ክፍ. ፮ የኢየሰስ አምላክነት ከአድስ ኪዳን( ሮሜ 9:5)

 

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ ፡ በወልድ ፡ በመንፈስ ቅዱስ ስም!


    ሰላም ለእናንተ ተወዳጅ የቻናላችን ቤተሰቦች እንምን አላችሁ? "እግዚአብሔር ይመስገን" ብለን እንድናመሰግነው የፈቀደልን ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን!።
ለቀደመው ክፍል ፭[ የሐዋርያት ስራ. 20:28 ]

      ዛሬም የጀመርነውን የኢየሱስን አምላክነት ከአድስ ኪዳን ዳሰሳችንን እንቀጥላለን። በ5  ክፍላትን ከዮሐንስ ወንጌልና ከሐዋርያት ስራ ተመልክተናል ዛሬ ደግሞ የብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ የመጀመሪያ መልእክት ወደሖነው ወደ  ሮሜ ገብተን ምዕራፍ 9 ቁጥር 5 ን እንመለከታለን። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሁን!

     ኢየሱስ ከዐረገ በኋላ ለእርሱ ተገልጦ ሐዋርያ ያደረገው ፤ የአህዛብ ሰባኪ የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቶቹ ላይ የኢየሱስን አምላክነት በተደጋጋሚ አውጇል ከእነዛም መካከል  በዚህ አሁን የምናዬው ሮሜ 9:5 አንዱ ነው። ይኽንን ጥቅስ በሌላ ፅሁፍ የዳሰስነው ሲሆን [ የቀደመውን ፅሁፍ በዚህ ይመልከቱ https://t.me/ekbetemnet/21] በዚህ ፅሁፋችን ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ሙግትን ጌታ በፈቀደ መጠን እናፈርሳለን።

     “አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን።”  — ሮሜ 9፥5

    ይኽንን ጥቅስ ለማጣጣል የሚሞክሩ ተቃዋሚዎች የግሪኩን ፅሁፍ ስርዓተ-ነጥብ አልባነት መነሻ በማድረግ " ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘላለም የተመሰገነ አምላክ ነው" የሚለው ለአብ እንጂ ለኢየሱስ ሊውል አይገባውም ይላሉ።

    የግሪኩ ፅሁፍ ስርዓተ - ነጥብ አልባነት እሙን ነው። ማንኛውም የአድስ ኪዳን መፅሀፍ ሲፃፍ ስርዓተ ነጥብን እየተጠቀሙ አልነበረም። ይኽም ከግሪኩ ወደ ሌላ ቋንቋ በሚተረጎምበት ጊዜ ሰዋሰው እና አውዱ እየታየ እንዲተረጎም ያደርገዋል። ስለዚህም የተነሳንበትን ጥቅስ ለአብ ወይንስ ለኢየሱስ የሚለውን በአውዱና በሰዋሰው መመልከት ያሻል።

     "ων οι πατέρες και εξ ων ο χριστός το κατά σάρκα ο ων επί πάντων θεός ευλογητός εις τους αιώνας αμήν"
    “to them belong the patriarchs, and from them, according to the flesh, comes the Messiah, who is over all, God blessed forever. Amen.” — Rom 9:5

  እስኪ እኛም ይኽ ጥቅስ የኢየሱስን አምላክነት የሚያሳይ ነው የምንልበትን ምክንያት በነጥብ በማቅረብ ምልከታችንን እንጀምር ፦

📌 ነጥብ 1፦ ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ በሮሜ 9:5  ስለ ኢየሱስ ሰውነት በመናገር ከጀመረ በኋላ ስለ አምላክነቱ በመናገር ይጨርሳል። ይህ ጥቅስ ስለ ኢየሱስ አምላክነት ያሳያል  ለማለት ከዚህ ተመሳሳይነት ያለውን አወቃቀር የያዘ ጥቅስ ማግኘት በቂ ነው ይኽን ደግሞ በዚሁ  መልእክት ውስጥ እናገኛለን ፦

³ ወንጌሉም ስለ ልጁ፣ #በሥጋ_ከዳዊት_ዘር_ስለ_ሆነ፣
⁴ በቅድስና መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በኀይል ስለ ተገለጠው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።(ሮሜ 1:3-4)

  👆 በዚህ ጥቅስ ላይ ከሮሜ 9:5 ጋር ተመሳሳይ የሆነ አካሄድን እናገኛለን ቅዱስ ጳውሎስ በሁለቱም ጥቅስ በመጀመሪያ ስለ ኢየሱስ ሰውነት ከተናገረ በኋላ ስለ አምላክነቱ ያውጃል።  የ ሮሜ 1:3-4  ለኢየሱስ ሳይሆን ለአብ ነው እንደማንል ሁሉ ይህም ሮሜ 9:5 ለአብ ነው እንድንል አይፈቅድልንም።

