መልስ ለወሒድ ዑመር

 መልስ ለወሒድ ዑመር


ሃይማኖተ አበው ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጡር ነው ይላልን?

     ወሒድ ዑመር ሃይማኖተ አበው  የተባለው የቤተክርስቲያን መጽሐፍ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጡር ነው ይላል ብሎ ትልቅ የቅጥፈት ፅሁፍ ፅፎ አስነብቦናል። ሃይማኖተ አበው የተባለው መጽሐፍ በይበልጥ ምሥጢረ ሥላሴን እና ምሥጥረ ሥጋዌን (ነገረ-ክርስቶስን) የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ ቀደምት የቤተክርስቲያን አባቶች( Early Church Fathers) ለመናፍቃን እና ለከሃድያን የሰጡትን ምላሾች እና ተግሳጾችን አሰባስቦ የያዘ ነው። እስቲ የወሒድ የስህተት ሀሳቦችን እንመልከት!


=>>>ወሒድ

"የተፈጠረ ነገር ሁሉ ላይወለድ ይችላል፥ ለምሳሌ መላእክት ተፈጥረዋል ግን አልተወለዱም። ግን የተወለደ ነገር ሁሉ ከመወለዱ በፊት በማኅጸን ይፈጠራል። ኢየሱስ ማርያም ማህፀን ውስጥ መፈጠሩን በተለይ የክርስትና የዐቂዳህ መጽሐፍ የሆነው ሃይማኖተ-አበው ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት በማህጸን ውስጥ የተፈጠረ “ፍጡር” ነው ይላል፦"

=>>>ምላሽ

ወሒድ "የተወለደ ሁሉ አስቀድሞ በማህጸን ይፈጠራል" በማለት የኢየሱስ ሕልውና የጀመረው በድንግል ማርያም ማህጸን ውስጥ እንደሆነ አድርጎ ያስቀምጣል። ኢየሱስ በማህጸን ተፈጠረ የሚለው የወሒድ ሀሳብ የኢየሱስ ሕልውና በማህጸን የተጀመረ እንደሆነ የሚናገር ነው። መክንያቱም መፈጠር ማለት ካለ መኖር ወደ መኖር መምጣት ነው።ከዚያም ከሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ማስረጃ ብሎ የተወሰኑ ጥቅሶችን ጠቅሷል። ወሒድ ከሃይማኖተ አበው እራሱ ሲጠቅስ በትክክል አይጠቅስም። ለምን እንደዚህ እንዳልኩ ከታች እንመለከተዋለን። ወሒድ ወደ ጠቀሳቸው ጥቅሶች ከማለፋችን በፊት እሱ እራሱ የጠቀሳቸው አባቶች ውስጥ ስለ ኢየሱስ ቅድመ ህልውና(ከማህጸን በፊት ስለመኖሩ) የተናገሯቸውን እንይ!

1. ወሒድ መጠሊጎን ጠቀሰው ብሎ ከሃይማኖተ አበው ምእራፍ 44÷3 ጠቅሷል። ነገር ግን ሃይማኖተ አበው ምእራፍ 44÷3 ሃይማኖተ አበው ዘመጠሊጎን ሳይሆን ዘአዮክንድዮስ ነው።  አዮክንድዮስ የተናገረውን መጠሊጎን ተናገረ ብሎ የተሳሳተ መረጃ ሰጥቷል። ስህተቱ እንዳለ ሆኖ እሱ ከጠቀሰበት ምእራፍ 44 አዮክንድዮስ ኢየሱስ ከማህጸነ ማርያም በፊት ህልውና እንደ ነበረው የተናገረውን እንይ!

"የእግዚአብሔር ቃል ከሰማይ በወረደ ጊዜ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ማህጸን በአደረ ጊዜ..." ሃይማኖተ አበው ዘአዮክንድዮስ 44÷2

በዚህ ጥቅስ ላይ የእግዚአብሔር ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ድንግል ማርያም ማህጸን ከመምጣቱ በፊት በሰማይት እንደኖረ በግልጽ ተቀምጧል።

