ክፍል ፯ ቲቶ 2:13
✟ የኢየሰስ አምላክነት ከአድስ ኪዳን( ቲቶ 2፥13)
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ ፡ በወልድ ፡ በመንፈስ ቅዱስ ስም!
ሰላም ተወዳጆች እንደምን አላችሁ? እነሆ ዛሬም ለሰባት ተከታታይ ክፍላት ስናየው የነበረው የኢየሱስን አምላክነት በአድስ ኪዳን ስምነተኛ ክፍሉን ይዘን ቀርበናል። በዚህም እንደቀደሙት ክፍላት የኢየሱስን አምላክነት አስረግጠን በማሳየት የምንቋጭ ይሆናል እርሶም አብረው በምስክርነት ይቁሙ ፤ አምላክነቱን የማይቀበሉ ከሆኑም እራስዎን ይጠይቁ!።
የቀደመው ክፍል [ሮሜ 9:5]
የአህዛብ ሰባኪ የሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ሶስት ምዕራፍ ባላት ትንሽ በተባለችው በቲቶ መልእክቱ የኢየሱስን አምላክነት በማያወላዳ አገላለፅ ይገልፅልናል፦
“ይህም የተባረከ ተስፋችን የሆነውን የታላቁን የአምላካችንንና የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ በመጠባበቅ ነው፤”— ቲቶ 2፥13
ይህንን የጠራ ጥቅስ ለማፍረስ ዳገት የሆነባቸው ተቃዋሚዎች የማፍረሻ መንገድ ቢያጡ እስከዛሬ የኢየሱስን አምላክነት የሚያሳዩ ጥቅሶችን ለማፍረስ ይጠቀሙበት የነበረውን የግራንቪል ሻርፕን የሰዋሰው ሕግ መልሶ በመቃወም ይህንን ጥቅስ ለማፍረስ ይሞክራሉ።
ወደ እነርሱ ሙግት ከመግባታችን በፊት ግን እስኪ ጥቅሱ በዚህ መልኩ ለመተርጎም አውዱና የሰዋሰው ህጉ ይፈቅድልናል ወይ? የሚለውን እንመልከት
ቅዱስ ጳውሎስ በቁጥር 14 ይህን ይላል፦
“እርሱም ከክፋት ሊቤዠን መልካም የሆነውን ለማድረግ የሚተጋውን የእርሱ የሆነውን ሕዝብ ለራሱ ያነጻ ዘንድ ራሱን ስለ እኛ ሰጥቶአል።” — ቲቶ 2፥14
who gave Himself for us to redeem us from every lawless deed, and to purify for Himself a people for His own possession, zealous for good deeds. (Titus 2:14)
በዚህ ጥቅስ እንደምንመለከተው ቅዱስ ጳውሎስ ኢየሱስን "እርሱም ከክፋት ሊቤዠን.....የእርሱ የሆነውን ሕዝብ ለራሱ ያነጻ ዘንድ ራሱን ስለ እኛ ሰጥቶአል" በማለት ይገልፀዋል። እዚህ ላይ ሁለት ወሳኝ ገለፃዎች አሉ፦
የመጀመሪያው ፦ ሊቤዠን የሚለው ገለፃ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ "ሊቤዠን" ሲል ኢየሱስን በስልጣኑ አዳኝነቱን እየገለፀው ነው። ነገር ግን ብሉይ ኪዳን አዳኛችን እግዚአብሔር እንደሆነ ይናገራል፦
መዝሙር 130
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁷ በእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት፣ #በእርሱም_ዘንድ_ማዳን_አለና፣ እስራኤል ሆይ፤ በእግዚአብሔር ተስፋ አድርግ።
⁸ እርሱም እስራኤልን፣ #ከኀጢአቱ ሁሉ ያድነዋል።
በተጨማሪም በዚህ መዝሙር " ከኃጢአቱ" ተብሎ ወደ አማርኛ የተተረጎመው በሰባ ሊቃናቱ ትርጓሜ ላይ የቀረበው እና በቲቶ 2:14 "ከክፋት" ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል "ሎትሮ(ανομιών)" የሚለው ነው ይህም አዳኛችን ኢየሱስ እርሱ እግዚአብሔር መሆኑን ያሳየናል።
ሁለተኛው ቲቶ 2:14 ከሰፈረው ጥቀስ ልብ ልንለው የሚገባን "የእርሱ የሆነውን ሕዝብ" የሚለው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ የሆኑትን ህዝቦች በራሱ ሊያድናቸው ወዷል። ህዝቡም የእርሱ ተብለዋል ይህንን ገለፃ ደግሞ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ሲናገረው እናገኛለን፦
