የመሲሁ አምላክነት በብሉይ ኪዳን ትንቢት ክ. ፬
ሰው ስለሆነው አምላክ!
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን
የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት በብሉይ ኪዳን ትንቢት!
"... እግዚአብሔር ጌታዬን። ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።"➞(መዝሙረ ዳዊት 110:1)
110ኛው የዳዊት መዝሙር ሁሉም በሚባል ሁኔታ የሚናገረው ስለ መሲሁ ነው። ስለመሲሁ ጌትነት፣መሲሁ አስቀድሞ በመለኮታዊ አካልነት ሳለ ቅድመ ዓለም ስለመወለዱ፣ ስለመሲሁ ሊቀ ካህንነት፣ የተነገረበት የመዝሙሩ ክፍል ነው። እንደመርሃግብራችንም ርዕስ ዛሬ ልናየው የወደድንውም ስለ አምላክነቱ የሚገልጸውን ክፍል ከመናፍቃን የሚነሱበትን ጥያቄ መመለስ ይሆናል።
❓ በመጀመሪያ ተቃዋሚዎች የሚያነሱት ጥያቄ *የዚህ የመዝሙር ጸሀፊ ነብዩ ዳዊት አይደለም* የሚል ነው።
መልስ፦
በመሰረቱ ይህ ሙግት ምንም አይነት ማስረጃ የሌለው ነው። ዳዊት የጻፈው መሆኑን የምናውቀው በመግቢያው ላይ *የዳዊት መዝሙር* በማለት ስለሚጅምር ነው። በዚህ ሀረግም የሚጀምር የመዝሙር ክፍል ሁሉ የዳዊት መዝሙር መሆኑን እንረዳለን ማለት ነው። የተቃዋሚዎቻችንም ሙግት በዚህ ይፈርሳል ማለት ነው።
ሁለተኛ ጥያቄ፦
❓*ዳዊት ዘመረው ብንልንኳን ጌታዬ ያለው ወይ መላዕክትን ወይም ልጁን ሊሆን ይችላል*
መልስ፦
ይህም ሙግት ፈጽሞ የተሳሳተ ነው። በመጀመሪያ
ለመላዕክት እንዳልሆነ የቅዱሳት መጻህፍት ምስክርነት ማየት በቂ ነው፦
"...ከመላእክትስ። አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም። እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል. . .ይላል። ነገር ግን ከመላእክት። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ከቶ ለማን ብሎአል?"➞(ወደ ዕብራውያን ምዕ. 1:5፣13)
ስለዚህም እግዚአብሔር በመዝሙር 110 ላይ ከአንድ ልጁ በስተቀር ለመላዕክት ይህን ቃል አልተናገረውም። ለመላዕክት የሚለው ሙግትም እዚሁ ይፈርሳል።
ሁለተኛ ደግሞ ነብዩ ዳዊት ይህን ትንቢት የተናገረው ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ወደ ምድር ሳይመጣና በስጋ ሳይወለድ ነው። እዚህ ላይ የምናስተውለው ነገር ንጉስ ዳዊት ትንቢቱን ሲናገር ያ አካል ጌታው ነበረ ማለት ነው። ዳዊትም ጌታዬ አለእንጅ ጌታዬ የሚሆነው አላለውም ጌታዬ የነበረውም አላለም። ሁለተኛ ደግሞ በመዝሙረ ዳዊት ሌሎች ክፍሎች ስንመለከት ንጉስ ዳዊት ጌታዬ ብሎ ሊጠራው የሚችለው እግዚአብሔርን ብቻ ነው፦
"... እግዚአብሔርን👈_👉አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ፤ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም።"(መዝሙረ ዳዊት 16:2)
