ምስጢረ ሥላሴ መግቢያ
ምስጢረ ሥላሴ መግቢያ
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ ፡ በወልድ ፡ በመንፈስ ቅዱስ ስም።
ኦርቶዶክሳዊት የሆነችው ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮዎቿን ሁሉ ጠቅለል ባሉ አምስት ምስጢራት ትገልፃቸዋለች። እነዚህ ምስጢራት የቤተክርስቲያናችን አዕማዶች ሲሆን በቅደም ተከተል ስንዘረዝራቸው ፦
፨ ምስጢረ ሥላሴ
፨ ምስጢረ ሥጋዌ
፨ ምስጢረ ጥምቀት
፨ ምስጢረ ቁርባን
፨ ምስጢረ ትንሳኤ ሙታን ናቸው።
እኒህ አምስቱን በቅደም ተከተል ማመን ያለብን ሲሆን ምስጢረ ሥላሴን ሳንረዳ ምስጢረ ሥጋዌን ፡ ምስጢረ ሥጋዌን ሳንረዳ ምስጢረ ጥምቀትን መረዳት አስቸጋሪ ነገር ነው የሚሆንብን። ለዛም ነው የመማማሪያ ፅሁፋችንን ስንጀምር ከአምስቱ ምስጢራት መጀመሪያ ላይ በሚገኘው በምስጢረ ሥላሴ መጀመር ያለብን።
በዚህ በመንደርደሪያ ፅሁፍ የምስጢረ ሥላሴን አስተምህሮ የማንዳስስ ቢሆንም በቀጣይ በተከታታይ በምንለቃቸው ፅሁፎች የምስጢረ ሥላሴ አስተምህሮን የምናፀናበት ይሆናል። በቀጣዮቹ ፅሁፎች ከቤተክርስቲያናችን ውጭ ያሉ ተቃዋሚዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች እየለቀምን የምንመልስ ሲሆን ለዛሬ ግን ምስጢራቱ ለምነ አምስት ሆኑ? አዕማድ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውንና ምስጢረ ለምን ተባሉ? የሚለውን እናያለን።
“ነገር ግን ሌሎችን ደግሞ አስተምር ዘንድ በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ።”
— 1ኛ ቆሮንቶስ 14፥19
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በትንታኔ ለማስረዳት ቢሞክር አድካሚ መሆኑን ስለተረዳ በአምስት ቃላት ትምህርቱን ጠቅለል አድርጎ መናገር እንደሚቀለው ይነግረናል የመፅሀፍን ንባብ ከነትርጓሜው አስማምታ የያዘች ቤተክርስቲያን ከዚህ ከጳውሎስ ንግግር በመነሳት የአስተምህሮቶቿን ሀሳብ በአንድ ላይ ጠቅልለው የያዙትን አምስት ምስጢራት ደንግጋ አስቀምጣልናለች ማለት ነው።
አዕማድ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ስንመለከት፦
ዐምድ የግዕዝ ነጠላ ቁጥር አመልካች ሲሆን ስናበዛው አዕማድ ይሆናል።
"ዐምድ ቃልነቱ የግዕዝ ቋንቋ ነው። ነገር ግን በአማርኛ ኹለት አይነት ትርጓሜ ስለ አለው ለቤት ሲሆን ቃሉ ተለውጦ ምሰሶ ይባላል ፤ ለጽህፈት ሲሆን በራሱ ሳይለወጥ አምድ ተብሎ ይጠራል። ኹኔታውም የገፅ ስፋት መክፈያና መመጠኛ ስለሆነ ምሰሶ ከማለት የራቀ ነገር የለውም።
በዚህም ነገር ሃይማኖትን ከፍለን መጥነን የምናጠናባቸው ከፍሎች አዕማድ ይባላሉ።
ምክንያቱም አምድ በገፅ ስፋት ላይ መክፈያ ፡ መመጠኛ በመሆኑ ለጽህፈት ፡ ለንባብ ደንብ እንዲሰጥ ይህም ሰው ሰፊ ፡ ጥልቅ ፡ ረቂቅ የሆነውን ባሕሪየ ሥላሴን ሊመረምር ቢወድ በመጠኑ መርምሮ ሕሊናውን እንዲወስን ፡ ከአቅሙ በላይ እንዳይመረምር ሕግ እና ደንብ የሚሰጥ ስለ ኾነ ነው።
እንዲሁም አምድ በምሰሶነቱ ቤትን እንዲያጠና ይህም ስለ ሃይማኖት በመፅሐፍ ቅዱስ በተፃፈው ቃል የሰውን ልቡና የሚያጠና ስለሆነ ነው።
ስለዚህ ከአዕማድ ተቀዳሚው መጀመሪያው እግዚአብሔር በአካላት ፡ በኩነታት ሦስት ፤ በባሕሪይ አንድ ብለን ማመንን የምንማርበት ፡ የምናስተምርበት ክፍል ምስጢረ ሥላሴ ይባላል። " (አለቃ አያሌው ታምሩ ፡ የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት ፡ ገፅ ፻፳፫)
