ምስጢረ ስላሴ ክ.፪

 ምስጢረ ሥላሴ


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ ፡ በወልድ ፡ በመንፈስ ቅዱስ ስም።

 ክፍል 2

ከዚህ ቀደም በነበሩን መርሃግብሮች

የተመለከትናቸው

ስላሴ ለምን ምስጢር መባሉን በዚህ ያግኙ

ምስጢረ ስላሴ መግቢያ

ስለ ስላሴ ምንነት በመፅሀፍ ቅዱስ መሰረት ክፍል አንድ በዚህ ያግኙ

ምስጢረ ስላሴ ክ.፪

         ዛሬ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ካለፈው ክፍል በተጨማሪ የስላሴን አስተምህሮ የሚደግፉ የመፅሀፍ ቅዱስ ክፍሎችን ከነማብራሪየቸው እና የሚሰነዘሩ ጥያቄዎች ከነመልሳቸው እንመለከታለን።

✟➫1-"... እግዚአብሔርም አለ። ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።"

(ኦሪት ዘፍጥረት 1:26)

"...እግዚአብሔር አምላክም አለ። ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።"

(ኦሪት ዘፍጥረት 2:18)

ይህ ቃል የስላሴን አስተምህሮ በጥቂቱም ቢሆን የሚደግፍ ነው። በዚህ ቃል ተነስተን እግዚአብሔር ሶስት አካል ነው ብሎ መናገር ባያስደፍረንም እግዚአብሔር ከአንድ አካል በላይ መሆኑን ይነግረናል። በ26 ላይ ሲጀምር እግዚአብሔርም #አለ(God said) ብሎ በነጠላ ቃል ይጀምራል። ይህ ቃል የሚያመለክተን  እግዚአብሔር በመናገር(በፈቃድ) አንድ መሆኑን ነው። በመቀጠልም➫ #በመልካችን፣ #እንደ_ምሳሌአችን፣ #እንፍጠር(ኦሪት ዘፍጥረት 1:26፤) እንዲሁም እንፍጠርለት(ኦሪት ዘፍጥረት 2:18፤) የሚሉት ቃላትን ስንመለከት የብዝሃነት(plurality) ምልክትን ይሰጠናል ስለዚህም እግዚአብሔር ከአንድ አካል በላይ ለመሆኑ ፍንትው ያለ ማስረጃን ይሰጠናል ማለት ነው።

በዚህ የመፅሀፍ ቅዱስ ክፍል ተነስተው የሚዘነዘሩ ጥያቄዎች፦

1-የብዝሃነት ወይም እኛ የሚለውን ቃል የተጠቀመው እራሱን ለማክበር ነው እንጅ ስላሴን ፈፅሞ አይጠቁምም!

መልስ፦ ይህ ፈፅሞ የተሳሳተ ሃሳብ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በብሉይም ይሁን በሀዲስ ኪዳን እራሱን #እኛ እያለ ያከበረበት አንቀፅ ከቶውንም የለም። እርሱ ቀድሞም የከበረ ነው መላዕክት እርሱን ለማክበር እርሱን ለማመስገን ቢፈጠሩም ቅድመ አለም የተመሰገነ የከበረ ነው።

➫"... አሁንም፥ አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ።"

(የዮሐንስ ወንጌል 17:5)

እርሱ በአምላክነቱ አስቀድሞ የከበረ ነው። እንጅ በቃላት ጨዋታ እራሱን #እኛ እያለ መቸውንም እራሱን ከፍ ሊያደርግ ሊያከብርም አይችልም። ይህን ሃሳብ ለሚያነሱት ለትዝብት አንዲት ጥያቄ እንጠይቃቸው

እግዚአብሔር #እኛ ወይም በብዝሃነት እራሱን ሲናገር እራሱን እያከበረ ከሆነ #እኔ ሲልስ እራሱን እያቃለለ ነው?ፍርድ ለህሊና!