📌   #ነጥብ 2፦ who is (ο ων) የሚለው ገለፃ  " በስጋ መጣ" ከሚለው ገለፃ ጋር የሚስማማ ነው።  "በስጋ የመጣ...  እርሱም" ቢባል የተፈጥሮ አደራደሩን የጠበቀ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ο ων የሚለው ሀረግ በመፅሀፍ ያለውን አገልግሎት ስንመለከት ቀድሞ እየተገለፀ የነበረን አካል ለማመልከት ይውላል። ይኽንንም ከራሱ ከጳውሎስ መልእክት እንይ፦

      ο θεός και πατήρ του κυρίου Ιησού χριστού οίδεν #ο_ων ευλογητός εις τους αιώνας ότι ου ψεύδομαι
     
      “The God and Father of the Lord Jesus, #who_is to be praised forever, knows that I am not lying.”— 2Cor 11:31

    በዚህ ጥቅስ እንደምንመለከተው " who is" የሚለው ቀድሞ ይነገርለት የነበረውን አካል ይገልፃል ጥቅሱ ስለ አብ በመናገር ይጀምራል "who is" የሚለው ደግሞ አብን የሚገልፅ ይሆናል ማለት ነው። ይህንን ወደተነሳንበት ጥቅስ ስናመጣው ሮሜ 9:5 ስለ ኢየሱስ በመናገር ይጀምራል  ስለዚህም "እርሱም " የሚለው ኢየሱስን የሚያመለክት ይሆናል ማለት ነው። "እርሱም" የሚለው ኢየሱስን አመለከተ ማለት ደግሞ ከዚህ ቃል ቀጥለው ያለው ዓ.ነገር ማለትም "ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው" የሚለው ኢየሱስን ያመለክታል ማለት ነው።

📌  #ነጥብ 3፦  ይህ ሮሜ 9:5 ጥቅስ ለአብ አይደለም እንዲንል የሚያደርገን ዋናው ምክንያት "የተባረከ (ευλογητός)" የሚለው ቃል አንፃራዊ መገኛ ነው። በመፅሀፍ ቅዱስ በብሉይ ሰባ ሊቃናቱ ትርኗሜም ሆነ በአድስ ኪዳን ላይ "blessed" የሚለውን ቃል አንፃራዊ መገኛ ስንመለከት ለአብ በሚያገለግልበት ጊዜ "አምላክ (θεός)" ከሚለው ቃል በመቅደም የሚመጣ ነው። በምሳሌ እንመልከተው፦

    και #ευλογητός_ο_θεός ο υψίστος ος παρέδωκε τους εχθρούς σου υποχειρίους σοι και έδωκεν αυτώ Άβραμ δεκάτην από πάντων   (ዘፍጥረት 14:20)

     #ευλογητός_ο_θεός και πατήρ του κυρίου ημών Ιησού χριστού ο πατήρ των οικτιρμών και θεός πάσης παρακλήσεως   (2 ቆሮንቶስ 1:3)

    ከእነዚህ ሁለት ጥቅሶች በቀላሉ ማየት እንደምንችለው ευλογητός የሚለው ቃል ከ θεός በፊት የሚመጣ እንጂ እርሱን የሚከተል አይደለም። የሮሜ 9:5ን ግን ስንመለከተው በተቃራኒው θεός የሚለው ከ ευλογητός ይቀድማል፦

      ων οι πατέρες και εξ ων ο χριστός το κατά σάρκα ο ων επί πάντων #θεός_ευλογητός εις τους αιώνας αμήν  (ሮሜ 9:5)

    ይኽም ለአብ ለማሳየት ሲውል የሚቀመጥበትን አወቃቀር የጠበቀ አይደለምና ለአብ ሊሆን አይችልም።

    ስለዚህም ከእነዚህ ከሶስት ቀላል ምክንያቶች የምንረዳው  ጥቅሱ ስለ ኢየሱስ አምላክነት የሚናገር ነው ማለት ነው።

   እስኪ ደግሞ ተቃዋሚዎች ኢየሱስን ሊገልፅ አይችልም የሚሉበትን ምክንያት እንመልከት፦

❌ #ነጥብ ➊፦ " ኢየሱስ በሐዋርያቶቹ አንዴም ቢሆን 'ከሁሉ የበላይ' አልተባለምና ጥቅሱ ኢየሱስን ሊገልፅ አይችልም" ይላሉ

    ተብሏል? አልተባለም? የሚለውን ከመመልከታችን በፊት ይህ አጠራር ይገባዋል ወይንስ አይገባውም? የሚለውን እስኪ እንይ፦

በመጀመሪያም "ከሁሉ የበላይ" የሚለውን ሀረግ እናጢነው። "ከሁሉ በላይ"ነት በምን ይገለፃል? ስንል ከየትኛውም ፍጥረት  የላቀ ፣ የበለጠ ስልጣን ወይንም ሀይል ያለው ፣ የበታቾቹን የሚመራ በሚሉት ይገለጻል ። ኢየሱስ ይኽን ያሟላ ይሆን? በሚገባ!

