ዕቅበተ እምነት
ዕቅበተ እምነት
ዕቅበተ ማለት ቃሉ የግዕዝ ሲሆን መጠበቅ፣ ጥበቃ የሚል የአማርኛ ትርጉም አለው።(ኪዳነወልድ ክፍሌ መፅሀፈ ሰዋሰው ወግስ መዝገበ ቃላት ሐዲስ ገፅ.705)እምነት የሚለውም ሃይማኖትን እምነትን ማለት ነው። ዕቅበተ እምነት ማለት የእምነት ጥበቃ ማለት ነው።
ዕቅበተ እምነትን የሚተገብረው ሰውም ዐቃቤ እምነት ይሰኛል። ዐቅበተ እምነትን በህብረት የሚሰሩ ከሆኑም ዐቃቢያነ እምነት ይሰኛሉ።
.
እምነትየሚጠበቀውም ከሃሳውያን መምህራን ከሃሳውያን የፍልስፍና አራማጆች ወደ ቤተ ክርስቲያን የሀሰት ትምህርትን ሲያስገቡ መካለከልና ለእነሱም መልስን መስጠት ነው።
በመፅሀፍ ቅዱሳችን አንድ ታሪክ አለ እርሱም በሐውርያት ስራ ምዕራፍ 17 ላይ የሚገኝ ነው። ብርሃነ አለም ቅዱስ ጳውሎስ ከአይሁድ ጋር ወይይቶችን ያደርግ ነበረ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስም መሲህነት ስለ ሀጢያታችን በቀራኒዮ መሰቀል ሞቶም ስለመነሳቱ ህያው አምላክ ለመሆኑም ይመስክር ነበረ። ምክንያቱም በዚያ ዘመን አይሁዶች ብዙ ክርስትናን ለማፈራረስ ይጥሩ ስለነበረ ነው፤ እርሱ ግን ብሉያትን እያጣቀሰ ይመልስላቸው ነበረ።
፧
የዐቅበተ እምነት ታሪኮች በታላላቅ ጉባኤያት
➫የኒቅያ ጉባኤ፦ ይህ ጉባኤ የተካሄደው በ318 ዓመተ ምህረት ወልድን ፍጡር ነው ብሎ የስህተት ትምህርት ያሰራጨውን አርዮስን በመፅሀፍ ቅዱስ መሰረት መልስ የተሰጠበትና፤ ከጉባኤያትም ሁሉ የላቀ ነው በጉባኤውም 318 የበቁ የነቁ የሃዋርያትን ፈለግ በተከተሉ ቅዱሳን አባቶች የእምነት ጠበቆች የተገኙበት ነው። ከእነሱም ልቆ የነበረው ዐቃቤ እምነትም በእለቱ ሊቀ ዲያቆን የነበረው ቅዱስ አትናቴዎስ ነበር።
➫የቁስጥንጥንያ ጉባኤ፦ ይህ ጉባኤ የተካሄደው በ381 ዓም በ150 ኤጲስቆጶሳት የተካሄደ ሲሆን ለዚህ ጉባኤ መካሄድ በዋናነት
➾መንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ ነው(ፍጡርነው)ያለውን የመቅዶንዮስ የሀሰት ትምህርት
➾ቃለ እግዚአብሔር የተዋሃደው ስጋን እንጅ ነፍስን አይደልም ላለው ለአቡሊናሪዮስ
➾እንዲሁም ቃለ እግዚአብሔር የተዋሃደው የአዳምን ስጋ ሳይሆን፤ ሌላ በቅድምና የነበረን ስጋ ነው ለሚሉ መናፍቃን ነበረ። ለእነዚህም መናፍቃን ተገቢውን መልስ በመስጠት ክርስትና ሃይማኖትን ከዚህ አድርሰውልናል በዚህም ጉባኤ አንድ ታላቅ ዐቃቤ እምነት ተነስቷል እሱም ጎርጎርዮስ ዘኢንዙናዚ(ነባቤመለኮት)
➫የኤፌሶንጉባኤ፦ በዚህ ጉባኤ በሊቀ ጳጳሱ በንስጥሮስ ይስፋፋ የነበረውን የሁለት አካል ትምህርት ነበረ ይህም የአብ ልጅና የማርያም ልጅ የተለያዩ ሁለት አካላት ናቸው፣ ድንግል ማርያም እመ አምላክ አትባልም እርሷ የወለደችው ዕሩቅ ብዕሲ ነው ቡሃላም በጥምቀት ቃል አደረበት"" በማለት በስልጣኑ ተመክቶ ይህን የስህተት ትምህርቱን ሲያስፋፋ 200 የሚሆኑ ደጋግ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጉባኤን በ431 ዓም አሰናዱ ይህንም የስህተት ትምህርቱን መፅሀፍ ቅዱስን መሰረት አድርገው ውድቅ አደረጉት!
በዚህጉባኤም ለክህደታቸው መልስ በመስጠት ቅዱስ ቄርሎስ የላቀውን ድርሻ ይይዛል።
፧
እንግዲህ የሃይማኖት ጥበቃ ከጥንት ከሃዋርያት ጀምሮ በሊቃውንት አልፎ ከዚህ ካለንበት ዘመን የደረሰ ነው። በዘመናችንም ለቁጥር የሚያታክቱ ከእውነተኛው ወንጌል ከእውነተኛውም የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የወጡ ትምህርቶች ይደመጣሉ። እነሆ እኛም ልክ እንደአባቶቻችን ብራናን ፍቀን ቀለም በጥብጠን ብዕር ቀርፀን ጉባኤን ሰርተን ለሃሳውያን መልስ ለመስጠት የእነሱን ያህል ፀጋው ባይኖረንም እንደ አቅማችን በዚሁ በማህበራዊ ሚዲያ መልስ ለመስጠት እነሆ ጀምረናል።
መልካም የአብሮነት ጊዜ!
.
በእናንተስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።
1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3 :15 እንደሚለን!
.
መልካም ንባብ!
ዕቅበተእምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ
Comments
Post a Comment