“በጣዖታቶቻቸው፣ በአስጸያፊ ምስሎቻቸው ወይም በማንኛውም ኀጢአት ራሳቸውን አያረክሱም፤ ነገር ግን እኔን በመተው ከሠሩት ኀጢአት ሁሉ አድናቸዋለሁ፤ አነጻቸዋለሁም። #እነርሱ_ሕዝቤ_ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።””— ሕዝቅኤል 37፥23
ከዚህም እኛ ኢየሱስ የኔ የሚለን ንብረቱ ስንሆን እረሱ ደግሞ እግዚአብሔር ነው።
አውዱ እንግዲህ በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች መነሻነት ኢየሱስ አዳኝም አምላክም ያደርገዋል ይህም በቁጥር 13 ላይ ኢየሱስ አምላክና መድኃኒት ተብሎ ቢገለፅ የከመፅሀፍ ውጭ ያልሆነ ገለፃ መሆኑን ያሳየናል።
⭕ እስኪ ደግሞ ግራንቪል ሻርፕ ከሚባለው የግሪክ ስዋሰው ህግ አንፃር ቲቶ 2:13 እንመልከተው።
προσδεχόμενοι την μακαρίαν ελπίδα και επιφάνειαν της δόξης #του_μεγάλου_θεού_και_σωτήρος ημών Ιησού χριστού
የቲቶ 2:13 የግሪክ አወቃቀሩን ስናየው μεγάλου θεού ከሚለው በፊት ውስን መስተኣምር του ያለች ሲሆን እና( και) ከምትለው አያያዥ ቃል በኋላ ግን ምንም አይነት ውስን መስተኣምር የለም ስለዚህም ይህ ጥቅስ ሊዳኝ የሚችለው በመጀመሪያው የግራንቪል ሻርፕ ህግ መሰረት ነው ማለት ነው። ህጉ እንዲህ ይላል፦
📌 When the copulative kai connects two nouns of the same case, [viz. nouns (either substantive or adjective, or participles) of personal description respecting office, dignity, affinity, or connection, and attributes, properties, or qualities, good or ill,] if the article #ho, or any of its cases, precedes the first of the said nouns or participles, and is not repeated before the second noun or participle, the latter always relates to the same person that is expressed or described by the first noun or participle: i.e. it denotes farther description of the first-named person,
በዚህም ህግ መሰረት ሁለት ተመሳሳይ ሙያ ያላቸው ስሞች በ "እና" በሚለው የግሪክ አያያዥ ቃል ከተጣመሩና የመጀመሪያው ስም ላይ ውስን መስተኣምር ኖሮ ሁለተኛው ስም ላይ ካልተደገመ (ከሌለ) ሁለተኛው ስም በመጀመሪያው ስም የተገለፀውን አካል የሚያመለክት ነው የሚል ነው።
ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ በርካታ ጥቅሶችን ማቅረብ ይቻላል። ለምሳሌ ጥቂት እንመልከት፦
“በምን ሁኔታ እንዳለሁና ምን እንደማደርግ ታውቁ ዘንድ ተወዳጅ #ወንድምና በጌታ ታማኝ #አገልጋይ የሆነው ቲኪቆስ ሁሉንም ነገር ይነግራችኋል።”— ኤፌሶን 6፥21
Tychicus, the dear brother and faithful servant in the Lord,
#ο αγαπητός #αδελφός_και πιστός #διάκονος εν κυρίω
የእምነታችን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት የሆነውን ኢየሱስን አስቡ።”— ዕብራውያን 3፥1
fix your thoughts on Jesus, #the_apostle_and high #priest whom we confess.
