ከአንድ በላይ ጋብቻ ከመፅሀፍ ቅዱስ!
*ከአንድ በላይ ጋብቻ በመፅሀፍ ቅዱስ... *
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ ፡ በወልድ ፡ በመንፈስ ቅዱስ ስም!
እስልምና ሀይማኖትን ከምንተችበት አስተምህሮዎቹ መካከል አንድኛው " አንድ ወንድ አራት ሴት ማግባት ይችላል" የሚለው ነው። ይህን ህሊና ላለው ወንድ እና ይሄ እጣ ለደረሰባቸው ሚስቶች የከበደ ሸክም ቀለል ለማድረግ ሲባል ሙስሊሞች "እከክልኝ ልከክልህ" አይነት ሙግትን ያነሳሉ። ሙስሊሞች" እንደት አንድ ወንድ ለአራት ሴት ይፈቀዳል?" ተብለው ሲጠየቁ " በእናንተስ መፅሀፍ አንድ ለአንድ የተባለው የት ነው? በሙሴ ህግስ ከአንድ በላይ ትዳር ተፈቅዶ የለምን? በመፅሀፍ ቅዱስስ ከአንድ በላይ ያገቡ ሰዎች አሉ አይደለም ወይ?" በማለት የእናንተም ይፈቅዳል ስለዚህ ልክ ነው የሚል ስሁት ሙግት ያቀርባሉ። ይኼንን ሙግታቸውን ከአመክንዮ(logic) አንፃር ካየነው "you too fallacy " በሚል የfallacy ጎራ የሚመደብ ነው። በአለማዊ የ philosophy ትምህርት ይሄ አመክንዮአቸው ስህተት መሆኑ ከተመሰከረባቸው በእውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል ሀሳባቸውን እስኪ እንመዝነው፦
➊ መፅሀፍ ቅዱስ አንድ ለአንድን ያዛልን? የሚለውን እናስቀድምና ፣
፨ ከብሉይ ኪዳን
፨ ከአድስ ኪዳንና
፨ ከሚስጥራዊ መልእክቱ ተነስተን ማስረጃዎችን እናቅርብ፦
✟ #ከብሉይ_ኪዳን፦ ትዳር ወይንም ጋብቻ በሰው ፈቃድ የተመሰረተ ሳይሆን እግዚአብሔር እራሱ ከፍጥረት መጀመሪያ የመሰረተው የተባረከ ግንኙነት ነው። እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ አልተወውም አጋዥ የምትሆነውን ሔዋንን ከጎኑ አበጅቶለታል። ይሄ የእግዚአብሔር ፍጥረት እንደሚያስረዳን ለአንድ ወንድ የሚያስፈልገው አንድት ሴት እንጂ የሴት ጋጋታ አይደለም። ለአዳም ከእርሱ በላይ ስለእርሱ ሁሉን አዋቂ የሆነው እግዚአብሔር ያውቃልና ለአዳም አንድት ሴት የማትበቃው ቢሆን ኖሮ አራት አጋሮችን በፈጠረለት ነበር ግን የሴት ብዛት እንኳን ለመንፈሳዊ ሰው ለስጋዊ ለራሱ እርካታን አያመጣምና በአንድ ሴት ወሰነው። ጥንተ ተፈጥሮ ለአንድ ወንድ አንድት ሴት በቂ መሆኗን ያስገነዝበናል። ሙስሊሞች አንድ ወንድ ለአራት ሴት ሲሉ እራሳቸው ከአምላክ በላይ እናውቃለን እያሉ እንደሆነ ማወቅ ይገባቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ከአስርቱ ህግጋት በአስረኛው ህግ
“የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤👉 #የባልንጀራህን_ሚስት ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።”
— ዘጸአት 20፥17 የሚል ነው በዚህ ላይ " ሚስት" የሚለው ቃል ነጠላ ቁጥርን አመልካች ሆኖ መቅረቡ አንድ ሚስት ሊኖር እንደሚገባ ያሳስበናል።
✟ ♦ አድስ ኪዳን ፦
ሮሜ 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
² ያገባች ሴት ባልዋ በሕይወት ሲኖር ከእርሱ ጋር በሕግ ታስራለችና፤ ባልዋ ቢሞት ግን ስለ ባል ከሆነው ሕግ ተፈትታለች።
³ ስለዚህ ባልዋ በሕይወት ሳለ ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ ትባላለች፤ ባልዋ ቢሞት ግን ከሕጉ አርነት ወጥታለችና ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ አይደለችም።
ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ ከሁለቱ የ polygamy አይነቶች (polygyny & polyandrous) መካከል የሁለተኛውን አይነት ማለትም አንድት ሴት በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ የምታገባበትን ስርዓት ሲቃወም እናገኘዋለን። ይኽ የሚያሳየን ከአንድ በላይ ጋብቻን (polygamy) በአድስ ኪዳን የተወገዘ መሆኑን ነው።
“ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት።”
— 1ኛ ቆሮንቶስ 7፥2
በዚህም ላይ ሐዋርያው "ሚስት ትኑረው " አለ እንጂ "ሚስቶች ይኑሩት "አላለም።
በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ የካህናት የስርዓት ሁኔታ ሊሆን ስለሚገባው አስቀምጦልናል፦
“እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥”
— 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥2
እና ይኼ ለካህናት እንጀ ሕዝበ ምዕመኑን መች ይመለከታል? ቢሉ የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪወች ለምዕመኑ ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚገባቸው በተደጋጋሚ ተገልጿል ፦
“ይህን እዘዝና አስተምር። በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ፥ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው።”
— 1ኛ ጢሞቴዎስ 4፥11-12
“ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤”
— 1ኛ ጴጥሮስ 5፥3
ለህዝበ ምዕመኑ አርአያ ሁኑ ከተባለ እነርሱ አንድ ሚስት በማግባት ምሳሌአችን ሲሆኑ እኛም የእነርሱን ፈለግ ተከትለን ወንዱ በአንድ ሚስት ፤ ሴቶች በአንድ ወንድ የምንወሰን ይሆናል ማለት ነው።
✟ ♦ ሚስጥራዊ ይዘቱ፦ በመፅሀፍ ቅዱስ የባልና የሚስት ግንኙነች ከክርስቶስና ከቤተክርስቲያን ግንኙነት ጋር በንፅፅራዊ መልኩ ቀሮቧል፦
ኤፌሶን 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²² ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤
…
³¹ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።
³² ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ።
³³ ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፥ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ።
አንዱ ክርስቶስ ለአንዲት ሙሽራ ከሆነ ያለችው አንድ ወንድ ለአንዲት ሚስት መወሰንም ተገቢ ይሆናል ማለት ነው። መፅሀፍ ቅዱስ ስለ አንድ ለአንድ ጋብቻ እንዲህ በጠራ መልኩ ያስተምረናል።
➋ በሙሴ ህግ ከአንድ በላይ ማግባት ተፈቅዶ የለምን?
በሙሴ ህግ አንድ ወንድ ከሚስቱ ሌላ ተጨማሪ ሚስትን ቢያጋባ በምን መልኩ ሊያስተዳድር እንደሚገባው ያስቀምጣል፦
“ከእርስዋ ሌላም ቢያጋባው፥ መኖዋን ልብስዋንም ለምንጣፍዋም ተገቢውን አያጕድልባት።”
— ዘጸአት 21፥10
ሙስሊሞች እና በዚህ ዘመን የሚመሰረቱ አዳድስ የክርስትና ዶሚኔሽኖች ይህንን ህግ ይጠቅሱና "እግዚአብሔር ከአንድ በላይ ጋብቻን ፈቅዷል" ይላሉ። እውነቱ እንደዛ ነውን? የሚለውን እንመልከት።
ከአንድ በላይ ላገቡ ሰዎች በህግ ተቀመጠ እና እግዚአብሔር ይህንን ድርጊት ይወደዋል ወይንም ፈቅዷል ማለት አይደለም ምክንያቱም በብሉይ እግዚአብሔር የማይወደውን ነገር ከልባቸው ድንዳኔ የተነሳ ህግ ሲሰራላቸው እንመለከታለን።
ለምሳሌ ፦ እግዚአብሔር ፍችን እንደሚጠላ በመፅሀፍ ተናግሯል፦
“👉 መፋታትን እጠላለሁ፥ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፥ ልብሱንም በግፍ ሥራ የሚከድነውን ሰው እጠላለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ እንዳታታልሉ መንፈሳችሁን ጠብቁ።”
— ሚልክያስ 2፥16
እግዚአብሔር ምንም እንኳን መፋታትን ቢጠላም ከልባቸው ድንዳኔ የተነሳ ግን በሙሴ ህግን አስቀምጦላቸዋል፦
“አንድ ሰው አንዲት ሴት ካገባ በኋላ፣ አሳፋሪ ነገር አግኝቶባት ባይደሰትባት፣ የፍቺ ወረቀት ጽፎ በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ይስደዳት።”
— ዘዳግም 24፥1
ከዚህ ልንረዳው እንደምንችለው በህግ ስለተቀመጠ ብቻ ድርጊቱን እግዚአብሔር ይወደዋል ማለት አይደለም። በዚህ ዙሪያ ከፈሪሳውያን ጌታን ለመፈተን የመጣ ጥያቄ ነበረ፦
ማቴዎስ 19
¯¯¯¯
¯¯¯¯¯¯
³ ፈሪሳውያንም ሊፈትኑት ቀርበው፣ “ለመሆኑ አንድ ሰው በማንኛውም ምክንያት ሚስቱን መፍታት ተፈቅዶአልን?” ሲሉ ጠየቁት።
⁴ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤👉 “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን?
