የድንግል ማርያም ትንሳኤና እርገት

 " ዕርገተ ማርያም"


        አንድ አምላክ በሚሆን በአብ ፡ በወልድ ፡ በመንፈስ ቅዱስ ስም!

    የክርስቶስ ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን!  ተወዳጅ የቻናላችን ቤተሰቦች በመጀመሪያ እናኳን ለፍስለታ ለማርያም በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን!   ዛሬ እግዚአብሔር ከፈቀደ በማርያም ፍስለተ ስጋ ላይ ትንሽ ነገርን ለማለት ፈልገን ነው ያው በርካታ ወንድሞች ፅፈውበታል አብራርተውታልም ግን ደግሞ እኛም የምናምነውን መመስከር ይገባናልና ትንሽ ነገር ለማለት ወደድን እስኪ አንዳንድ ጥያቄዎችን እያነሳን እንይ፦

 📌  ጥያቄ ➊፦

       “ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።”  — ዮሐንስ 3፥13

     " ይህ ቃል እንደሚነግረን ወደሰማይ ሊያርግ የሚችለው ኢየሱስ ብቻ ነው ስለዚህ ማርያም አርጋለች የሚለው የለየለት ክህደት ነው" ለሚሉት፦

   ይህን አመክንዮ የሚያነሱ ፕሮቴስታንት ወይንም ተሐድሶ ወንድሞች ሁለት ነገሮችን ዘንግተዋል እኒህ ነገሮች ደግሞ እንዲህ ለስህተት ዳርገዋቸዋል። የዘነጓቸው ሁለት ነገሮች፦

➊፦ ገና ከጅምሩ ይህንን አመክንዮ ስህተት የሚያደርገው ነገር ቢኖር እነርሱ እንደሚሉን ወደሰማይ ያረገው ኢየሱስ ብቻ ከሆነ መፅሀፍ እርስ በራሱ ይጋጫል ወደሚል ድምዳሜ ማምራታችን ነው ምክንያቱም መፅሀፍ ሄኖክና ኤልያስ ወደሰማይ አርገዋል ይለናልና፦

        “ሲሄዱም፦ እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ።”— 2ኛ ነገሥት 2፥11

      “ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና፤”— ዕብራውያን 11፥5

    ስለዚህም ወደሰማይ የወጣው ኢየሱስ ብቻ አይደለም ማለት ነው።

 ➋፦ ሁለተኛውና ወሳኙ ነገር ግን የኢየሱስ እርገት እና የማርያም እርገት አንድ ነው ወይ? የሚለው ነው።

    “No one has #ascended into heaven except the one who descended from heaven, the Son of Man.”— John 3:13 (NRSV)

    የእንግሊዝኛ መፅሀፍ ቅዱስ የኢየሱስን ወደ ሰማይ መውጣት ለመግለፅ የተጠቀመው የእንግሊዝኛ ቃል  "ascended " የሚለው ሲሆን ይሄ ቃል ኢየሱስን እና በራሳቸው ወደሰማይ መውጣት እና መውረድ የሚችሉትን ፍጡራን መላእክትን ከመግለፅ ውጭ የሰዎችን ወደሰማይ መውጣች መፅሀፍ አይገልፅበትም። ለምሳሌ ከላይ የጠቀስነውን የሄኖክን ብንመለከት "ተወሰደ (taken)" አለ እንጂ በስልጣኑ አረገ (ascended) " አላለም

      የማርያምን እርገት ለመግለፅ የምንጠቀመው የእንግሊዘኛ ቃል ደግሞ " assumption " የሚለውን ሲሆን ይህ ቃል "assumere" ከሚለው የላቲን ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓማውም " ወደራስ መውሰድ (to take to oneself.)"  ማለት ነው ይህ የሚያሳየን ማርያም አረገች ስንል ልክ ኢየሱስ በስልጣኑ ወደሰማይ አረገ በምንለው ሂሳብ አይነት የሚታሰብ ሳይሆን የልጇ በወዳጇ የኢየሱስ ስልጣንና ፈቃድ አስነሳት ወሰዳት በማለት ነው ይህ ደግሞ ከላይ ለሄኖክ ከተባለው ጋር ተመሳሳይ ነው።