2-እግዚአብሔር እንፍጠር ብሎ የተናገረው ለመላዕክት ነው!

///ኩፋሌ 4፥4 ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ለእኛ እንዲህ አለን፦ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።///

ይህ ጥያቄ የተሳሳተ ነው። በመፅሀፍ ቅዱስ መሰረት እግዚአብሔር ብቻውን ፍጥረቱን ሁሉ ፈጠረ እንጅ ከቶውንም የመላዕክትን እገዛ አልጠየቀም መፅሀፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ይላል፦ "... ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ። #ሁሉን_የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ #እግዚአብሔር_እኔ_ነኝ፤ #ከእኔ_ጋር_ማን_ነበረ? "

(ትንቢተ ኢሳይያስ 44:24)

      እግዚአብሔር ፍጥረቱን ሲፈጥር ለመፍጠር ከእርሱ ጋር ማንም አልነበረም ስለዚህ መላዕክትም አብረውት አልነበሩም!...ታዲያ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር መላዕክቱን እንፍጠር ብሎ #አዘዛቸው ቢሉን ከቅዱሳት መፃህፍት ጋር አይጋጩምን?..ፍርድ ለህሊና


       ከላይ እንደተነጋገርንው እንፍጠር የሚባለው መፍጠርን ገንዘቡ ያደረገን አካል ብቻ ነው። እግዚአብሔርም አለሙን ሁሉ ሲፈጥር ብቻውን ነው የፈጠረው(ለመፍጠር ከእርሱ ጋር ማንም የለም)። ታዲያ በኩፋሌ ላይ ያለው ምንድነው ብለን ብንጠይቅ መፅሀፍ ቅዱስ መልስ አለው፦

"... በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም። "

(ትንቢተ አሞጽ 3:7)

በዚህ ቃል መሰረት እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ስራውን ይነግራል። አሐዱ ስሉስ የሆነ እግዚአብሔር ለመላዕክትም የሚሰራውን ነገር እየነገራቸው ነው እንጅ በመፍጠሩ እንዲያግዙት እያዘዛቸውም ወይም እየጠየቃቸው አልነበረም። አንዱ የእግዚአብሔር አካል ለሁለቱ የስላሴ አካል ይህን እንፍጠርለት ብሏል በመንገር ደረጃ ደግሞ ይህን ጉዳይ ለመላዕክት ተናግሯል ነገር ግን በመተግበር ደረጃ ለመላዕክት ሳይሆን ለሁለቱ የስላሴ አካል ነው።


      እንግዲህ ከላይ እንደተመለከትንው በኩፋሌ ላይ መላዕክት እንፍጠር አለን ያሉት በመፍጠር ደረጃ ሳይሆን አንድን ነገር ከመተግበሩ በፊት ለሚወዳቸው እንደሚናገረው ሁሉ መናገሩ ነው። በእራሳቸው ወገን ሆነውም እንዲህ *አለን* ብለዋል። የፍጥረትን ሥራ እያዩ ለሚደነቁት መላዕክት ቀጣዩ ሥራው ምን እንደሚመስል እንደነገራቸው ብቻ ነው የሚያስረዳው።

ሲጀመር በዘፍጥረት 2:18 ላይ "አለ" እንጅ "አለን" የሚል የለም። ጸሐፊው ራሱ እግዚአብሔርን ማዕከል አርጎ ሲናገር "እግዚአብሔርም አለ" ይላል፡፡ መላዕክት የሰሙትን ሲመሰክሩ ደግም "እግዚአብሔር አለን" ተብሎ ተጽፏል። 


______________~+

✟➫2-"እግዚአብሔር አምላክም አለ። እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ...."