2. ወሒድ ከቄርሎስ መልክት ጠቅሷል። የጠቀሰው ቄርሎስ የተናገረውን ቢሆንም የጠቀሰው ክፍል ግን ሃይማኖቱ አበው ዘቄርሎስ አይደለም የሚባለው። ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ እራሱን የቻለ ሌላ ክፍል ነው። ምእራፍ 124 ሃይማኖተ አበው ስምዓት ተብሎ ሲጠራ ክፍሉ የተለያዩ ሊቃውንት የተናገሩትን በአንድ ላይ አሰባስቦ የያዘ ክፍል ነው። ወሒድ የመጽሐፉን ክፍል ስም እንኳን በአግባቡ ሳያውቀው ከመጽሐፉ ለመጥቀስ መዳፈሩ ይገርማል። ኢየሱስ ከማህጸነ ማርያም በፊት እንደነበረ የሚናገር ጥቅስ እሱ እራሱ ከጠቀሰው የቅዱስ ቄርሎስ መልእክት ከሚገኝበት ሃይማኖተ አበው ስምዓት እንመልከት።

" እሱ የባህርይ አምላክ እንደሆነ፣ በባህርዩን ፍጥረትን ሁሉ ፈጥሮ መግዛት ገንዘቡ እንደሆነ፣ የተገዥ የአዳምን ባሕርይ ቢነሣም ከፍጥረቱ ሁሉ በላይ እንደሆነ፣ ፍጹም ሰው በሆነ ጊዜም  ከሰው ጋር አንድ እንደሆነ እናምናለን" ሃይማኖተ አበው ስምዓት124÷18


በጥቅሱ በግልጽ እንደ ተቀመጠው ፍጥረታትን ፈጥሮ የሚገዛቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ፍጥረታትን የፈጠረው እሱ ከሆነ ሕልውናው በማህጸነ ማርያም የተጀመረ ነው (በማህጸን የተፈጠረ ነው) የሚለው የወሒድ ቅዠት ነው።


3. ወሒድ በሶስተኛ ደረጃ የጠቀሰው ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎሪዮስን ነው። እስቲ ጎርጎሪያስ ኢየሱስ ክርስቶስ ከማህጸነ ማርያም በፊት በአምላክነት እንደ ነበረ የተናገረበት ጥቅስ እንመልከት።


"ክርስቶስ ማለት ፈጣሪና ፍጡር አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን አንድ ሆነ ማለት ነው። ዓለም ሳይፈጠር የነበረ ለዘላለሙ የሚኖር ያለውን ሁሉ የፈጠረ እርሱ ነውና ስለ እርሱ ስንናገር ያልተፈጠረ ነው እንላለን" ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎሪዮስ 35÷2


=>>>ወሒድ ማስረጃ ይሆኑልኛል ብሎ የተጠቀሳቸው አባቶች በሙሉ በአንድ ላይ ተስማምተው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጣሪነት፣ አለም ሳይፈጠር በመለኮቱ ስለ መኖሩ ይመሰክራሉ። ይህ ከሆነ ወሒድ ማስረጃ ይሆኑልኛል ብሎ የጠቀሳቸው ምንድናቸው? ወደ ሚለው ሀሳብ እንምጣ።


=>>>በመጀመሪያ አንድ መታወቅ ያለበት በሃይማኖተ አበው ውስጥ ኢየሱስ ፍጡር ነው የሚል በፍጹም የለም። ወሒድም እንደዚህ የሚል ማስረጃ አምጥቶ መሞገት ከቻለ ይሞግተን። ወሒድ ሃይማኖተ አበው ኢየሱስ ፍጡር ይላል ለማለት የጠቀሳቸው ጥቅሶች ሲመዘኑ:-


©ወሒድ

1. ሃይማኖተ-አበው ዘመጠሊጎን 44፥3

“እርሱ ሥጋውን በድንግል ማሕፀን ፈጠረ፤ ሥጋውን በመፍጠር ማንም አጋዥ አልሆነውም፤ እርሱ እራሱ ፈጠረው እንጂ”


©ምላሽ

በመሠረቱ ከላይ እንደ ገለጽኩት ይህን ጥቅስ የተናገረው መጠሊጎን ሳይሆን አዮክንድዮስ ነው። ወሒድ ስሙን እንኳን በአግባቡ ሳያጣራ ነው ከመጽሐፉ የጠቀሰው። አንባቢያን ኢየሱስ ፍጡር ነው የሚል ወሒድ በጠቀሰው ላይ አለ? በፍጹም የለም። እንዲያውም የኢየሱስ ፈጣሪነትን ነው የሚናገረው።


"እርሱም ሥጋውን በድንግል ማሕፀን ፈጠረ" ብሎ የሚዋሃደውን ሥጋ አስቀድሞ በድንግል ማርያም ማህጸን እንዳዘጋጀ ይነግረናል። " እርሱም" የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ የምናውቀው ከላይ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እያወራ በመምጣቱ ነው። በተጨማሪም "ሥጋውን" ብሎ ለኢየሱስ ክርስቶስ ባለቤትነት ሰጥቷል። ሥጋን የተዋሃደው ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ወሒድ እራሱ በጠቀሰው ጥቅስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጣሪነት ይመሰክራል።

