አማኑኤል ተብሎ የተጠራበትን ቦታ አሳዩን❓
አማኑኤል ተብሎ የተጠራበትን ቦታ አሳዩን❓
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ ፡ በወልድ ፡ በመንፈስ ቅዱስ ስም!
ብዙ ጊዜ ስለ ኢየሱስ አምላክነት የተተነበየበትን የብሉይ ኪዳን ትንቢት ለማሳየት ከምንጠቅሳቸው ጥቅሶች መካከል ኢሳይያስ 7:14 አንዱ ሲሆን ይህንን ጥቅስ ስንጠቅስ ሙስሊሞችም ሆኑ አይሆዱች ይህንን ጥቅስ ለመቃዎም አንድ ሁለት ሙግቶችን ያነሳሉ። አንዱን ሙግታቸውን እግዚአብሔር ቢወድና ቢፈቅድ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን ብለን ቀጠሮ እንያዝና ከሁለቱ እየተዘወተረ የሚነሳውን አንዱን " ትንቢቱ ' ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። ' ነው የሚለው ይህ ትንቢት ስለ ኢየሱስ ከሆነ ኢየሱስ አማኑኤል ተብሎ የተጠራበት ቦታ የት አለ?" የሚለውን ለዛሬ እንመለከታለን ።
ወደ መልሱ ስንገባ ይህ ሙግታቸው ውሃ የማያነሳበትን ሁለት ምክንያት በማስቀመጥ ምላሻችንን እንቋጫለን፦
➊፦ ትንቢቱ የተፃፈው በአይሁድ ልማድ ነውና በእነርሱ ልማድ መሰረት ለአንድ አካል ስም ሲሰጥ የግድ በዛ ስም መጠራት አለበትን? የሚለውን አስቀድመን እንመልከት።
በጊዜው በነበሩ አይሆዶች ለአንድ አካል ጊዜውን እና ሁኔታዎችን ያገናዘበ ወይንም ደግሞ የተሰየመው አካል ሊያሟላው የሚችል የተለያየ ስም መስጠት የተለመደ ነው ግን ይህን የተለያየ ስም ሲሰጡ የግድ በዛ ስም ይጠራ የሚል መርህ የላቸውም። ይህንን ለማሳየት ሶስት ምሳሌዎችን ልጥቀስ፦
#1ኛ፦ በዚሁ በትንቢተ ኢሳይያስ 8 : 3 ላይ ነቢዪቱ ልጅን እንደምትወልድ ስሙንም " ማሄር ሻላል ሃሽ ባዝ(ምርኮ ፈጠነ ፤ ብዝበዛ ቸኮለ)" ብለው እንዲጠሩት ይናገራል፦
“እኔም ወደ ነቢዪቱ ሄድሁ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። እግዚአብሔርም፣ እንዲህ አለኝ፤ “ስሙን ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ ብለህ ጥራው።”— ኢሳይያስ 8፥3
ኢየሱስ የግድ አማኑኤል በሚለው ስም መጠራት አለበት ለሚሉ ጥያቄን እንጠይቅ፦ ይህ የተወለደው ህፃን የት ነው ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ ተብሎ የተጠራው? የተባለበት የለምና ሊያመጡ አይችሉም ምክንያቱም ይህ ስም የተሰጠው እርሱ በሚወለድበት ጊዜ የምርኮ መወሰድና መከፋፈል ስለነበረ ነው፦
“ሕፃኑም፣ ‘አባባ’ ወይም ‘እማማ’ ብሎ መጥራት ከመቻሉ በፊት፣ የደማስቆ ሀብትና የሰማርያ ምርኮ በአሦር ንጉሥ ይወሰዳል።””— ኢሳይያስ 8፥4
ስለዚህ ይህ ሰም ድርጊቶችን ያገናዘበ እንጂ በግድ እንዲጠራበት የተሰጠው አይደለም።
#2ኛ፦ አሁንም ከዛው ከትንቢተ ኢሳይያስ ሳንወጣ ሌላ ምሳሌን እንጥቀስ፦
“ፈራጆችሽንም እንደ ቀድሞ አማካሪዎችሽንም እንደ መጀመሪያው ጊዜ መልሼ አስነሣለሁ፤ ከዚያም በኋላ የጽድቅ_ከተማ_የታመነችም_ከተማ_ተብለሽ_ትጠሪያለሽ።” — ኢሳይያስ 1፥26
ይህቺ ከተማ " የጽድቅ ከተማ የታመነችም ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ" ብትባልም ኢየሩሳሌም ከመባል ውጭ እንዲህ ተብላ የተጠራችበት ቦታ የለም። እና ለምን "ተብለሽ ትጣሪያለሽ አለ?"ካልን ልክ እንደላይኛው በጊዜው የነበረው የሀገሪቱ ሁኔታ ሊያሟላው የሚችለው ስያሜ ነው። በዚያን ጊዜ በሀገሪቱ ፍትህ ተመልሶ ጥሩ ሁኔታ ላይ በመገኘቷ የጽድቅ ከተማ የታመነች ከተማ አሰኝቷት ነበር።
3ኛ፦በመጨረሻም አንድ ከመፀሀፈ ሳሙኤል እንጥቀስ፦
2ኛ ሳሙኤል 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁴ ዳዊትም ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፥ ወደ እርስዋም ገባ፥ ከእርስዋም ጋር ተኛ፤ ወንድ ልጅም ወለደች፥ ስሙንም 👉 #ሰሎሞን ብሎ_ጠራው። እግዚአብሔርም ወደደው፤
²⁵ ደግሞም በነቢዩ በናታን እጅ ልኮ ስሙን ስለ እግዚአብሔርም 👉 #ይዲድያ_ብሎ_ጠራው።