📌 ጥያቄ ➋፦ "የድንግል ማርያም እርገት በመፅሐፍ ቅዱስ አልተፃፈም ስለዚህም ሀሰት ነው" ለሚሉት፦

    ይህንን ጥያቄ የሚያነሱት ወንድሞች ፕሮቴስታንት እና ተሐድሶዎች ስለሆነ ማንሳታቸው በእውነቱ የሚደንቅ ነገር አይደለም ምክንያቱም እነርሱ "መፅሀፍ ቅዱስ ብቻ" የሚል ፈሩን የሳተ መንገድ ላይ ናቸውና ስለዚህም የተፃፈውን ብቻ እንጂ ሐዋርያቶች በቃል ያስተምሩት የነበረውን ነገር አይቀበሉም ይህ ደግሞ መፅሀፍ ከሚያስተምረው ውጭ መሆን ነው ምክንያቱም ወንጌላዊያን እንኳን ሲፅፉ በቃል ይነገር የነበረውንም አካተው ፅፈዋል፦

   “የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን፥ በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ፥ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ።”— ሉቃስ 1፥1-4

    ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያት እራሳቸው በቃል ያስተምሩ እንደነበረ ያንንም መያዝ እንደሚገባን ነግረውናል፦

     “እንግዲያስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፥ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ።”— 2ኛ ተሰሎንቄ 2፥15

     ስለዚህም ሁሉ በመፅሀፍ ይፃፍ ያልተፃፈ ስህተት ነው የሚለው አያስኬደንም ማለት ነው።

    ከዚህ በተጨማሪ ሐዋርያት የክርስቶስን ትንሳኤ በሚያስምሩበት ወቅት በጊዜው በነበሩ ፈላስፎች ምን ይሉ እንደነበረ  መፅሀፍ ይነግረናል

      “ከኤፊቆሮስ ወገንና ኢስጦኢኮችም ከተባሉት ፈላስፎች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር ተገናኙ። አንዳንዶቹም፦ ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይወዳል? አሉ፤ ሌሎችም የኢየሱስንና የትንሣኤውን ወንጌል ስለ ሰበከላቸው፦ አዲሶችን አማልክት የሚያወራ ይመስላል አሉ።”— ሐዋርያት 17፥18

    የኢየሱስን ትንሳኤ በመስበካቸው እንዲህ ከአማልክት አስተምህሮ ጋር ካገናኙት የድንግልን ዕርገት ጨምረው ቢያስተምሩማ ምን ሊባሉ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ስለዚህም ለሚሰማቸው ህዝብ ድንግል ማርያም አማልክት ናት ብለው አስበው በእርሱ እንዳይስቱ በመልእክታቸውና በወንጌላቸው ሳያሰፍሩት ቀርተዋል።

  ከዚህ ባለፈ መፅሀፍ ስለ ማርያም እርገት በቀጥታ ንባብ ያይደለ በምስጢራዊ ይዘቱ በትንቢት  ተናግሯል፦

   “አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት።”— መዝሙር 132፥8


      የድንግል ትንሳኤ ተቃዋሚዎች ይኽ ጥቅስ "ስለ ታቦቱ ወደ ቤተመቅደስ መግባት የተነገረ እንጂ ስለ ድንግል ማርያም የተነገረ አይደለም " ተቃውሞን ያነሳሉ። እነርሱ እንዳሉት መዝሙሩ በጊዜው የተነገረው ስለ ታቦት ቢሆንም ፍፃሜው ግን ለድንግል ማርያም ነው። ይኽንን ስንል ከመሬት ተነስተን ሳይሆን በብሉይ ኪዳን እና በአድስ ኪዳን የቀረቡ ንግግሮችን በንፅፅር በማስቀመጥ ታቦት የተባለችው ድንግል ማርያም መሆኗን በማሳየት ነው፦