(ኦሪት ዘፍጥረት 3:22)

    ይህ ቃል የተነገረው አዳምና ሄዋን ካጠፉ ቡሃላ ነው። እግዚአብሔር በመጀመሪያ አዳምንና ሄዋንን እንዲህ ብሏቸው ነበረ " ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። "(ኦሪት ዘፍጥረት 2:17) ይህንም ቃል በሻረ ጊዜ እግዚአብሔር ሲገስፀው ከላይ የጠቀስንውን ቃል ተናገረ። 

የስላሴን አስተምህሮ የሚደግፈው ቃል #ከእኛ_እንደ_አንዱ ሆነ የሚለው ቃል ነው። እኛ የሚለው ቃልበከላይ እንደተመለከትነው ብዝሃነትን ያመላክታል 👉 *እንደ አንዱ* የሚለው ቃል ይበልጥ ያጠናክርልናል እንደ አንዱ ለማለት እግዚአብሔር ከአንድ አካል በላይ እንደሆነ እና አዳም ከእነዛ አካላት አንዱ እንደሚሆን ያመላክታል።

___________~+

✟➫3-(ኦሪት ዘፍጥረት ምዕ. 18)

----------

"... በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት። ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፤ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፥ ወደ ምድርም ሰገደ፥ እንዲህም አለ። 


     ይህ ቃል ከቁጥር አንድ ጀምረን ስንመለከተው እግዚአብሔር ለአብርሃም እንደተገለጠለት ያመላክታል። በቁጥር ሁለትም ላይ የተገለጠውን እግዚአብሔር ለማየት አይኑን ሲያነሳ ሶስት ሰዎች እንደተመለከተ ይነግረናል፤ ወድቆም ሰገደ(ቁ. 3) 

ምንባባችሁን እስከ ምዕ. 19 ቀጥሉ።


     ስለ ስላሴ እንዴት ያብራራል ልትሉኝ ትችላላችሁ! እስኪ አብረን እንመልከተው🙏

ሳራ ወዴት ናት!...

" #እነርሱም። ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? አሉት። እርሱም። በድንኳኑ ውስጥ ናት አላቸው።"

(ኦሪት ዘፍጥረት 18:9)ይህን ጥያቄ የጠየቁት ሶስቱም ሰዎች ነበሩ ይህንም ለማወቅ #እነርሱም ብሎ ስለሚጀምር እና አሉት ብሎ ስለሚያጠናቅቅ ለማወቅ አያዳግትም። መልሱንም ለሶስቱም ነው የመለሰው። ነገር ግን እግዚአብሔር  መለሰ እንዲህም አለ " እርሱም። የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች አለ። ሣራም በድንኳን ደጃፍ በስተ ኋላው ሳለች ይህንን ሰማች።"(ኦሪት ዘፍጥረት 18:10) አብርሃም መልሱን የመለሰው ለሶስቱም ሰዎች ነበር ነገር ግን ከላይ እግዚአብሔር ተገለጠ ተብሎ ሶስት ሰው እንደታየው ሁሉ በዚህም ክፍል አብርሃም ለሶስቱም ሰዎች መልስ ሰጥቶ በአንድነት እግዚአብሔር ድጋሜ መልስ ሲሰጠው እንመለከታለን። ከዚህም ሶስትነት እና አንድነትን እንመለከታለን። በተጨማሪም እነዚህ ተገለጡ የተባሉት ሶስት አካላት(በሶስት ሰዎች የተመሰሉት መላዕክት) ለየሽቻ እግዚአብሄር እንደተባሉ በቀጣይነት እንመልከት።


(ኦሪት ዘፍጥረት ምዕ. 18:20-22)

"... እግዚአብሔርም አለ። የሰዶምና የገሞራ ጩኸት እጅግ በዝቶአልና፥ ኃጢአታቸውም እጅግ ከብዳለችና፥ እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደ ሆነ #ወርጄ_አያለሁ፤ እንዲሁም ባይሆን አውቃለሁ።