⁵ እንዲህም አለ፤👉 ‘ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ የተባለው በዚህ ምክንያት አይደለምን?
⁶👉 ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”
⁷ እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ሙሴ አንድ ወንድ የፍቺውን የምስክር ወረቀት ሰጥቶ ሚስቱን እንዲያሰናብት ለምን አዘዘ?” አሉት።
⁸ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ የልባችሁን ጥንካሬ አይቶ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ እንጂ ከመጀመሪያው እንዲህ አልነበረም፤
ጌታ የፍች ህጉ ለምን እንደተቀመጠ ሲናገር ከልባቸው ድንዳኔ የተነሳ እንጂ ጥንተ ተፈጥሮ ይህ እንዳልነበረ ነግሮናል። ይኽ የሚያሳየን ከአንድ በላይ የማግባትም ህግ ከልባቸው ድንዳኔና ከበደላቸው ብዛት የተነሳ እንጂ ጌታ ወዶት ህጉን አልሰጠንም ማለት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ በዚህን ንግግሩ ያ የወጣውን ህግ ሽሮ ትዳርም ከጥንቱ አንድ ለአንድ መሆኑን ፣ አሁንም ከአንድ በላይ ማግባት እንደማይገባን አስተምህሮናል።
➌፦ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ሰዎች ከአንድ በላይ ሚስትን ያገቡ አልነበረምን?
በብሉይ ኪዳን ከአንድ በላይ እንዳገቡ የሚገነርላቸው በርካታ ሰዎች አሉ ከእነዛ መካከል አብርሃም ፣ ያዕቆብ ፣ ዳዊትና ሰለሞን በብዛት የሚጠቀሱት ናቸው። ሙስሊሞች እና ዘመነኛ <<ክርስቲያኖች>> ( ክርስቲያን የሚለው ስም በ << >> ምልክት ውስጥ መቀመጡ እኒህ ሰዎች ክርስቲያን ሊባሉ የማይገባቸው መሆኑን ያመለክታል) እነዚህ የተጠቀሱ አባቶች ከአንድ በላይ ስላገቡ ከአንድ በላይ ጋብቻ ችግር የለውም ሲሉ ይደመጣሉ። ዋናው ነጥብ ግን ከአንድ በላይ ሲያገቡ እግዚአብሔር ፈቅዶላቸው ነው ወይ? የሚለው ነው። በመፅሀፍ በየትም ስፍራ እግዚአብሔር ከአንድ በላይ እንዲያገቡ ወዶ ፈቅዶላቸው ያገቡ የሉም። እግዚአብሔር ወዶ ያልፈቀደላቸውን ይዘው "እኛም" ማለት የዋህነት ነው።
እስኪ ከላይ የተጠቀሱትን አባቶች የጋብቻ ሁኔታ እንዬው፦
⭕ አብርሃም ፦ የአብርሃም ጋብቻ የሰመረ የነበረ ቢሆንም ልጅ አልነበራቸውም። እግዚአብሔር ለአብርሃም ልጅ እንደሚሰጠው ቃል ቢገባለትም ሚስቱ ሳራ ግን ከእምነቷ ማነስ የተነሳ ተስፋ በመቁረጥ አብርሃምን ወደ ሰራተኛዋ ወደ አጋር እንዲገባ እና ልጅን እንዲወልድ አደረገችው። ጻድቅ አብርሃምም የሚስቱን ቃል ሰምቶ ገባ። አብርሃም ወደ አጋር መግባቱ የሳራን የእምነት ድክመት የሚያሳየን ሲሆን በዚሁ እምነት ማነሷ በሰራተኛዋ ስትናቅ እናያለን።በዚህ ላይ ከእግዚአብሔር የሆነ ምንም ተግባር የለም!