     ቅዱስ ዳዊት የእግዚአብሔር ታቦት ወደእርሱ ሲመጣ “ የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል? ።” በማለት እንደተናገረ ሁሉ (2ኛ ሳሙኤል 6፥9)

  ኤልሳቤጥም ድንግል ማርያም ወደእርሷ ስትመጣ   “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?” በማለት ተናግራለች (ሉቃስ 1፥43)

    ቅዱስ ዳዊት የእግዚአብሔር ታቦት በመጣ ጊዜ በታቦቱ ፊት እየዘመረ እንደዘለለ ሁሉ (2ኛ ሳሙኤል 6፥16)  ኤልሳቤጥ የድንግልን ድምፅ በሰማች ጊዜ ጽንሱ በማኅፀን ዘሏል (ሉቃስ 1:44)

    ታቦቱ በአቢዳራ ቤት ለሶስት ወር እንደቆዬ ሁሉ (2ኛ ሳሙኤል 6፥11) ድንግል ማርያምም በዘካርያስ ቤት ለሶስት ወር ያህል ቆይታለች (ሉቃስ 1:56)

    ይኽ ተራ መመሳሰል ነው የሚል የዋህ ካለ እራሱን እንደዛ እያለ ማሞኘት ይችላል ግን ይኼ ተራ መመሳሰል አንደለም ድንግል ማርያምን በምሳሌ እየመሰሉ ነብያት ያስቀመጡት ትንቢት እንጂ።

   ከዚህ በተጨማሪ መዝ132÷8 "አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት" በሚለው ውስጥ "አንተ" የተባለው አካል "የመቅደስህ ታቦት የተባለው አካል" እና "ዕረፍት" የተባለውን መመለከት ያስፈልጋል። 

"ኢየሱስም መልሶ። ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው።ስለዚህ አይሁድ። ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት።

እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር። ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ይህን እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ።" ዮሐ2÷19-22

  በዚህ ክፍል ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የራሱን ሰውነት መቅደስ ብሎ ጠርቶታል። አይሁድ ይህን መቅደስ ቢያፈርሱትም( ቢገሉትም) ከሞት እንደሚያስነሳው ነግሯቸዋል። ደቀ መዛሙርቱም በመጽሐፍ የተጻፈውን አሰቡ የሚለው በመዝ132÷8 ላይ የተጻፈውን ነው። መቅደስ የተባለ የክርስቶስ ሰውነት ከሆነ የመቅደስህ ታቦት ሲል የሰውነትህ ማደሪያ ማለቱ ነው። የሰውነቱ ማደሪያ ደግሞ ድንግል ማርያም ናት። ደንግል ማርያም ታቦት እንደምትባል ከላይ ያነሳናቸው ማነጻጸሪያዎች ይናገራሉ።

"ወደ ዕረፍትህ ተነስ" ሲል ደግሞ ወደ ሰማይ ተነስ ማለቱ ነው። መክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ሰማይ "ዕረፍት" ተብሏል።

" እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ።"

 ዕብ4:11እንዲል።

 📌ጥያቄ ➌፦  "በጥንቷ ቤተክርስቲያን አባቶች(early church fathers) ዘንድ አልተነገረም" ስለሚሉት ፦

     በጥንታዊያን የቤተክርስቲያን አባቶች ዘንድ ይህ የማርያም እርገት እስከ 5ኛው ክፍለ ዘመን ተፅፎ አናገኘውም ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው በጊዜው የነበሩ መናፍቆች ማለትም ኖስቲኮች በዚህ ዙሪያ ምንም አይነት ተቃውሞ ስላልነበራቸው ነው። የጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን አባቶችን ፅሁፍ ከተመለከትን የዕቅበተ እምነትን ስራ የሚሰሩ ነበሩ ማለትም ይነሱ ለነበሩት መናፍቃን መልስ ይሰጡ ነበረ በድንግል ማርያም ህይወት ዙሪያ ግን የተነሳ ምንፍቅና አልነበረም እና መፃፉ ያን ያህል አስፈላጊ አልነበረም። በእነዚህ የቤተክርስቲያን አባቶች ዘንድ ስለ ማርያም እርገት አልተፃፈምና እርገቷ ስህተት ነው ከተባለ በተመሳሳይ ስለ ድንግል ማርያም ሞቶ መቅረት የተፃፈ የለምና አላረገችም የሚለው ሀሰት ነው ማለት ነው። ነገር ግን ከአምስተኛው ክፍለ ዘመን በኋላ የተነሱ ተአማኒ የቤተክርስቲያን አባቶች ስለ ማርያም እርገት ፅፈዋል። ለምሳሌ አንድ አራት እንጥቀስ፦

