ክፍ. ፬ የኢየሱስ አምላክነት ከአድስ ኪዳን ( ዮሐንስ 20:28)

 

      አንድ አምላክ በሚሆን በአብ ፡ በወልድ ፡ በመንፈስ ቅዱስ ስም!

    የክርስቶስ ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን ተወዳጅ የድረገፃችን ቤተሰቦች።
የቀደመውን ክፍል ለማግኘት፦( ክፍል ፫ [ የዮሐንስ 10:30 ] )

  ለዛሬም በዚህ ፅሁፍ የምንዳስሰው የወንጌል ክፍል ደግሞ ዮሐ 20:28 ሲሆን የዮሐንስ ወንጌል የመጨረሻ ክፍላችን ይሆናል ማለት ነው። የመጨረሻ ክፍል ስንል ግን "ሌሎች የኢየሱስን አምላክነት የሚያሳዩ የሉም" ማለት አይደለም በዚሁ ክፍል ንዑስ ክፍል ፩ ላይ እንዳልነው አድስ ኪዳን የኢየሱስን አምላክነት በገፍ ያውጃል እኛ የምንመለከተው ግን በወፍ በረር ነውና ኢየሱስ አምላክ መሆኑን የተናገረበት እና የተነገረበትን ጥቅስ  በዮሐንስ ወንጌል የወፍ በረር ዳሰሳችን የመጨረሻችንን ይዘን ቀርበናል። ሌሎች ያሉትን ማስረጃዎች ደግሞ በሌላ መንገድ የኢየሱስን አምላክነት ለማሳየት ይጠቅሙናልና ያኔ እንመዛቸዋለን።  ወደ ምልከታችን እንሂድ ፦

²⁷ ከዚያም በኋላ ቶማስን፦ ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው።²⁸ ቶማስም፦ ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት።²⁹ ኢየሱስም፦ ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው።( ዮሐንስ 20:27-29)
    የኢየሱስ አምላክነት በማወጅ የሚጀምረው የዮሐንስ ወንጌል ባሉት ምዕራፎች ለአምላክነቱ ምስክር እየሰጠ ከመጣ በኋላ በስተመጨረሻም በግልፅ እና በማያወላዳ መልኩ የኢየሱስን አምላክነት እንዲህ በመሰለ መልኩ ገልፆ ያስረግጣል።

   ምንም እንኳን ጥቅሱ በራሱ ግልፅ  እና ግልፅልፅ ያለ ቢሆንም ላለማመን ምክንያት ደርዳሪዎች አሉና እራሳቸውን ምክንያታዊ ለማድረግ የሚያነሷቸውን ደካማ የሙግት ነጥቦች በመመልከት የኢየሱስን አምላክነት አናውጃለን።

    በዚህ ጥቅስ ዙሪያ የሚነሱት ክሶች በሁለት ነጥብ የሚቀመጡ ናቸው እነርሱም፦

   ➊፦ ጌታዬ የተባለው ኢየሱስ ሲሆን ፤ አምላኬ የተባለው ደግሞ አብ ነው።

   ➋፦ ቶማስ " ጌታዬ አምላኬ" ሲል በመገረም ስሜት እንጂ ኢየሱስን አምላኬ እያለ አይደለም።
   የሚሉት ናቸው እስኪ እያንዳንዳቸውን ጌታ በፈቀደ መጠን እንመልከታቸው፦
~~
  ነጥብ ➊፦ ጌታዬ የተባለው ኢየሱስ ሲሆን ፤ አምላኬ የተባለው ደግሞ አብ ነው።

    ይኽን የመቃወሚያ ነጥብ ይዘው የሚከራከሩ ተቃዋሚዎች ሙግታቸውን በሁለት መንገድ ያቀርባሉ፦

   ➊.1 ፦ የመጀመሪያው የግሪኩን ሰዋሰው አወቃቀር በመጠቀም  ሲሆን
   ➊.2፦ ሌላኛው ደግሞ " አብ በኢየሱስ ውስጥ ነበርና አምላኬ ሲል አብን የሚያመለክት ነው" የሚለው ነው።
   ነጥብ አንድን እኒህን ሁለት ሙግቶች በመመልከት እንጨርሳለን፦

  ➊.1፦ የግሪክ ሰዋሰው ፦  የግሪክ ሰዋሰውን ጠቅሰው የሚሞግቱት ወገኖች ለሙግታቸው ሙሉውን ማንበባቸውን የሚያጠራጥረውን  የታዋቂውን የግራንቪል ሻርፕ 6ኛውን የግሪክ ሰዋሰው ሕግ ይጠቅሳሉ።  ሕጉ ይህን ይላል፦