#τον_απόστολον_και_αρχιερέα της ομολογίας ημών χριστόν Ιησούν
ከእነዚህ ከሁለቱ በተጨማሪ ኤፌ 1:3 ፣ ፊልጶ 4:20 ፣ ቆላ 4:7 እና ሌሎችም እጅግ ብዙ ጥቅሶችን ማንሳት እንችላለን።ለማነፃፀር ግን እኒህ በቂ ናችው። ከእነዚህ ጥቅሶች በመነሳት ቅዱስ ጳውሎስ "አምላካችን እና መድኃኒታችን" ሲል አንድ አካል ኢየሱስን እየገለፀ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም።
ቲቶ 2:13 በዚህ መልኩ መተርጎም እንዳለበት ወይንም አንድ አካል ስለማሳየቱ ተጨማሪ ግንዛቤን የሚፈጥርልን በሰዋሰው አወቃቀሩ ከቲቶ 2:13 አንድ የሆነ ገለፃን በ 2ኛ ጴጥ 1:1 ላይ እናገኛለን፦
“የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይና ሐዋርያ ስምዖን ጴጥሮስ፤ #በአምላካችንና_በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ በኩል እንደ ተቀበልነው ዐይነት ክቡር እምነት ለተቀበሉት፤” — 2ኛ ጴጥሮስ 1፥1
ቅዱስ ጴጥሮስ ከቲቶ 2:13 ጋር ተመሳሳይ አወቃቀርን የሚጠቀመው በዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ አይደለም በዚች በትንሽ መልዕክቱ ላይ በበርካታ ቦታዎች ላይ ደጋግሞታል። ይህን አወቃቀር የተጠቀመባቸው ጥቅሶች ግን ሁሉም አንድ አካልን የሚያመለክቱ ናቸው፦
ለምሳሌ አንድ እንመልከት ተወዳጆች፦
“#ጌታችንንና_አዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ እንደ ገና ተጠላልፈው ቢሸነፉ ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታቸው የከፋ ይሆንባቸዋል።”— 2ኛ ጴጥሮስ 2፥20
#του_κυρίου_και_σωτήρος Ιησού χριστού
በዚህ ላይ ቅዱስ ጴጥሮስ በ 1:1 ላይ ካለው ተመሳሳይ የሰዋሰው አደረጃጀት የተጠቀመ ቢሆንም "ጌታችንንና አዳኛችንን " ሲል ግን ሁለት አካል ነው የሚያመለክተው ብሎ የሚሞግት ማንም የለም። ሁሉም በአንድ ድምፅ ኢየሱስን እየገለፀ እንደሆነ ይስማማሉ። ነገር ግን ከቲቶ 2:13 ጋር ስናነፃፅረው አወቃቀሩ ሁሉ አንድ ሲሆን የተቀየረውም θεού የምትለው ቃል ብቻ ናት እና ይህን 2ኛ ጴጥ 2:20 ለአንድ አካል ነው ካሉ የቲቶ 2:13 እና 2ኛ ጴጥ 1:1 ንስ ለምን በዛ መንገድ አይረዱትም? የህ የሚያሳየን ላለማመን የሚደረግን መፍጨርጨር ነው። በሰዋሰው አደረጃጀታቸው ከእነዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ በ ምዕራፍ 3 ቁጥር 2 እና 18 ላይ መመልከት ይችላሉ።
ከአውዱና ከሰዋሰው አወቃቀሩ በመነሳት ቅዱስ ጳውሎስም ሆነ ቅዱስ ጴጥሮስ "አምላክ" ሲሉ አብን " መድኃኒት " ሲሉ ደግሞ ኢየሱስን እየገለፁ ሳይሆን ሁለቱንም ስሞች የተጠቀሙት የኢየሱስን አምላክነት ለመግለፅ እንደሆነ እንረዳለን።
አውዱና ሰዋሰው ይህ ሆኖ ሳለ ግን ተቃዋሚዎች ጥያቄን ያነሳሉ፦
ተቃዋሚዎች "የግራንቪል ሻርፕን ህግ ይዞ መሞገት ውሃ የማያነሳ ነው " ለዚህም ምክንየያታቸው ከቲቶ 2:13 በተመሳሳይ የሰዋስው አወቃቀር ቀርበው ነገር ግን ሁለት አካላትን የሚያሳዩ አሉ የሚል ነው። ነገር ግን ይህ የመጀመሪያው ህግ ሊሰራባቸው ጥቅሶቹ የሚከተሉትን ሶስት ነገሮች ካለፉ ነው፦
➊ኛ፦ ስሞቹ impersonal ወይንም አካላዊ ያልሆነን ነገር የሚያመለክቱ መሆን የለባቸውም።
➋ኛ፦ ስሙ አካላዊ የሆነ ማንነትን ቢያመለክት እንኳን የተውፅኦ ስም መሆን የለበትም ( ለምሳሌ ፦ ጳውሎስ ፣ ዮሐንስ ፣ ኢየሱስ... የመሳሰሉትን መሆን የለበትም ህጉ ሊሰራ የሚችለው በጋራ ስሞች ማለትም አባት ፣ ጌታ ፣ መድኃኒት... ወዘተ በሚሉት ላይ ነው)
➌ኛ፦ የጋራ ስም ሆነውም ነጠላ ቁጥር አመልካች መሆን ይገባቸዋል።
የመጀመሪያው የግራንቪል የሰዋሰው ህግ ምንም አይነት exception የሌለው ሲሆን አወቃቀሩ ግን እኒህን ሶስት ነገሮች ያሟላ መሆን አለበት። እስኪ ተቃዋሚዎች የሰዋሰው ህጉን ለመቃወም የሚጠቅሷቸው ጥቅሶች ከላይ ካስቀመጥናቸው ሶስት መስፈርቶች ያልፉ ይሆን? የሚለውን እንመልከት፦