   

©ወሒድ 


2. ሃይማኖተ-አበው ዘቄርሎስ 124:19

ቄርሎስም አለ፦

“ከሴት በሥጋ ስለተወለደ ፍጡር ነው እንላለን”


©ምላሽ


ቅዱስ ቄርሎስ "በሥጋ ስለተወለደ" ያለውን እናስተውል። ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ የተዋሃደው የፍጡርን ሥጋ ነው። ለዚህም ከተዋህዶ በፊት ስለ ነበረው ሥጋ ሲናገር ፍጡር ነው እንላለን አለ።  በተጨማሪም በሥጋው የሚለው ቃል በመለኮቱ ፍጡርነት እንደ ሌለበት ያሳያል። ወሒድ ጥቅሱን ቆርጦ አቀረበው እንጂ ሙሉ ጥቅሱ እንዲህ ነው የሚለው:-


"ንብሎ ፈጣሪ በእንተ ከመ ውእቱ አምላክ ወእግዚአብሔር፣ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ወዓዲመ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ተወልደ በሥጋ እምብእሲት---አምላክ እግዚአብሔር ስለሆነ ፈጣሪ  እንለዋለን፣ ወዲህም ከድንግል በሥጋ ስለ ተወለደ ሰው(ፍጡረ) እንለዋለን"!  


ወሒድ ፈጣሪ እንለዋለን የሚለውን ቆርጦ አውጥቶ በሥጋ ከድንግል ስለ ተወለደ እና የፍጡርን ስጋ ስለ ተዋሃደ " ንብሎ ፍጡረ" የሚውን ብቻ ወስዶ ለማወዛገብ ይሞክራል። ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ብሎ ለሚያምን ይህ ሀሳብ ግልጽ ነው።


©ወሒድ


3. ሃይማኖተ-አበው ዘጎርጎርዮስ 35:6

ጎርጎርዮስም አለ፦ “ስጋ ስለሆነ ፍጡር ይባላል”


©ምላሽ 

ወሒድ ጥቅሶችን በመቆራረጥ ለራሱ ሀሳብ ለማመቻቸት እየጣረ ነው። ሙሉ ጥቅሱ እንዲህ የሚል ነው።


"ዳግመኛም ባህሪያችንን ተዋሕዶ ሰው ስለሆነ (ዘኮነ ሥጋ ወኀደረ ላእሌነ) ሰው (ፍጡረ) ይባላል። እርሱ ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በሥጋ እንደ ታየ በሥራው ጌትነቱን ገለ


ጠ፣ እርሱ አምላክ ወልድ ወሕድ በአባቱ ዕሪና ያለ ነው።" 


እንግዲህ በጥቅሱ እንደ ተገለጸው ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠ እግዚአብሔር ነው። ነገር ግን የተፈጠረ ባህሪያችንን ተዋህዶ ሰው ስለሆነ ስለ ተዋሐደው ሥጋ ሲናገር (ከተዋህዶ በፊት ስለ ነበረው ሥጋ ሲናገር) ፍጡር ይባላል አለ። መክንያቱም የተዋሐደው የእኛ ባህርይ ፍጡር ነውና። ይህ ማለት ግን ከተዋሐዶ በኃላ በሥጋው ፍጡር ነው ማለት አይደለም። እርሱ ጥንት የሌለው ፈጣሪ ሲሆን የተዋሐደው ሥጋ ግን ጥንት መገኛ ያለው ፍጡር ነው።


"በተገዥ የአዳም ባሕርይም በሥጋ የሰውነትን ሥራ ሠራ፣ጥንት የሌለው እርሱ ያለ መለወጥ ንጽህት ከምትሆን ከቅድስት ድንግል ማርያም የነሣውን ጥንት መገኛ ያለውን የሥጋን ባህርይ በተለየ አካሉ ተዋሐደ" ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎሪዮስ35÷12


©ወሒድ


“ፍጡረ” ማለት “ፍጡር” ማለት ነው። አንዱ እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃሉ ከዳዊት ዘር ለእስራኤል መድኃኒትን ኢየሱስን ካለመኖር ወደ መኖር አመጣ፤ ይህም የተስፋ ቃል ኢየሱስ በማህፀን የተፈጠረ ፍጡር መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፦