 ➊፦  ቅዱስ ያዕቆብ (Jacob of Serugh) የተባለው የቤተክርስቲያን አባት በ451 የተወለደ ሲሆን ስለድንግል ማርያም እርገት ውዳሴን ፅፏል፦

     She wove and placed on her exalted head a beautiful crown, on which precious pearls were arranged. 

The name of Christ the King, who was crucified on Golgotha, gives life and sheds forth mercy to those who call upon it, and to me, a sinner, who is inadequate for the praises of the mother of mercies, who gave birth to you according to the flesh

➋፦   ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በ6ኛው ክፍለ ዘመን በጻፈው ድጓው ላይ የድንግል ማርያምን እርገት አስቀምጧል፦

     ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ይኽነን  በድጓው ላይ “ፃኢ እምሊባኖስ ሥነ ሕይወት ርቱዕ አፍቅሮትኪ ቡርክት አንቲ እምአንስት ማኅደረ መለኮት ሰላም ለኪ፤ ማርያም እመ አምላክ ወልድኪ ይጼውዐኪ ውስተ ሕይወት ወመንግሥተ ክብር” (የሕይወት ደም ግባት የአምላክ እናት ከሊባኖስ ውጪ፤ ፍቅርሽ የቀና ነው፤ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ፤ የመለኮት ማደሪያ ሰላምታ ላንቺ ይገባል፤ የአምላክ እናት ማርያም ሆይ ልጅሽ ወደ ዘላለማዊ ሕይወትና ወደ ክብር መንግሥት ይጠራሻል) በማለት አመስጥሮታል፡፡

በተጨማሪም ቅዱስ ያሬድም በዝማሬው ላይ “ፈለሰት ማርያም በስብሐት ውስተ ሰማያት መላእክት ወሊቃነ መላእክት ወረዱ ለተቀብሎታ” (እመቤታችን በምስጋና ወደዚያኛው ዓለም በተለየች ጊዜ ለአቀባበሏ መላእክትና ሊቃነ መላእክት ወረዱ) ይላል፡፡

➌፦ የምዕራባዊያን ቤተክርስቲያን አባት የሆነ ጎርጎሪዮስ (St. Gregory of Tours) የተባለ በ6ኛው ክፍለ ዘመን ሶስት አስርት አመታት አካባቢ ይኖር የነበረ አባት ስለ ድንግል ማርያም እርገት ፅፏል። 

 ❹፦ በ676 የተወለደው ለአስልምና እና ለተለያዩ ኑፋቄዎች መልስ በመስጠት የዕቅበተ እምነትን ስራ የሰራው ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ (St. John Damascene) የተባለው አባት በውዳሴው ላይ የድንግል ማርያምን እርገት ሰፋ ያለ ትንታኔ ድርሰቱን ፅፏል።

 እኒህን ሶስት አባቶች ተአማኒነት ያላቸው በማለት ጠቀስን እንጂ ሌሎች St. Andrew of Crete, St. Modestus of Jerusalem እና Bishop Theoteknos of Livias  የተባሉ ተአማኒነት ያላቸው ሌሎችም አባቶች አሉ። ከእነዚህ በተጨማሪ  apocryphal ወይንም psuedo በማለት የሚያጣጥሏቸው በርካታ ከአስረኛው ክፍለ ዘመን በፊት የነበሩ ፅሁፎች ተገኝተዋል። ይህንን መመልከት ለወደደ Ancient Traditions of the Virgin Mary’s Dormition and  Assumption በሚል ርዕስ በ STEPHEN J. SHOEMAKER የተፃፈን መፅሀፍ ገፅ 419 ላይ ገልፆ መመልከት ይችላል።