ከዚህም በተጨማሪ አብርሃም ከአጋር ጋር የትዳር ግንኙነት የሌለው መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ወደ አጋር የገባው በትዳር ሳይሆን ልጅን ለመውለድ ነው።
📌 የያዕቆብ ትዳርን ስንመለከት ይህም ትዳር ልክ እንደ አብርሃም ትዳር እግዚአብሔር ያልፈቀደው ነው። ይህን ከታሪኩ መረዳት እንችላለን። ያዕቆብ ላባን ሲያገለግል የነበረው ራሔልን ለማግኘት ነበር ላባ ግን የያዕቆብ እርሱን ማገልገል ባለጸጋ አድርጎታልና ተጨማሪ አመት እንዲያገለግለው ሲል ልያን አጋብቶታል ያዕቆብም ያገባትን መፍታት ስለማይችል ለራሔል ሌላ ተጨማሪ አመታትን አገልግሎ ወሰዳት። ይኽ እንደሚያሳየን የያዕቆብ ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት እንኳን እግዚአብሔር አድርግ ብሎ ያዘዘው መሆኑ ይቅርና የራሱ የያዕቆብ እንኳን ፍላጎት እንዳልነበረ ነው።
አብርሃም ወደ አጋር ፣ ያዕቆብም ወደ ዘለፋ እና ባላ መግባታቸው በእግዚአብሔር አስቀጥቷቸዋልን? የሚለውን ስንመለከት እንደ ጥንታዊያን አባቶች አመለካከት ለሚስታቸው ቃል ያላቸውን ቀናኢነት የሚያመለክት እንጂ የእነርሱ ጥፋት አይደለም የሚል ነው፦
"For it is a thing established of old time, and frequently
heard of in the Ecclesiastical books that not only the natural way of birth, but the free
choice of the will also, should give birth to a child. For women, if they had no children
of their own, used to adopt children born of their husbands by their hand-maids, and even
oblige their husbands to give them children in this way; as Sarah, Rachel, and Leah And
in doing this the husbands did not commit adultery, in that they obeyed their wives in that
matter which had regard to conjugal duty" ( S.Augustine npnf1o6. Pp 547)
📌 የዳዊትን ስንመለከት እነሱ ከሚችሉት ጋር ተመሳሳይ ጋብቻ ሳይሆን ዝሙት ነው ዳዊት ምንም እንኳን በጌታ የተመረጠ ነብይ የነበረ ቢሆንም ሰው ነውና ኃጢአትን ፈፅሟል በነዚህም ጌታ በእርሱ ላይ ሌላ ነብይን ሹሞ ገስፆታል እርሱም እግዚአብሔርን በደልኩ በማለት ንስሐ ገብቷል። ይኼ የሚያሳየን የዳዊት በንስሐ የመጣ ቅድስናውን እንጂ ከአንድ በላይ ጋብቻውን አይደለም።
📌 የሰለሞን ስንመለከት እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ለሚነግስ ንጉስ ያስቀመጠው ህግ ነበር፦
“ልቡ እንዳይስትም ብዙ ሚስቶችን አያግባ፤ ብዙ ብርና ወርቅም አያግበስብስ።”
— ዘዳግም 17፥17
በእስራኤል ላይ የሚነግሰው ንጉስ ባለው የጦር ሰራዊት እንዳይመካ ፈረሶችን አያብዛ ፣ ልቡ ስቶ ከእግዚአብሔር ሀሳብ እንዳይወጣ ሚስት አያብዛ ፣ ባለጸጋ ነኝ ብሎ እግዚአብሔርን እንዳይረሳ ሀብት አያብዛ የሚል ህግ ወጥቶ ነበር። ሰሎሞን ግን ይህንን ህግ በመተላለፍ ከአንድ በላይ ሚስትን አግበቷዋል። ለዚህም በደሉ እግዚአብሔር ዕድሜው እንዲያጥር ፣ መንግስቱም እንዲከፈል አድርጎበታል።
በዚህ መሰረት ከብሉይ ኪዳን አባቶች ከአንድ በላይ በፈቃዳቸው ያገቡ የሉም ፣ ያገቡትም የንግስና ስርዓቱን ሽረዋልና በእግዚአብሔር ሲቀጡ የምንመለከት እንጂ የእነርሱን ስራ እንደበጎ ግብር ወስደን እኛ የምንደግመው አይነት አይደለም።
ስናጠቃልል ከአንድ በላይ ጋብቻ ጅምሩን ያደረገው በዘፍ 4:19 ላይ በላሜሕ ትዳር ነው፦
“ላሜሕ ሁለት ሚስቶች አገባ፤ የአንደኛዋ ስም ዓዳ፣ የሁለተኛዋም ጺላ ነበር።”
— ዘፍጥረት 4፥19
ላሜሕ እራሱን የሚቅብ ፣ ከእግዚአብሔር ውጭ የሚሄድ ሰው መሆኑን ዝቅ ብለን ቁጥር 23ን መመለከት እንችላለን፦
“ላሜሕ ሚስቶቹን እንዲህ አላቸው፤ “ዓዳና ጺላ ሆይ ስሙኝ፤ የላሜሕ ሚስቶች ሆይ አድምጡኝ፤ አንድ ሰው ቢያቈስለኝ፣ ጒልማሳው ቢጐዳኝ፣ ገደልሁት፤”
— ዘፍጥረት 4፥23
ይህ የሚያሳየን ከአንድ በላይ ማግባት ከጅምሩም የኃጢአት ውጤት እንጂ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተጀመረ አልነበረም።
ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ሚስትን በማግባት የፍትወት እርካታን ማግኘት የማይቻልም መሆኑን ከዳዊት እና ሰሎሞን ታሪክ መማር እንችላለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
Comments
Post a Comment