ስለዚህ የዳዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። ምክንያቱም ደግሞ በምድር ከነበሩ ነገስታት ሁሉ ከፍ ያለ ነውና፦
(መዝሙረ ዳዊት ምዕ. 89:20፣27)
"...ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት።. . .እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁ፥ ከምድር ነገሥታትም ከፍ ይላል።
ስለዚም ዳዊት ጌታዬ ብሎ ሊጠራው የሚችለው እግዚአብሔርን ብቻ ነው።
በአዲስ ኪዳንም ጌታችን በመዋዕለ ስጋዌው ወቅት ለአይሁድ ነብዩ ዳዊት በመዝሙሩ ጌታዬ ያለው ማንንም ሳይሆን አምላኩ የሆነውን መሲሁን እራሱን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሆነ ተናግሯል፦
"...ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ።"➞(የማርቆስ ወንጌል 12:36)
ታዲያ ለምን *እግዚአብሔር አለው* ተባለ ቢሉ በስላሴ አስተምህሮ ሶስቱም የስላሴ አካላት እግዚአብሔር እየተባሉ እንደተጠሩ ከዚህ በፊት ተመልክተናል። ስለዚህም ደግሞ በዚህ ክፍል ላይ *እግዚአብሔር* የተባለው *አብ* ነው፤ ይህን የሚያመለክተን ዝቅ ብሎ #ወለድሁህ ስለሚለው ነው፤ ወላዲነት ግብሩ የሆነው አብ ነውና። *እግዚአብሔር አብ* አለው መባሉ ነው።
የሁለተኛውን ጥያቄ መልስ ለማጠቃለል ዳዊት ከእግዚአብሄር በቀር ጌታዬ ብሎ ሊጠራው የሚችለው እንደሌለ ተመልክተናል ምክንያቱም ደግሞ እርሱ ከምድር ካሉና ከነበሩ ነገስታት ሁሉ ከፍ ያለ ስለነበረ ነው። በዚህም የመዝሙር ክፍል ጌታዬ ብሎ የዘመረለት ለእግዚአብሔር ወልድ ለኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ሶስተኛ ጥያቄ፦
"በመዝሙሩ ክፍል ኢየሱስ ጌታ ቢባልንኳ ፍጡር ከመሆነ የዘለለ ማንነት አይኖረውም ምክንያቱም ደግሞ ጌትነቱን ለማመልከት የገባው የዕብራይስጥ ቃል adoni ሲሆን የፍጡርን ጌትነት/አለቅነት ለማመልከት የሚገባ ስለሆነ ነው።"
መልስ፦
በመፅሀፍ ቅዱስ ha adon(THE LORD) የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ለእግዚአብሄር ብቻ የሚውል ሲሆን ለፍጡር ውሎ አያውቅም adon(lord) የሚለው ግን ለእግዚአብሔር ጌትነትም ለፍጡራንም አለቅነት ሲውል እንመለከታለን። ብዙ ተቃዋሚዎች ግን adon የሚለው ቃል የእግዚአብሄርን ጌትነት ለማመልከት ፈጽሞ ጥቅም ላይ አልዋለም የሚል ነው። ይህ ሃሳብ ሀሰት ለመሆኑ *adon* የሚለው ቃል ለእግዚአብሄር የዋለበትን እንመልከት፦
1-እግዚአብሔር በመላዕክት አምሳል ተገልጦ አዶን ተብሏል
እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን በሰው አምሳል፣ በመላዕክት አምሳል እንዲሁም በእሳት አምድ እና በመሳሰሉት መገለጡ ይታወቃል። ከእነዚህም ውስጥ በመላዕክት አምሳል ሲገለጥ አዶን ተብሏል። ለምሳሌ፦
(መጽሐፈ መሳፍንት ምዕ. 6:13-16
"ጌዴዎንም፦ ጌታዬ(אֲדֹנִ֔י) ሆይ...
...እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ። በዚህ በጕልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን፤ እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው። እርሱም። ጌታ(adon) ሆይ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ አለው። እግዚአብሔርም። በእርግጥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታለህ አለው።
ለዕብራይስጡ ንባብ፦[ https://biblehub.com/lexicon/judges/6-13.htm ]
ለጌዴዎን *የእግዚአብሔር መልዓክ* ተብሎ የተገለጠለት አለ ሙሉ አውዱን ስንመለከት ይህ የተገለጠለት አካል እግዚአብሔር ተብሏል(ቁ. 16) ይህም በመልዓክ አምሳል የተገለጠው እግዚአብሔር መሆኑን ሲያመለክተን በዚህ ቦታ ላይም በቁ. 13 ላይም ጌታዬ(adoni) ተብሏል። ጌታ የሚለው ቃል አዶን ነው። ይህ የተገለጠው አካል ግን እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ በተዛዋሪ አዶን የሚለው ቃል የእግዚአብሔርን ጌትነት ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል ማለት ነው።
2-አዶን የሚለው ቃል በtheophoric ስሞች ላይ የያህዌን ጌትነት ለመግለጽ ውሏል፦
Theophoric ማለት በስነ መለኮት አፈታት የአምላክ ስም ከአንድ ሃሳብ ጋር ተጫፍሮ መጥቶ አንድ ሰው ሊጠራበት የሚችል ስም ነው፦
A theophoric name (from Greek: θεόφορος, theophoros, literally "bearing or carrying a god") embeds the name of a god, both invoking and displaying the protection of that deity.[ https://en.m.wikipedia.org/wiki/Theophoric_name ]
ይህን መሰረት በማድረግ በtheophoric ስሞች ላይ እግዚአብሔር አዶን የተባለበትን ነው። ብዙ ማሳያ ቢኖርም የምንመለከተው የአንድ ሰው ስም ነው። እርሱም አዶንያስ ይባላል። በዕብራይስጥ ንባብ ደግሞ አዶኒያህ፦
"...ከእነርሱም ጋር ሌዋውያንን #አዶንያስን... ሰደደ።"
(መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 17:8)
ከዚህ በላይ የተመለከታችሁት የእግዚአብሔር ሰው ስም አዶንያስ በዕብራይስጥ ንባብ አዶኒያህ ይባላል። theophoric ከሚባሉ የስም አይነቶች የሚመደብ ሲሆን ይህ ሰው ስለሚያመልከው አምላክ አንድን ጽንሰ ሃሳብ የሚያስተላልፍበት ነው። እንመልከተው፦
አዶኒያህ(adoniyah)(אֲדֹנִיָּה)የሚለውም ስም የሶስት ቃላት ውቅር ነው። እነርሱም፦
1➞adon (ጌታ) 2➞እንዲሁም አገናዛቢ አጸፋ ተውላጠ ስም የሆነችው ጌታዬ በሚለው ስም ተውጣ ያለችው የዕብራይስጧ (ዮድ) 3➞እንዲሁም ከስሞች ጋር ተጫፍሮ የሚመጣው የአምላክ ስም yah የሚሉት ናቸው።
ትርጉሙም "ጌታዬ ያህዌህ ነው" ማለት ነው። እንግዲህ አንባቢ ልብ የምትሉት ያህዌህ በዚህ ቦታ አዶን ተብሎ መጠራቱን ነው። ምክንያቱም አዶንያስ የተባለው ሰው የሚያመልከው እውነተኛውን አምላክ ያህዌህ ነውና። በዳዊትም ስንመጣ እርሱ ጌታዬ ብሎ ሊጠራው የሚችለው ከእግዚአብሔር ውጭ ማንም እንደሌለ ካወቅን ዳዊት በመዝሙሩ መሲሁን ጌታዬ እግዚአብሔር ብሎ እንደጠራው እናስተውላለን።
ማጠቃለያ፦ መዝሙረኛው ዳዊት በዚህ የመዝሙር ክፍሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት እና እግዚአብሔር በአካል ከአንድ በላይ መሆኑን አስተምሮናል። እውነት ነው ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው።
በቀጣይ ክፍል ሌሎች በአዲስ ኪዳን ያሉ የክርስቶስን አምላክነት የሚገልፁ ምንባባት ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ይዘን እንመጣለን።...ሰላም ለእናንተ ይሁን!
ወስብሀት ለእግዚአብሄር
©✞ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
Comments
Post a Comment