    And as the insertion of the copulative kai between nouns of the same case, without articles, (according to the fifth rule,) denotes that the second noun expresses a different person, thing, or quality, from the preceding noun, so, likewise, the same effect attends the copulative when each of the nouns are preceded by articles.
    ይኽም ሕግ በሁለት ተመሳሳይ ሙያ ባላቸው ስሞች መካከል አያያዥ ቃል "እና " ከገባች በስሞቹ ፊት ለፊት ደግሞ አርቲክል "the" ከሌለ (በአምስተኛው ሕግ መሰረት) ሁለተኛው ስም የተለየ አካልን ያመለክታል በተመሳሳይ መልኩ ከሁለቱ ስሞች ፊት ለፊት አርቲክል " the" ቢኖርም የተለያየን አካል ያሳያል ይለናል።

    ተቃዋሚዎች እንግዲህ የያዙት ይችን ብቻ ነው። ነገር ግን ይህን ሕግ የፃፈው እራሱ ግራንቪል ሻርፕ ስድስተኛው ህግ የማይሰራበትን ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል ፦

   1፦ አውዱ ግልፅ ካደረገው
    2፦ በሁለቱም ስሞች ፊት ለፊት ለአንድ አካል መሆኑን የሚያመለክት ካለ እነዛ ስሞች አንድ አካል ያመለክታሉ። ለዚህም ምሳሌዎችን ያስቀምጥልናል፦
     “አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።”— ራእይ 22፥13

    #εγώ_το Α #και_το Ω αρχή και τέλος ο πρώτος και ο έσχατος

      ለምሳሌ ይኽንን የራዕይ ክፍል ብንመለከት አልፋ እና ኦሜጋ የሚሉት በ the(το) የተያያዙ ሲሆን ሁለቱም "እና(και)" በምትለው ቃል ተለያይተዋል ይኽም የስድስተኛውን ሕግ የሚያሟላ ነው። ግን አልፋ የሚለው አንድ አካል ፤ ኦሜጋ የሚለው ደግሞ ሌላን የሚያመለክት አንደለም ምክንያቱም የ exception ሕጉን ያሟላል።

    1፦ አውዱ ስለ ኢየሱስ እንደሚናገር ግልፅ ነው።
   2፦ "እኔ ነኝ" የምትለው ሀረግ አልፋ እና ኦሜጋ የተባለው አንድ አካል መሆኑን ያመለክታል። በዚሁ ሂሳብ ዮሐ 20:28ንም እንመልከተው፦

    και απεκρίθη ο Θωμάς και είπεν #αυτώ ο κύριός μου και ο θεός μου

1፦ አውዱ ስንመለከት ከቁጥር 24 ጀምሮ ስለ ኢየሱስ እተናገረ የመጣ ነውና "አውዱ ግልፅ ካደረገው" የሚለውን ያሟላል።

2፦ αυτώ(አለው) የምትለው ቃል መልሱ ለኢየሱስ እንደሆነ ግልፅ ያደርገዋል። ይኽም የሚገለፀው አካል አንድ አካል መሆኑን ለማመልከት ማሟላት የሚገባውን ቅድመ ሁኔታ ያሟላል ማለት ነው። ስለዚህ ቶማስ " ጌታዬ አምላኬም" ሲል ኢየሱስን እየገለፀ እንደሆነ ግልፅ ያደርግልናል።  ወደ ሁለተኛው ሙግት እንለፍ፦

  ➊.2፦ "ቶማስ ግን ኢየሱስን ዳሶ ባየው ጊዜ
<ጌታዬ አምላኬም> አለ። አሁን ቶማስ ጌታን ብቻ ሳይሆን ያየው አምላክንም ጭምር ነው!! አምላክን ያየው እንዴት ነው??? አምላክ በኢየሱስ ባደረገው ሥራ ይታያል። “ # ክርስቶስንም # ከሙታን_ሲያስነሣው_በክርስቶስ_ባደረገው_ሥራ_የብርታቱ_ጉልበት_ይታያል፤” "

   ይኽን ክስ በቀላሉ እንመልከተው፦ said to him  ተብሎ የተተረጎመው ሀረግ "#είπεν_αυτώ (eipon auto) " በዮሐንስ ወንጌል ያለውን አገልግሎት ስንመለተከት ቀደም ብሎ ለተናገረው አካል የሚሰጥን መልስ የሚያመለክተን ነው። ምሳሌ እንጥቀስ፦

   “አይሁድም፦ ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? #አሉት(eipon auton)።”  — ዮሐንስ 8፥57

    "አሉት " የሚለው ቃል ኢየሱስ ቀድሞ ለተናገረው እንደ መልስ ነው። ይኽም በንግግሩ ተደራሽ የሚሆነው ቀድሞ የተናገረው አካል እንደሆነ ያሳየናል።