    የተሐዲሶና ፕሮቴስታንቶችን ከነቱ ድካምነት ለማሳየት ግን እራሳቸው የተሐዲሶ መስራቾች ያሉትን በማስቀመጥ ነጥባችንን እንቋጫለን፦ 

 Martin Butzer የተባለው የፕሮቴስታንት አቀንቃኝ የነበረ ስለ ድንግል እርገት ይህንን ብሏል፦    "Indeed, no Christian doubts that the most worthy Mother of the Lord lives with her beloved Son in heavenly

joy." ( Marienlexikon , vol 3, 200)

  በተጨማሪም Martin Luther ይህንን ብሏል፦

    "There can be no doubt that the Virgin Mary is in heaven. How it happened we do not know. And since the Holy Spirit has told us nothing about it, we can make of  it no article of faith... It is enough to know that she lives in Christ." -Martin Luther (Sermon, Feast of the Assumption of Mary, 1522)

📌 ጥያቄ ❹፦ "ሞት የኃጢአት ውጤት ነው ማርያም ደግሞ ከጥንተ አብሶ ነፃ ከሆነች ለምን ሞተች?" ስለሚሉት

1) ድካም በእረፍት እንደሚወገድ ከምድራዊው ድካም እመቤታችንን ያሳርፋት ዘንድ እረፍተ ሥጋን ወደእርሷ ልጇ አመጣ ይኸውም ከተገፋችበት ፤ከተንከራተተችበትና የኀዘንና የመከራ ሰይፍን ካስታናገደችበት ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ወደመንግሥተ ሰማያት መጠራቷን ሲያጠይቅ በሥጋ አረፈች ተባለላት ።ሞቷስ የማያልፈውን ዋጋ እንደተቀበለች ለማሳየት እንጂ የሞት ሞት የሚባለውን መፍረስና መበስበስን፤ወደ ሲኦል መውረድን የሚያሳይ አይደለም ።


2) ከሰማይ የወረደች (ኃይል አርያማዊት) ናት የሚሉ አሉና ሰው እንደሆነች እና ከምድር እንደተገኘች


፤ሙሉ የሰውነት ማንነት ያላት መሆኑን ለማጠየቅ ነው፤ እመቤታችንን ሞት ባያገኛት ካልዕ ፍጥረት (ልዩ ፍጥረት) ስለሆነች ነው ብለው ብዙዎች በተከራከሩ ነበር፤ይህም ደግሞ ክርስቶስ የነሣውን ሥጋና ነፍስ (ምሥጢረ ተዋሕዶን) ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከተው ነበርና

በዚህ ምክንያት በሕገ ሰብእ በሩካቤ ብእሲ ወብእሲት ስለተገኘች በሕገ ሰብእ ሞት ተጠርታለች፤ ይህ ሞቷ እሷን ሌላ ፍጥረት የጌታን ተዋሕዶ ምትሐት ከማለት የሚታደግ መድኃኒትም ጭምር ነው፡፡


3) ፍትሑ ርቱዕ (ፍርዱ ቅን የሆነ) እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ ያጠይቃል፤ እመቤታችን እንደማንኛውም ሰው ሞትን ባታይና ባትቀምስ ፍርዱ ትክክል አይደለም፤ አንዱን በሞት ይወስዳል ሌላውን ይተዋል፤ወዲህም ልጅዋ አምላክ ነውና ሞትን ያልቀመሰችው በልጅዋ ምክንያት እንጂ እርሷ የተለየ ቅድስና ስላላት አይደለም በተባለ ነበርና ሞትን እንድትቀምስ ፈቅዷል፤ሞትን መቅመሷ በክብር ላይ ክብር ቢጨምርላት እንጂ ቅንጣት ታህል ክብር አይቀንስባትምና፡፡

