አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ነው። ክፍ. 3
አብ ስም በወልድ ስም በመንፈስ ቅዱስ ስም አንድ አምላክ አሜን!
=>>>[ በክፍል ፪ ] ጽሁፋችን ጽሁፍ ሙስሊሞች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ይሰጣቹኃል ያላቸው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ብለው ለሚያቀርቧቸው ሶስት ሙግቶች በቂ መልስ ተመልክተናል። በዚህ ጽሁፍ ከባለፈው የቀረ አንድ የሙስሊሞች ሙግት ተመልክተን መልስ እንሰጣለን። በዛውም ማጠቃለያ ሀሳቦችን እናሰፍራለን!
=>>>የሙስሊሞች (ሙግት-4)
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አጽናኙ " እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤"
(የዮሐንስ ወንጌል 16:8) ተብሎ ተነግሮለታል። መንፈስ ቅዱስ ከላይ የተጠቀሱትን ወቀሳዎች ሲያደርግ በተጨባጭ ታይቶ አይታወቅም። ስለዚህ አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ሊሆን አይችልም።
=>>>ምላሽ (ቁጥር-4)
ሙስሊሞች ስለ መንፈስ ቅዱስ ያላቸው እውቀት አነስተኛ እንደሆነ በዚህ ሀሳባቸው ማወቅ ይቻላል። መንፈስ ቅዱስ ተናገረ ለማለት እግዚአብሔር ቃል በቃል ሙሴን እናዳናገረው መንፈስ ቅዱስም እንደዛ መናገር ነበረበት የሚሉ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ መንፈስቅዱስ አናጋሪነት የተነገረውን በምልአት አላወቁትም ማለት ነው። በመሠረቱ መንፈስ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን በነቢያት ላይ አድሮ በወቅቱ ቃል ኪዳን የተሰጣቸውን ሕዝቦች (እስራኤላውያንን) ሲወቅስ ነበር። ምንም እንኳን ነቢያት ቢናገሩትም በነቢያት ላይ አድሮ ሲያናግራቸው የነበረው መንፈስ ቅዱስ ነው።
" ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።"(2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1:21)
በሀዲስ ኪዳንም መንፈስ ቅዱስ በወንጌል ሰባኪያን እያደረ አለምን ይወቅሳል። በብሉይ ኪዳን እስራኤልን ብቻ ከኃጢአት እንደሚለሱ ወቅሷል፣ በሀዲስ ኪዳን ግን አለምን ሁሉ ይወቅሳል። በሀዲስ ኪዳን ወንጌልን ሲያስተምሩ የነበሩትን ደቀ መዛሙርቱን ሲያናግራቸው የነበረው መንፈስ ቅዱስ ነው። ሐዋ2÷4 ፣ ሐዋ4÷81ኛተሰ1÷5 ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በተጨባጭ አለምን ሲወቅስ አልተየም የሚለው መንፈስ ቅዱስ በቤተክርስቲያን በኩል እንዴት እንደ ሚሰራ ካለማወቅ የመጣ ነው።
=>>ማጠቃለያ ሀሳቦች
አሁን ደግሞ እስቲ ጌታችን ስለ አጽናኙ የተናገራቸውን ከሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች ጋር በማዛመድ አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ምስክሮችን እንይ።
1.የመጀመሪያው ሀሳብ መንፈስ ቅዱስ ከጌታችን ወደ ሰማይ ማረግ በኃላ እንደ ሚወርድ ስለ መነገሩ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር።
" ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና።" (የዮሐንስ ወንጌል 7:39)
በዚህ ጥቅስ ላይ በክርስቶስ ለሚያምኑት መንፈስ ቅዱስ እንደ ሚሰጥ እና መንፈስ ቅዱስ የሚወርደው ክርስቶስ ኢየሱስ ከከበረ በኃላ እንደሆነ ይናገራል። ይሄን ይዘን ኢየሱስ ሁሉን ፈጽሞ ወደ ክብሩ(ጌትነቱ) እንደገባ ወደ ሚናገረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ እናምራ።
" ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው።"(የሉቃስ ወንጌል 24:26)
እንግዲህ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ፈጽሞ ወደ ክብሩ ከገባ በኃለ ይወርዳል የተባለው መንፈስ ቅዱስ በክርስቶስ ለሚያምኑት ተሰ ጠ! ሐዋ2÷4
2. በሁለተኛ ደረጃ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አጽናኙ የተናገራቸው ቅጽሎች ለደቀ መዛሙርቱ መፈጸማቸውን በመጽሐፍ ቅዱስን እናረጋግጣለን። የሚከተሉትን ጥቅሶች በማነጻጸር ይመልከቱ
=>>>አጽናኝ ይሰጣቹኃል
" ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤"(የዮሐንስ ወንጌል 14:15-16)
" በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም።"(ወደ ሮሜ ሰዎች 5:5)
=>>>አጽናኙ ይመሰክራል
" ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤"(የዮሐንስ ወንጌል 15:26)
" ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፤ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል።"
(ወደ ሮሜ ሰዎች 9:1-2)
=>>>አጽናኙ በደቀ መዛሙርቱ ውስጥ ይኖራል
" ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።"(የዮሐንስ ወንጌል 14:17)
" መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ።"(2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1:14)
=>>>በአጠቃላይ ሙስሊሞች አስቀድመው ስለ መሐመድ መላክ የተናገሩ እስላማዊ ማስረጃዎች ስለ ለሌላቸው ተብርዟል ከሚሉት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፍለጋ መጀመራቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል። ያም ቢሆን ሙግቶቻቸው በሙሉ በግድ ለመሐመድ ለመስጠት የሚደረግ ጥረት እንጂ ሚዛን የሚደፋ አይደለም። እኛ ይሰጣቹኃል የተባለው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን በማመን በውስጣችን በሚያድረው መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደሶች መሆናችንን እምነናል። ህይወት ወደ ሆነው ክርስቶስ እንዲመጡ በመንፈስ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ እንመሰክራለን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
[ ማውጫ ]
______________✝
ለማንኛውም አስተያየት፦
[ ዐቃቢያነ እምነት ዘኦርቶዶክስ ]
ለቴሌግራም ቻናላችን፦
[ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ]
Comments
Post a Comment