በዚህ ላይ እንደምንመለከተው ለዳዊት ልጅ ሁለት ስም ወጥተውለታል። የመጀመሪያው "ሰሎሞን" ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ "ይዲድያ" የሚል ነው። ይዲድያ(יְדִידְיָה ; Yᵉdîydᵉyâh) የሚለውን ትርጓሜ ስንመለከት ቃሉ( יְדִיד ; yᵉdîyd) & (יָהּ ; Yâhh) ከሚሉት ከሁለት ቃላት ጥምረት የመጣ ሲሆን ትርጓሜውን እግዚአብሔር የወደደው ወይንም በእግዚአብሔር የተወወደ ልንለው እንችላለን። ምንም እንኳን ይህ ህፃን "ይዲድያ" የሚል ስም ቢወጣለትም " ሰሎሞን" ከሚለው ስም ውጭ ግን ተጠርቶ አያውቅም። ይህ የሚያሳየን " ይዲድያ" የሚለው ስም የግድ እንዲጠራበት የተሰጠው ሳይሆን በልጁ እግዚአብሔር መደሰቱን ወይንም እግዚአብሔር ልጁን እንደወደደው የሚያመለክት ነው። ያ ማለት የልጁ የሚያሟላውን ባህሪይ የሚያመለክት ነው ማለት ነው።
ከዚህና ከላይ ከጠቀስናቸው ምሳለረዎች በመነሳት አይሁዶች ለአንድ አካል ወይንም ነገር የተለያየ ስም መስጠት ልማዳቸው ቢሆንም በግድ በዛ ስም ይጠራ የሚል ግን መርህ እንደሌላቸው እንረዳለን።
የአይሁዶችን ልማድ ካየን ወደተነሳንበት ስንመለስ ፦ የሚወለደውን ልጅ " አማኑኤል" ትይዋለሽ መባሉ በሶስቱ ምሳሌዎች መሰረት የግድ ይጠራበት የሚለውን መርህ ያነገበ አይደለም። ከዛ ይልቅ በምሳሌ 2&3 ላይ እንዳሉት ይህም ስም የሚወለደው ህፃን የሚያሟላው ባህሪው ነው፦
የሚወለደው ህፃን " አማኑኤል" መባሉ ስጋን ተዋህዶ ከእኛ ዘንድ ማደሩን (ዮሀ1:14) ፣ በምድር እንደ ሰዎች መመላለሱን እንዲሁም ለዘላለም እንደማይተወን ሁሌም ከእኛ ጋር እንደሚሆን የሚያመለክት ነው።
“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤👉 #እነሆም_እኔ_እስከ_ዓለም_ፍጻሜ_ድረስ_ሁልጊዜ_ከእናንተ_ጋር_ነኝ።”— ማቴዎስ 28፥19-20
ስለዚህ "አማኑኤል ተብሎ ይጠራል" ሲባል የግድ እንዲጠራበት ተፈልጎ ሳይሆን የልጁን ባህሪይና ሁኔታዎችን ያገናዘበ ነው ማለት ነው።
ከዚህ ከኢሳ 7:14 በተጨማሪ ይህ አይነቱ ሙግት በኢሳ 9:6 ላይም ይታያል። በኢሳ 9:6 ለሚወለደው ህፃን " ድንቅ መካር ፣ ኃያል አምላክ ፣ የዘላለም አባት ፣ የሰላም አለቃ " የሚሉ በርካታ ስሞች ተሰጥተውታል። እኒህ ሁሉ ግን ከላይ እንዳየነው ሁሉ የግድ ሊጠራባቸው የተሰጡት ሳይሆን በሚወለደው ህፃን የሚሟሉ ናቸው።
"ድንቅ መካር " የዘላለም ህይወት የምናገኝባትን የመንግስተ ሰማያት እውነተኛ መንገድ በምክር ፡ በትምህርቱ የመራን እርሱ መሆኑን ያመለክታል።
"ኃያል አምላክ " ሰማያትን የዘረጋ ምድርን ያነጠፈ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ያመለክታል [ "ኃያል አምላክ" እግዚአብሔርን ብቻ ለመግለፅ የሚገባ መሆኑን ልብ ይሏል]
"የዘላለም አባት" መባሉ ለዘመኑ መነሻ እና መድረሻ የሌለው ዘላለማዊ መሆኑን ያሳያል።
ዕብራውያን 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁰ ደግሞ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤
¹¹ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥
¹² እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል።
"የሰላም አለቃ" መባሉ በምድር እና በሰማይ እርቅን መፈፀሙን በተጨማሪም እውነተኛ ሰላም ከእርሱ መሆኑን ያመለክተናል።
“ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።”— ዮሐንስ 14፥27
➋፦ ይህንን ሙግት የሚያነሱ ሰዎች እንደነርሱ አባባል ይሁንላቸው እንበል እንኳን ብንል የትንቢቱ ፍፃሜ "ይሉታል" ነው የሚለው፦
“እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል #ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም፦ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።”— ማቴዎስ 1፥23
ይሄ ደግሞ ድንግል ማርያምን እና ዮሴፍን ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ያለነውን እኛንም የሚያጠቃልል ነው። አሁን ላይ ያለነው እኛ ደግሞ " አማኑኤል" እያልን እንጠራዋለን። ስለዚህ ለምን በመፅሀፍ ቅዱስ በዚህ ስም አልተጠራም የሚለው በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ይፈርሳል ማለት ነው።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
©✞ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
Comments
Post a Comment