~ይህንንም ደራሲው፦

"ኢያድለወ ሞተ ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ፤ክርስቶስ ሥጋውን ለነሳበት አካል

# በሞት # አላዳላም " በማለት ተናግሯል፡፡

ቅዱስ ያሬድም ፦

"እንበይነዝ አእምሩ በውስተ ፍትሕ ከመ ኢያደሉ ትጥዓም ሞተ እሙ ወእመኩሉ አዘዘ ወልድ በርቱዕ ቃሉ" (በፍርድ እንደማያዳላ ስለዚህ ነገር ዕወቁ፤የእርሱ እናት፤የሁሉ እናት እመቤታችን ሞትን ትቀምስ ዘንድ ወልድ በማይሻር ቃሉ አዘዘ) በማለት አስረግጦ ተናግሯል። (የዕለቱ ዚቅ)፡፡


4) በነገረ ማርያም ላይ እንደተጻፈው እመቤታችን የዕረፍት ጊዜዋ መድረሱን

ጌታችን ሲነግራት እንዴት እኔ የአንተ እናት ሆኜ ሞት ያገኘኛል? በማለት ጠይቃለች፤ቅዱስ ያሬድ እንደገለጸው "እፎኑመ እመ አምላክ በከየት ደንጊፃ ከመ ኩሉ ሰብእ ሞት ሶበ ሐወጻ፤እንደማንኛውም ሰው ሞት በጎበኛት ጊዜ የአምላክ እናት እንደምን አለቀሰች?" (የዕለቱ ዚቅ)፡፡ጌታችንም አንቺ ስትሞቺ ባንቺ ሞት ምክንያት ከሲኦል የሚወጡ ነፍሳት አሉ

በማለት ነገራት፤ እመቤታችንም ርኅርኅት ናትና በኔ ሞት ምክንያት ነጻ የሚወጡ ነፍሳት ካሉ አንድ ጊዜ አይደለም ሰባት ጊዜ ልሙት ብላ መልሳለታለች፤ይህም ማለት ሁሉም ነፍሳት በእመቤታችን ሞት ምክንያት ከገነት ይወጣሉ ማለት ሳይሆን እግዚአብሔር ባወቀ የእናቱ ሞት ቤዛ እንዲሆናቸው የመረጣቸው ነፍሳት መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡

• በብሉይ ኪዳን ጥንተ አብሶ ያለባቸው ሰዎች ሲሞቱ መልአከ ሞት

ይታያቸው ነበር ለእመቤታችን ግን ልጅዋ ራሱ ክርስቶስ ነው የተገለጠላት፤

• በብሉይ ኪዳን የሞቱ ሰዎች ወደ ሲኦል ነበር የሚወርዱት እመቤታችን ግን

ሥጋዋ በገነት ነፍሷ በልጅዋ እጅ ነበር፤

• ከአዳም ልጆች ወገን የመጨረሻውን ትንሣኤ የተነሣ የለም፤እመቤታችን

ግን እንደ ልጅዋ ተነሥታለች ዐርጋለች፤መዝ 131፤8፡፡ ሰለዚህ የእመቤታችን ሞት ይደንቃል፤ሁላችን ከሞታችን በፊት የሰራነው ብዙ

ኃጢአት አለ፤ እመቤታችን ግን ንጽሕት ናት

ሞቷም በሲኦል ስላሉ ውስን ነፍሳት በልጅዋ ፈቃድ ቤዛ ሆኖ የተሰጠ፤የተከፈለ ነው፡፡



               ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

          ወለወላዲቱ ድንግል!

          ወለመስቀሉ ክቡር!

          ይቆየን!




         ©✞ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ


ለማንኛውም አስተያየት ➞ @akabianement

    

  👍 Like our page & follow us

የቴሌግራም    ቻናላችንን ይቀላቀሉ👇

     https://t.me/ekbetemnet

Comments

Popular posts from this blog

ዕቅበተ እምነት

ወላዲተ አምላክ

መልስ ለወሒድ ዑመር