   👇 ይኽንንም ጨምራችሁ ተመልከቱት፦

   “በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ። ይህንም ብሎ፦ ተከተለኝ አለው(eipon auto)።”— ዮሐንስ 21፥19

   ከእነዚህ ጥቅሶች ማንም በቀላሉ እንደሚረዳው " አለው " ወይንም "አሉት" ሲል ቀድሞ ይናገር የነበረውን አካል እንጂ ሌላን አካል አይደለም። በዚሁ መሰረት

ቶማስም "ጌታዬ አምላኬም" ብሎ ሲመልስለት ቀድሞ ተናግሮት የነበረውን ኢየሱስን እንጂ አብን አይደለም።

    ከዚህ ባለፈ " ጌታዬ አምላኬም" የሚለው ለአንድ አካል ሲውል በብሉይም በአድስም አይተናል።

   “#አምላኬ_ጌታዬም፥ ወደ ፍርዴ ተነሥ፥ አቤቱ፥ ፍርዴን አድምጥ።” — መዝሙር 35፥23

    “#ጌታችንና_አምላካችን ሆይ፤ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤ በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤ ሆነዋልምና።”— ራእይ 4፥11

    እኒህ ሁለት ጥቅሶች ስለ አንድ አካል እንደሚናገሩ ማንም ይስማማል እና ኢየሱስ ላይ ሲሆን "ጌታ ለኢየሱስ ፤ አምላክ ለአብ " የሚለው ከየት መጣ?  ይኽ እንግዲህ ላለማመን ሰበብ መደርደርን የሚያመለክት ነው።

ነጥብ   ➋፦ ቶማስ " ጌታዬ አምላኬ" ሲል በመገረም ስሜት እንጂ ኢየሱስን አምላኬ እያለ አይደለም።

     ይኽን ሙግት የሚያነሱት ሰዎች " ቶማስ ጌታዬና አምላኬ ሲል ልክ አሁን በዘመናችን ስንደነግጥ የምንጠቀመውን አይነት እንጂ ኢየሱስን አምላክ እያለ አይደለም " የሚል ነው። በዚህ ሙግት ውስጥ ሁለት ድክመቶች አሉት፦

  1፦ የመጀመሪያው የአይሁዶችን ባህል ካለማወቅ የመጣ ነው። አይሁዶች የሚመሩበት የብሉይ ኪዳን መፅሀፍ የእግዚአብሔርን ስም በምን መልኩ መጠቀም እንደሚገባ ይኽን ይላል፦

     “የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና።”— ዘዳግም 5፥11

ቶማስ ደግሞ ከአይሁድ ወገን የነበረ ሀዋርያ ነው። አይሁዶች በከንቱ አትጥሩ እየተባሉ ቶማስ በድንጋጤ አምላኬ አለ ማለት አይሁዶችን ከመሳደብ አይተናነስም። ስለዚህም ቶማስ "ጌታዬ አምላኬም" ሲል በ exclamatory ነው የሚለው አያስኬድም።

  2፦ የሙግቱን ደካማነት የሚያሳየን ሁለተኛው ነገር ቶማስ ያንን ያለው እንኳን በድንጋጤ ነው ብለው ድርቅ ቢሉ ለዚህ ማስረጃቸው የሚሆን ኢየሱስ በነበረበት ጊዜ ድንጋጤን ወይንም መገረምን በሚገልፅ መልኩ የተፃፈን ፅሁፍ እንዲያቀርቡልን እንጠይቃለን ቅሉ ግን እንደዚህ አይነት ገለፃዎች ከአመታት በኋላ የመጡ ናቸውና ሊያቀርቡ አይችሉም። ስለዚህም ቶማስ "ጌታዬ አምላኬም" ያለው በመገረን ስሜት ነው የሚለውን ይፈርሳል ማለት ነው።

     ለዛሬ ይህን ክፍል በዚህ መልኩ አየን በቀጣይ አምስትን ያነቡ ዘንድ ጋበዝን
(ክፍል ፭ [ የሐዋርያት ስራ 20:28 ] ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን

           ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

    ክፍል አምስት [ የሐዋርያት ስራ 20:28 ]
     ክፍል ስድስት [ ሮሜ 9:5]
     ክፍል ሰባት [
ለማንኛውም አስተያየት፦
[ ዐቃቢያነ እምነት ዘኦርቶዶክስ ]
https://t.me/akabianement

ለቴሌግራም ቻናላችን፦
[ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ]
     https://t.me/ekbetemnet

Comments

Popular posts from this blog

ዕቅበተ እምነት

ወላዲተ አምላክ

መልስ ለወሒድ ዑመር