❌፦ “#በሐዋርያትና_በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማእዘኑ ራስ ድንጋይም ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱ ነው፤” — ኤፌሶን 2፥20
#των_αποστόλων_και_προφητών
ቲቶ 2:13 & 2ኛ ጴጥ 1:1 ን የሚቃወሙ ሰዎች ሙግቻቸውን ምክንያታዊ ለማድረግ ሲሉ የሚጠቅሱት የመጀመሪያው ጥቅስ ይህንኑ 👆 ነው። የዚህን ጥቅስ የሰዋሰው አወቃቀር ካየነው ከቲቶ 2:13 ጋር ምንም የሚለየው የለም αποστόλων ከሚለው በፊት ውስን መስተኣምር የተጠቀመ ሲሆን προφητών ከሚለው ፊት ግን ምንም አይነት ውስን መስተኣምር የለም። " የቲቶ 2:13 አንድ አካልን ያሳያል ካላችሁ ይህ ኤፌሶን 2:20 ም አንድ አካልን ያሳያል ማለት ነውን?" በማለት ይጠይቃሉ መልሱም አጭር ነው ምንም እንኳን የሰዋሰው አደረጃጀቱ ከቲቶ 2:13 ጋር የተስማማ ቢሆንም ቅሉ ያንስቀመጥናቸው 3 መስፈርቶች ግን ማለፍ አይችልም። በኤፌ 2:20 የተጠቀሱት ሁለት ስሞች ማለትም " ሐዋርያት እና ነብያት" የሚሉት ቃሎች ብዙ ቁጥርን የሚያመለክቱ በመሆናቸው መስፈርቱን አያልፉም እና በሰዋሰው ህጉ ሊዳኙ አይችሉም።
❌➋፦ “ደግሞም ይህን ዕወቁ፤ ማንም አመንዝራ ወይም ርኩስ ወይም ስግብግብ ይኸውም ጣዖት አምላኪ #በክርስቶስና_በእግዚአብሔር_መንግሥት ርስት የለውም።” ኤፌሶን 5፥5
#του_χριστού_και_θεού
ተቃዋሚዎች ቀጥለውም ይህንን 👆 ይጠቅሳሉ አደረጃጀቱን ካየነው ከቲቶ 2:13 ም ሆነ ከ2ኛ ጴጥ 1:1 በትክክል የሚገጥም ነው። ነገር ግን ይህ ጥቅስ የተቀመጡትን ሶስት መስፈርቶች ያሟላል ወይ? የሚለውን መጠየቅ ተገቢ ነው። ጥቅሱ በእኛ አቀማመጥ መሰረት መስፈርት 1 አና 3ን ሲያሟላ ሁለተኛውን ግን ማሟላት አይችልም ምክንያቱም θεού(theos) የሚለው ስም በውስን መስተአምርም ሆነ ያለውስን መስተኣምር እንደ ተውፅኦ ስም ሆኖ ሊያገለግል ይችላልና ነው። በዚህ ተከታታይ ፅሁፋችን በብዛት እንደ ማጣቀሻ የጠቀስነው አሜሪካዊው የግሪክ ቋንቋ ሊቅ A.T Robertson ይህንን ጥቅስ ባተመለከተ ይህንን ይላል፦
" But 👉 Sharp's rule cannot be insisted on here because theos is often definite without the article like a proper name. Paul did teach the deity of Christ and may do it here. "( Word Picture In The New Testament Vol. IV)
ከዚህም በተጨማሪ እኒሁ ሊቅ በሌላ መፅሐፋቸው ይህንን ይላሉ፦
"The word θεού , like a proper name, is freely used with and without the article. But it is "beyond comparison the most frequently in the Epistles without the article."(A Grammar of the Greek New testament in the light of historical research, pp 795)
ስለዚህም ይህ ሙግታቸው ውሃ የማያነሳ ይሆናል ማለት ነው።
ማጠቃለያ ፦ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ አምላክ ነው። ታላቅ አምላክ መባሉም ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለማበላለጥ ሳይሆን የመለኮት ሙላት በእርሱ ያለ መሆኑን ፣ በምድር አምላክ ከሚባሉት ጣኦታን የላቀ መሆኑን የሚያመለክተን ነው።
በዚህ በአንድ ፅሁፍ ሁለት ጥቀሶችን ( ቲቶ 2:13 & 2ኛ ጴጥ 1:1) ጌታ በፈቀደልን መጠን ይህንን በመሰለ መልኩ አዬን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
_______________________
ለማንኛውም አስተያየት፦
[ ዐቃቢያነ እምነት ዘኦርቶዶክስ ]
https://t.me/akabianement
ለቴሌግራም ቻናላችን፦
[ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ]
https://t.me/ekbetemnet
Comments
Post a Comment