   መፅሀፍ እኛን የፈጠረ እርሱ እንደሆነ ይናገራሉ ፦

    “ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም።” — ዮሐንስ 1፥3

     “ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለ ሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።”— ቆላስይስ 1፥16

     እኛን የፈጠረ እኛ ላይ ስልጣን አይኖረው ይሆን? የማይሆን ነገር ነው እኛ የእጆቹ ስራ ነንና በእኛ ላይ ሙሉ ስልጣን አለው።

ቅዱስ መፅሀፍ ኢየሱስ የገዢነት እና የስልጣን ሁሉ የበላይ መሆኑን ይናገራል፦

    “እናንተም #የገዥነትና_የሥልጣን_ሁሉ_ራስ በሆነው በክርስቶስ ሙሉ ሆናችኋል።” — ቆላስይስ 2፥10

  ከዚህም በተጨማሪ የሰዎች ሁሉ ራስ ተብሏል፦

   “ነገር ግን ይህን እንድታውቁ እወዳለሁ፤ #የወንድ_ሁሉ_ራስ_ክርስቶስ_ነው፤ የሴትም ራስ ወንድ ነው፤ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው።”— 1ኛ ቆሮንቶስ 11፥3

    ከእነዚህ ቀላል ማሳያዎች  ኢየሱስ ከሁሉ በላይ መባሉ የሚገባው መባሉ የሚገባው እንደሆነ እንረዳለን።

    በቀጥታ የተባለበትስ ይኖር ይሆን? በሚገባ አለ፦

⁹ 👉“ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ። … ¹² በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ልዩነት የለም፤ #አንዱ_ጌታ_የሁሉ_ጌታ_ነውና፤ የሚለምኑትንም አብዝቶ ይባርካል( ሮሜ 10:9,12)
   “For there is no difference between the Jew and the Greek: for the same #Lord_over_all is rich unto all that call upon him.”— Romans 10:12

  ❌ ነጥብ ➋፦ " ጳውሎስ ኢየሱስን አምላክ ብሎት አያውቅም"

  ይኽ ጭፍን ጥላቻ የመዘዘው ክስ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ቅዱስ ጳውሎስ ኢየሱስን "አምላክ" ብሎ በተደጋጋሚ ገልፆታል

    “ለራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ።”— ሐዋርያት 20፥28

    “ይህም የተባረከ ተስፋችን የሆነውን የታላቁን የአምላካችንንና የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ በመጠባበቅ ነው፤”  — ቲቶ 2፥13

   ስለዚህም ይኽ ክስ ከንቱ ውንጀላ ብቻ ሁኖ ይቀራል ማለት ነው። ተቃዋሚዎችም የኢየሱስን አምላክነት አያሳይም ብለው የሚያቀርቡት ሙግት ውሃ የማይቋጥር ይሆናል።

    ማጠቃለያ ፦ ምንም እንኳን በጥንታዊያን እደ ክታባት ላይ ስርዓተ - ነጥብ ባይኖርም ይህ ሮሜ 9:5 የኢየሱስን አምላክነት በሚገባ የሚገልፅ ነው። ስርዓተ-ነጥብ በሌለበት ጊዜ የነበሩ ደጋግ የቤተክርስቲያን አባቶች የተረዱትም በዚሁ መልኩ ነው፦

   Paul, when writing to the Romans, has explained this very point: . . . .   And again, writing to the Romans about Israel, he says: “Whose are the fathers, and from whom is Christ according to the flesh, who is God over all, blessed for ever.” [ st. Irenaeus : against heresies,  book 3, chapter 16.  ANF, vo.1, pp 1114]

    I will therefore not speak of gods at all, nor of lords, but I shall follow the apostle; so that if the Father and the Son, are alike to be invoked, I shall call the Father “God,” and invoke Jesus Christ as “Lord.” But when Christ alone (is mentioned), I shall be able to call Him “God,” as the same apostle says: “Of whom is Christ, who is over all, God blessed for ever.” [Tertullian : against praxeas . ANF, vo. 3, pp 1345]
 
     ለዘመነ ሐዋርያት ቅርብ የነበሩት አባቶች ሮሜ 9:5 የኢየሱስን አምላክነት እንደሚገልፅ እንዲህ ይመሰክራሉ።እኛም የእነዚህን ደጋግ አባቶች ምስክርነት ይዘን ጥቅሱ የኢየሱስን አምላክነት ይገልፃል እንላለን። ለዛሬ ይህንን አየን በቀጣይ በሌላ ጥቅስ እስክንገናኝ ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን!
________________________
         ክፍል ሰባት [ ቆላስይስ 1:15 ]
         ክፍል ስምንት [ ታላቁ አምላክ ]
_______________________
ለማንኛውም አስተያየት፦
[ ዐቃቢያነ እምነት ዘኦርቶዶክስ ]
https://t.me/akabianement

ለቴሌግራም ቻናላችን፦
[ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ]
     https://t.me/ekbetemnet

Comments

Popular posts from this blog

ዕቅበተ እምነት

ወላዲተ አምላክ

መልስ ለወሒድ ዑመር