አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

       "... በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም። አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው።"
(የማቴዎስ ወንጌል 27:46)

         ሙስሊም ወገኖቻችን ከኢየሱስ ስቅለት ጋር በተያያዘ ከሚያነሱት ጥያቄዎች መካከል በወንጌላት ላይ"አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ?" በሚለው ቃል መሰረትነት ነው። እኛም በዚህ መልሳችን ጌታ በረዳን መጠን ጥያቄያቸውን ከመልስ ጋር ግልፅ በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ እንሞክራለን።

ጥያቄያቸውም፦ አምላኬ አምላኬ ተውከኝ ብሏልና ለመሰቀል አልፈለገም ነበረ!

     ከዚህ ቀደም ስቅለት በኢየሱስ ክርስቶስ አንደበት በሚል ርዕስ ባቀረብናት ፅሁፍ ጌታችን ለመሰቀል ፍላጎት እንደነበረውና የእኛም ድህነት የሚፈፀመው በእርሱ ስለሆነ ሊሰቀል እንደሚገባው በእራሱ አንደበት የተናገረ መሆኑን ተመልክተናል። ለማስታወስም ያህል፦ 
"... ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር።"(የማቴዎስ ወንጌል 16:21)
እንዲሁም፦"... እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና #ነፍሱን_ለብዙዎች_ቤዛ_ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።" (የማርቆስ ወንጌል 10:45)

ስለዚህ ጌታችን ከመሰቀሉ በፊት ሊሰቀል እንደሚገባው   እራሱን ለእኛ አሳልፎ እንደሚሰጥ መናገሩ ጌታችን ለመሰቀል ሙሉ ፍላጎት እንደነበረውና የመጣበትም አላማ እንደሆነ መረዳት አያዳግተንም።
ሙስሊም ወገኖቻችን ወደሚጠቅሱት የወንጌል ክፍል ስንመለስ ደግሞ
በመጀመሪያ በዚሁ በጠቀሰው ክፍል ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሞተ ይነገራል።
ታዲያ ኢየሱስ ክርስቶስ #ለመሰቀል_ፍላጎት_እያለው ለምን አምላኬ አምላኬ ለምን አለ?
         1-የአዳምን ጩኸት ጮኸ አምላኬ አምላኬ አለ፦

ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር ስጋ ለብሶ ዳግማዊ አዳም ሆኖ ነው።(1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15:45)ዳግማዊ አዳም ማለት በአዳም ቦታ ገብቶ የአዳምን ሞቶ፣ አዳም ሊያቀርበው የሚገባውን መስዋዕት አቅርቦ አዳምን የሚያድን ማለት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቦታ በሲዖል ሆኖ ይሰቃይ የነበረውን የአዳምን ጩኸት ጮኋል።

          2-ትንቢቱን ለመፈፀም፦
"አምላኬ አምላኬ ከምን ተውከኝ" ብሎ የሚጀምረውን የቅዱስ ዳዊት ትንቢት ስለ እርሱ የተተነበየ መሆኑን ለመጠቆም ነው። በዚህ የመዝሙር ክፍል(22ተኛው መዝሙር) ላይ ቅዱስ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚደርስበት ህማም እንግልት በስፋት የተነበየው ትንቢት ይገኛል። እንደሚከተለው እንመልከታቸው፦
✅1-በወታደሮች እንደሚያዝና በእርሱ ላይ አፋቸውን ስለ መክፈታቸው፦
12፤ ብዙ በሬዎች ከበቡኝ፥ የሰቡትም ፍሪዳዎች ያዙኝ፤
13፤ እንደ ነጣቂና እንደሚጮኽ አንበሳ በላዬ አፋቸውን ከፈቱ።
✅2-እንደተገረፈ የሚያመለክት(በመገረፉም ሃይሉ እንደገል ደቀቀ)

14፤ እንደ ውኃ ፈሰስሁ፤ አጥንቶቼም ሁሉ ተለያዩ፤ ልቤ እንደ ሰም ሆነ፥ በአንጀቴም መካከል ቀለጠ።
15፤ ኃይሌ እንደ ገል ደረቀ፥ በጕሮሮዬም ምላሴ ተጣጋ፥ ወደ ሞትም አሸዋ አወረድኸኝ።

✅3-ሰዎች እንደሚያላግጡበት፦

""7፤ የሚያዩኝ ሁሉ ይላገዱብኛል፤ ራሳቸውን እየነቀነቁ በከንፈሮቻቸው እንዲህ ይላሉ። 8፤ በእግዚአብሔር ተማመነ፥ እርሱንም ያድነው፤ ቢወድደውስ ያድነው።"" ይህ ትንቢት በጌታችን ላይ ለመፈፀሙ በሉቃስ ወንጌል ላይ ተቀምጧል።
"... ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። መኳንንቱም ደግሞ። ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ፥ ራሱን ያድን እያሉ #ያፌዙበት ነበር።"(የሉቃስ ወንጌል 23:35፤)

✅4-ልብሱን እንደሚከፋፈሉት ዕጣ እንደሚጣጣሉበት፦

"... ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ።" (መዝሙረ ዳዊት 22:18)

"23፤ ጭፍሮችም ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ለእያንዳንዱ ጭፍራ አንድ ክፍል ሆኖ በአራት ከፋፈሉት፤ እጀጠባቡን ደግሞ ወሰዱ። እጀ ጠባቡም ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ አልነበረም።"
(የዮሐንስ ወንጌል 19:23) "... ስለዚህ እርስ በርሳቸው። ለማን እንዲሆን በእርሱ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው ተባባሉ። ይህም። ልብሴን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉበት የሚለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።"(የዮሐንስ ወንጌል 19:24)

----------
16፤ ብዙ ውሾች ከብበውኛልና፤ የክፋተኞች ጉባኤም ያዘኝ፤ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ።
17፤ አጥንቶቼ ሁሉ ተቈጠሩ፤ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም።

ከዚህ ትንቢት ላይ የሚገርመውና የሚያስደንቀው ጉዳይ  ስቅለት ዳዊት ባልነረበት ዘመን ስለ ስቅለት መተንበዩ ነው። ስቅለት የተጀመረው ከዳዊት ቡሃላ ነበረ ስለዚህ ትንቢቱ ስለ ኢየሱስ ስለ እራሱ ለመሆኑ ጌታችን የትንቢታዊ መዝሙሩን የመጀመሪያ ስንኝ ተናግሮ መፅሀፍን እንዲያስተውሉ እድል ፈንታ ሰጥቷቸዋል።

ማጠቃለያ፦ ጌታችን በመስቀል ላይ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ ያለው ለመሰቀል ሳይፈልግ ቀርቶ ሳይሆን በመዝሙሩ ላይ ያለውን ትንቢት እንደተፈፀመ ለማሳወቅ ነው።

        ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
______________✝
       ለማንኛውም አስተያየት፦
[ ዐቃቢያነ እምነት ዘኦርቶዶክስ ]

ለቴሌግራም ቻናላችን፦
[ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ]
     

Comments

Popular posts from this blog

ዕቅበተ እምነት

ወላዲተ አምላክ

መልስ ለወሒድ ዑመር