በዚህ ቦታ ላይ እግዚአብሔር ወደ ሰዶም እንደሚወርድ ይናገራል።(ቁ.21) ስለዚህ እግዚአብሔር ወደ ሁለቱ ከተሞች እንዲህ ወረደ "ሰዎቹም ከዚያ ፊታቸውን አቀኑ፥ #ወደ_ሰዶምም_ሄዱ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት ገና ቆሞ ነበር።"(ኦሪት ዘፍጥረት 18:22)  ተገለጠ የተባለው እግዚአብሔር ነው የተገለጠውም ሶስት ሰዎችን የሚመስሉ መላዕክትን በመምሰል ነበረ።(ቁ.2) ነገር ግን በዚህ ስፍራ (ቁ.22) ሁለቱ ሰዎች የተባሉት ሲሄዱ አንድ አካል መቅረቱን እንመልከት እርሱም እግዚአብሔር ተባለ። ስለዚህ በዚህ ስፍራ ላይ ከስላሴ አካላት አንዱ ከአብርሃም ጋር እንደቀረ እንመለታለን።


     እነዚህ የሄዱት ሰዎችም በምዕ. 19 ላይ መላዕክት ተባሉ ይህ የሚያመላክተን በሰው አምሳልና በመላዕክት አምሳል የተገለጡ አካላት መሆናቸውን ነው።

"...ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ፤ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ፤ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ፥ አላቸውም። "

(ኦሪት ዘፍጥረት 19:1)

     የሰዶምና የገሞራ አጥፊ እግዚአብሔር እንደሆነ በቁ. 21 ላይ ተገልጿል። ነገር ግን መላዕክቱ የተባሉት ሁለት ሰዎች ይህችን ከተማ እንደሚያጠፏት ይናገራሉ ይህ የሚያመለክተው እነዚህ መላዕክት የተባሉ አካላት ከስላሴ አካላት ውስጥ እንደሆኑ ነው።

"... #እኛ_ይህን_ስፍራ_እናጠፋለንና፥ ጩኸታቸው በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ሆኖአልና፤ #እናጠፋውም_ዘንድ_እግዚአብሔር_ሰድዶናል።"

(ኦሪት ዘፍጥረት 19:13) ከዚህም በመቀጠል "... እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፤"

(ኦሪት ዘፍጥረት 19:24) ይለናል። አጠፋለሁ አለ የተባለ እግዚአብሔር ነው(18:21) ሁለቱ አካላትም እናጠፋለን ብለዋል(19:13) ከእነዚህ ከወረዱት ሁለት አካላት አንዱ እግዚአብሔር ከእግዚአብሔር ዘንድ እሳትና ዲን አዝንቦ ሰዶምን አጠፋ።

   “ሰዶምንና ገሞራን በአጠገባቸውም የነበሩትን ከተምች 👉#እግዚአብሔር እንደ ገለበጣቸው፥ #ይላል #እግዚአብሔር፥ እንዲሁ ሰው በዚያ አይቀመጥም የሰውም ልጅ አይኖርባትም።”

  — ኤርምያስ 50፥40

አንዱ አካል አንዱን ሲናገር በዚህም እንመለከታለን!...የተገለጠው ሶስት አካል ነው፤ ሶስቱም አካላት በአንድነት እግዚአብሔር ተብለዋል። በተናጠልም እግዚአብሔር ተብለዋል ይህ የሚያሳየን በዮሐንስ ወንጌል 1:1  "በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።" በዚህ ቦታ ላይ ቃል እግዚአብሔር  ተብሏል ቃል የነበረበትም አካል እግዚአብሔር ተብሏል። እንደየ አውዱ የስላሴ አካላት በተናጠልም ቢሆን እግዚአብሔር ይባላሉ።

ማጠቃለያ፦ የተገለጠው እግዚአብሔር ነው፤ አብርሃም ያየው ሶስት ሰዎችን ነው። አብርሃምም ለተገለጠው ለእግዚአብሔር ስግደትን ሰግዷል። ሁሉም አካላት በዚህ situationንም በተናጠልም እግዚአብሔር ተብለዋል። ስለዚህ አንድ አምላክ በሶስት አካላት ተጓልጧል።