አንዳንድ ሙስሊም ወገኖች ምስጢረ ሥላሴ ምስጢር መባሉን ይይዙና ምስጢር ስለተባለ የማይገነር አድርገው ይይዙታል ያ ግን አይደለም ቤተክርስቲያን ከምዕመኖቿ ደብቃ የምታስቀምጠው ነገር የለም። ምስጢር መባሉ ለምንድን ነው ብንል ነብየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ይህንን ይለናል ፦
“እውቀትህ ከእኔ ይልቅ ተደነቀች፤ በረታች፥ ወደ እርስዋም ለመድረስ አልችልም።”— መዝሙር 139፥6
በአምላክ ዘንድ ያለች እውቀት የላቀች ፡ የተደነቀች ነችና ማንም መርምሮ ፡ አስልቶ ሊደርስባት አይችልም።
ምስጢረ ሥላሴ ስለ አምላክ አንድነትና ሶስትነት የምንነጋገርበት ስለሆነ አምላክ ከእኛ አዕምሮ ልክ በላይ እና በላይ ነውና የአምላክ ነገር ምስጢር ነው።
ኢዮብ ይህንን ብሏል፦
“የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ልትመረምር ትችላለህን? ወይስ ሁሉን የሚችል አምላክ ፈጽመህ ልትመረምር ትችላለህን?”
— ኢዮብ 11፥7
የእግዚአብሔር ጥልቅ ነገር ሊመረምረው የሚቻለው ይኖር ይሆን? እንኳን ከኛ ኃጥያትን በግብርና በነቢብ የምንከውነው ይቅርና እና በነጽሮተ እግዚአብሔር ማዕረግ ላይ የደረሱ ቅዱሳን እና መላእክትም ቢሆኑ እርሱ ሊገልጥላቸው ከወደደው ውጭ ሊያውቁ የሚችሉ አይደሉም። እና እንዲህ ለረቀቀ የአምላክ ነገር ምስጢር መባሉ አስገራሚ ነገር ነውን? በፍፁም!
በቅዳሴ ሰዓታችን ካህኑ ይህንን ይላል፦
" ወሶበ አሔሊ ክዕበ ይፈቅድ ይዕርግ ላዕለ ወይፃአ በሥውር ወይቅላዕ መንጦላዕተ መሥዋራቲሁ ወይፈርህ እምነደ እሳት ወኢይበጽህ እስከ መንፈቀ መንፈቆሙ ለዐየራት.... ፦ ዳግመኛም ባሰብኩ ጊዜ ሕሊናዬ ተሰውሮ ወደ ላይ ወጥቶ የሕያው መሰወሪያ የሆነውን ሊገልጥ ይወዳል። ከነደ እሳትነቱ የተነሳ ይፈራል ከዐየራት ከአርቧቸው አርቦ አይደርስም። ይህንንም ባሰብኩ ጊዜ ሕሊናዬ በንፋስ ትካሻ ተጭኖ በምስራቅና በምዕራብ በሰሜንና በደቡብ በዳርቻቸውም ሁሉ ሊበር ይወዳል። የፍጡራንን አኗኗር ያይ ዘንድ፤ የአብሕርትንም ጥልቀታቸውን ይለካ ዘንድ፤ የሰማይንም ርዝመቱን ያውቅ ዘንድ በሁሉ ዘንድ ፤ በሁሉም ይዞራል። አቅቶት ወደ ቀደመው አኗኗሩ ይመለሳል። #አሁንም_ገናናነቱን_አንመርምር፤ #ጥልቀቱንም_አንጠናቀቅ_የገናናነቱን_መጠን_ለማመስገን_የነብያትና_የሐዋርያት_አንደበት_የማይቻለው_ነው።
ለነብያትና ለሐዋርያት አንደበት ያልተቻለ ገናናነት ምስጢር ብለን ብንገልፀው አሳነስነው እንጂ ሌላ አላደረግነውም።
የእግዚአብሔር ነገር ፈፅሞ ሊመረመር የማይችል የረቀቀ መሆኑን ከላይ ከጠቀስናቸው ጥቅሶች ውጭ እኒህን ለማጠናከሪያ መመልከት ይቻላል፦
“እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም። የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም።”— ኢዮብ 36፥26
“አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም።” — ኢሳይያስ 40፥28
“የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም።”— ሮሜ 11፥33
እንግድህ መፅሐፍ የእግዚአብሔር ነገር ፈፅሞ ሊደረስ እና ሊታዎቅ የማይችል መሆኑን እንዲህ አበክሮ ከነገረን ስለ እርሱ የሚቀርበው ትምህርት ምስጢር መባሉ ሊያስደንቀንም ሆነ ሊያስገርመን አይገባም።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
Comments
Post a Comment