ሐዋ ሥራ 13፥23 ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም *ኢየሱስን አመጣ*።

ኢሳይያስ 49፥5-6 ያዕቆብን ወደ እርሱ እንድመልስ እስራኤልንም ወደ እርሱ እንድሰበስብ ባሪያ እሆነው ዘንድ ከማኅፀን ጀምሮ *የሠራኝ* እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡— እርሱም፡— የያዕቆብን ነገዶች እንድታስነሣ ከእስራኤልም የዳኑትን እንድትመልስ ባሪያዬ ትሆን ዘንድ እጅግ ቀላል ነገር ነውና እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኃኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ፥ ይላል።


©ምላሽ


=>>>ከማሕጸነ ማርያም በፊት ህልውና እንደ ነበረው እራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ደጋግሞ ነግሮናል።


" ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ።"

(የዮሐንስ ወንጌል 16:28)


" ኢየሱስም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው።"

(የዮሐንስ ወንጌል 8:58)


=>>>ይህ ከሆነ በማህጸን ሰራኸኝ የሚለው ስለ ምንድነው ከተባለ ስለ ተዋሃደው ሥጋ ነው። በማህጸን ውስጥ የተዋሃደው ሥጋ  በእግዚአብሔር የተፈጠረ ነው። 


" ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ። መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤"

(ወደ ዕብራውያን 10:5)


ይህ በድንግል ማርያም ማህጸን ከእሷ ተወስዶ የተሰራው(የተዘጋጀው) ሥጋ የተፈጠረ ነው። እሱ ያንን የተፈጠረ ሥጋ ስለ ተዋሐደ በማህጸን የሰራከኸኝ አለ። እስቲ ማስረጃ ይሆንልኛል ብሎ የጠቀሰው አባት እንዴት እንደ ተረጎመው እንይ!


©ወሒድ 


1.ሃይማኖተ-አበው ዘቄርሎስ 76:19

ቄርሎስምአለ፦


“ዳግመኛም መድኅን ክርስቶስ ከድንግል ስለመወለዱ በኢሳይያስ አፍ “ብዙ ሥራ እሠራ ዘንድ የያዕቆብንም ወገን አጸና

ዘንድ አስራኤልንም አንድ አደርግ ዘንድ በማሕጸን ተፈጠርኩ አለ”


©ምላሽ


ቅዱስ ቄርሎስ በማህጸን ሰራኝ/ፈጠረኝ የሚለውን እንዴት እንደ ተረጎመው ከእዛው ከቅዱስ ቄርሎስ ንግግር እንመልከት።


"የምትናገር የምታውቅ ነፍስ ያለችው ሥጋን ሊዋሐደው ከድንግል ፈጠረ" ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ 76÷27


"በኃለ የተገኘን ሥጋ ሊዋሐደው ከዳዊት ባሕርይ እርሱ ፈጠረ እንደ ተጻፈ ከሦስቱ አካላት አንዱን አደረገው"  ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ77÷2


=>>>ቅዱስ ቄርሎስ ደጋግሞ እንደ ተናገረው  አካላዊ ቃል የተዋሃደው የተፈጠረን ሥጋን ነው። በመፍጠር ከአባቱ ጋር አንድ ስለሆነ በነቢያት ሥጋን አዘጋጀህልኝ፣ በማህጸን ሰራኝ ያለውን እሱ እራሱ ኢየሱስ የሚዋሐደውን ሥጋ እንደ ፈጠረ ገለጸ። ወሒድም ሆኑ ሌሎች ሙስሊሞች በመለኮትና በሥጋ መካከል ስለተደረገው ተዋሕዶ በሃይማኖተ አበው መጽሐፍ የተገለጸውን ሙሉ ሀሳብ እንዲያዩ ግብዣዬ ነው።


=>>>ማጠቃለያ

ወሒድ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጣሪነት ደጋግሞ ከሚናገረው መጽሐፍ ጠቅሶ መናገሩ እራሱን አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተ ነው። ስለ ተዋሐደው ሥጋ የተነገሩትን ጥቅሶችም አስቀድሞ ከነበረው መለኮታዊ ህልውና ጋር ተምታቶበት ይዳክራል። እባክህን ጥቅስ እየቆራረጥክ አንተም ተወዛግበክ ሰው አታወዛግብ። እግዚአብሔር ልቦናህን ያብራልህ!


©ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶኮስ ተዋህዶ!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር!

Comments

Popular posts from this blog

ዕቅበተ እምነት

ወላዲተ አምላክ