✟➫5-" ወደ እኔ ቅረቡ ይህንም ስሙ፤ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስውር አልተናገርሁም፤ ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ፥ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል።"

(ትንቢተ ኢሳይያስ 48:16)


     በዚህ ቃል መሰረት አንድ አካል 👉""ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል።"" ሲል ይደመጣል። ስለ ስላሴ ከማብራራታችን በፊት #ተላኪው አካል ማነው?

     ይህን የትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 48ን ከመጀመሪያው ጀምረን ስናነበው እግዚአብሔር ህዝቡን ከባቢሎን በማውጣት ያደረገውን ምህረት እንመለከታለን ከቁ1 ጀምረን እያነበብን ስንወርድ በዚህ ምዕራፍ የሚናገረው አካል(በቁጥር 16 ተላኩኝ የሚለን) መለኮታዊ ባህሪያት እንዳለው እንመልከታለን ። 

ለምሳሌ ፦ ዘላለማዊት (ቁ12)➫"... ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ነኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ።" (ትንቢተ ኢሳይያስ 48:12)

ምድርን መመስረቱ (ቁ13)➫"...እጄም ምድርን መሥርታለች ቀኜም ሰማያትን ዘርግታለች፤ በጠራኋቸው ጊዜ በአንድነት ይቆማሉ። "

(ትንቢተ ኢሳይያስ 48:13) ይገኙበታል እኒህን ከያዝን በኋላ ከላይ ወደጠቀስነው ጥቅስ እንመለስ።  ቁ16ን ስንመለከት ያ መለኮታዊ ባህሪይ ያለው አካል እራሱን በመለየት ሌላ መለኮታዊ ማንነት ያላቸውን ሁለት አካላት ሲጠቅስ እናያለን። በዚህ በቁ16 ላይ ሶስት የተለያዩ አካላትን እናገኛለን ማለት ነው።

     የመጀመሪያው ከቁጥር 1 ጀምሮ እየተናገረ የመጣው ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ "እግዚአብሔር " ተብሎ የተጠቀሰው አካል ነው  ፤ በሶስተኛነት ደግሞ " መንፈሱ" ተብሎ የተጠቀሰው የእግዚአብሔር መንፈስ። የእግዚአብሔር መንፈስ የተባለው ከእግዚአብሔር ጋር በአካል የተለየ ስለመሆኑ " እና" በሚል አያያዥ ቃል ከእግዚአብሔር ጋር የተለያየ ሲሆን  ከዛም በተጨማሪ ላኪ መሆኑ የራሱ የሆነ አካል ያለው እንደሆነ ያመለክተናል። 

      ከዚህ በመነሳት እግዚአብሄር ሶስት በስላሴነት የሚኖር ለመሆኑ እንመሰክራለን ምክንያቱም ከዚች ጥቅስ ሶስት መለኮታዊ ማንነት ያላቸውን አካላት እናገኛለና። ለዚህ ቃል ሰፊ ማብራሪያ ከዚህ ቀደም መልስ በሰጠንበት በዚህ ሊንክ ያገኛሉ፦( https://t.me/ekbetemnet/10 )

በቀጣይ ክፍል 3

የስላሴ አስተምህሮን የሚደግፉ ተጨማሪ የአዲስ ኪዳን መፃህፍት ክፍሎችና ማብራሪያቸውን ይዘን እንመጣለን!


                   6/7/2012 ተፃፈ 

         #ወስብሐት ለእግዚአብሔር

            #ወለወላዲቱ ድንግል

             #ወለመስቀሉ ክቡር

                   #ይቆየን

Comments

Popular posts from this blog

ዕቅበተ እምነት

ወላዲተ አምላክ

መልስ ለወሒድ ዑመር