጢአታቸው ስለሚሞቱ ነው።

    አይሁዳውያን ኢየሱስን በሚገባ አላወቁትም ። ከመጀመሪያው ለአባቶቻቸው የተናገረው እርሱ መሆኑና መሲህ መሆኑን አላወቁም። ስለዚህም ኢየሱስ ይህንን ብሏቸዋል፦ 👇

   

      ዮሐንስ 8

"..²⁴ እንግዲህ፦ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤👉 #እኔ #እንደሆንሁ #ባታምኑ #በኃጢአታችሁ #ትሞታላችሁና አላቸው።²⁵ እንግዲህ፦ አንተ ማን ነህ? አሉት። ኢየሱስም፦👉 #ከመጀመሪያ #ለእናንተ #የተናገርሁት #ነኝ።

   እነርሱም ይህንን ባለማወቃቸው በኃጢአታቸው ይሞታሉ።  በኃጢአት የሚሞት ሰው ደግሞ ከጌታ ጋር በአንድነት ሊኖር አይችልም ከዛ ይልቅ የሚገባው ወደተዘጋጀለት ወደ ገሃነም እሳት ነው።

     “በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል፦ እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ።”— ማቴዎስ 25፥41

    እኒህ በኃጢአታቸው የሞቱ የሚገቡት ወደገሃነም እሳት ከሆነ ጌታ ወዳለበት ሊሄዱ አይችሉም ማለት ነው።

   እስኪ ደግሞ የሙስሊሞቹን ሙግት አቅመ ቢስነት የሚያመለክት ተመሳሳይ ጥቅስ እንጥቀስ፦

     ዮሐንስ 13

³³ ልጆች ሆይ፥ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤👉 ለአይሁድም፦ እኔ #ወደምሄድበት #እናንተ #ልትመጡ #አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፥ አሁን👉 ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ።

   እዚች ጋር ለሙስሊም ወገኖቻችን ጥያቄ እናስቀምጥ ፦ ኢየሱስ " እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አይቻላችሁም" ማለቱ አይሁዶች ሊሰቅሉት ፈልገው እንደማያገኙት እየተናገረ ነው ካልን ሐዋርያትም ኢየሱስን ለመስቀል ይፈልጉት ነበርን❓🤔 ምክንያቱም ለአይሁዶች ያላቸውን መልሶ ለሐዋርያቱም ብሏቸዋልና ነው።  ይሄ ግን የለየለት ክህደት ነው። ይህ እንግዲህ የሙስሊሞች አመክንዮ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ ያሳየናል።

     የጥቅሱን አፈታት ግን ከላይ ባልነው መሰረት ካስኬድነው ክህደቱ የሚወገድ ይሆናል።

     ኢየሱስ ከስቅለቱ እስከ ከትንሳኤው ሐዋርያቱ እንደማያዩት ፤ ከትንሳኤው እስከ ዕርገቱ ጥቂት ጊዜ ከሐዋርያቱ ጋር እንደሚሆን ፤ ከዛ ብኋላ ወደ አብ እንደሚሄድና እንደማያዩት ነግሯቸዋል ፦

     “ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁም፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና።” — ዮሐንስ 16፥16

     እንግዲህ ወደ አብ ከሄደ ብኋላ በስጋ ቢፈልጉትም አያገኙትም። ግን ሐዋርያት እርሱ ወዳለበት ሊሄዱ ይችላሉ ምክንያቱም እነርሱ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ፡ መሲህ መሆኑን አውቀዋል።

      “ስምዖን ጴጥሮስም፦ ጌታ ሆይ፥ ወዴት ትሄዳለህ? አለው። ኢየሱስም፦ ወደምሄድበት👉 #አሁን ልትከተለኝ አትችልም፥ ነገር ግን በኋላ ትከተለኛለህ ብሎ መለሰለት።”— ዮሐንስ 13፥36

    ይሄ አይሁዶችን ከሐዋርያት ይለያቸዋል። አይሁዶች ኢየሱስን ሳያውቁ በኃጢአታቸው በመምታቸው ኢየሱስ ወዳለበት መሄድ የማይችሉ ሲሆን ሐዋርያት ግን ኢየሱስ ወዳለበት መሄድ ይችላሉ።

    ስናጠቃልል ኢየሱስ "ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም " ማለቱ አለመሰቀሉን የሚያሳይ ሳይሆን በተቃራኒው ከተሰቀለ ፤ ከሙታን ከተነሳ እና ካረገ በኋላ ስላለው ሁኔታ የሚገልፅ ነው።

       ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

______________✝
       ለማንኛውም አስተያየት፦
[ ዐቃቢያነ እምነት ዘኦርቶዶክስ ]

ለቴሌግራም ቻናላችን፦
[ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ]
     

Comments

Popular posts from this blog

ዕቅበተ እምነት

ወላዲተ አምላክ

መልስ ለወሒድ ዑመር