ምስጢረ ስላሴ በነብያት

   አንድ አምላክ በሚሆን በአብ ፡ በወልድ ፡ በመፈንስ ቅዱስ ስም!

    ባለፉት ሶስት ክፍላት ስለ ምስጢረ ሥላሴ መነጋገራችን ይታወሳል በተለይ ደግሞ በክፍል ሁለት በብሉይ ኪዳን ምስጢረ ሥላሴን የሚያሳዩልንን ማስረጃዎች ማቅረባችን ይታወሳል። ያንን አይተው ያልተረዱ ይሁኑ ለመረዳት ያልፈለጉ "ነብያት ስለ ምስጢረ ሥላሴ አላስተማሩም" ሲሉ ተመለከትንና እኛም በዚሁ ርዕስ ላይ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለማቅረብ ወደድን። ( NB=> ስቅለት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን እግዚአብሔር አምላክ በረዳን መጠን ለመመለስ አስበናልና በዚህ ርዕስ ዙሪያ የምንለቀው በመሃል ጣልቃ እያስገባን ይሆናል።)


   ለዛሬ ልንዳስሰው የወደድነው የነብይ መፅሀፍ ከዐበይት ነብያት መካከል አንዱ የሆነው ታላቁ ነብይ ብዙ ትንቢቶችን በመፅሀፉ ያሰፈረልን ነብዬ እግዚአብሔር ነብዩ ኢሳይያስ ይሆናል። ልባችሁን ከፍታችሁ እንድታነቡት በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን 🙏


   ለሀሳባችን መነሻ አድርገን የምንጠቀመው ጥቅስ በዘወትር ጸሎታችን ላይ የሚገኘውን " ቅዱስ : ቅዱስ : ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት ፍፁም ምሉእ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሐቲከ" የሚለው የተወሰደበት የሱራፌል ምስጋና ይሆናል። በነብዩ መፅሀፍ ደግሞ እንዲህ ሰፍሯል፦

   ኢሳይያስ 6 

¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

³ እርስ በርሳቸው በመቀባበልም “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ በክብሩ ተሞልታለችቃ ይሉ ነበር።


 …  

⁸ ከዚያም የጌታ ድምፅ፣ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” ሲል ሰማሁት። እኔም፣ “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” አልሁ።

   👆 በዚህ ጥቅስ እንደምንመለከተው ሱራፌል "ቅዱስ" የሚለውን ሶስት ጊዜ ሲጠሩት "እግዚአብሔር " ብለው ደግሞ በነጠላ ቁጥር አንድ ጊዜ ብቻ ጠርተውታል። ይሄን ደግሞ ከሥላሴ አስተምህሮ ጋር ስናገናኘው፦ እንደ ሶስትነቱ ሶስት ጊዜ " ቅዱስ ፡ ቅዱስ ፡ ቅዱስ" ሲሉ እንደ አንድነቱ ደግሞ " ጌታ እግዚአብሔር " ብለው በነጠላ ቁጥር ተናግረዋል። ይሄ ሙሉ ለሙሉ ከሥላሴ አስተምህሯችን የሚስማማ ነው። ለአማኝ ይሄ በቀላሉ የሚገባ ቢሆንም ተቃዋሚዎችን ሶስት ጊዜ " ቅዱስ ፡ ቅዱስ ፡ቅዱስ" መባሉ እንዴት አድርጎ ነው ሥላሴን የሚያሳየው? በማለት የሚያነሱትን ተቃውሞ ለማፈራረስ ሲባል የበለጠ ለማብራራት ሁለት ነጥቦችን እናንሳ፦

 📚 ማሳያ_1፦ " ቅዱስ ፡ ቅዱስ ፡ቅዱስ " ተብሎ ሶስት ጊዜ መገለፁ ሶስት አካል መኖሩን ያሳያል ስንል በባዶ ሳይሆን ከታች ወረድ ብሎ በቁጥር 8 ላይ በብዙ ቁጥር " ማንስ ይሄድልናል" ብሎ ማቅረቡን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው። ከላይ ሶስት ጊዜ "ቅዱስ" ማለቱን ይዘን ከታች ከምናገኘው ብዙ ቁጥር ጋር ስናገጣጥመው በእርግጥም በአንድ አምላክነት ያሉ ሶስት አካላት መኖራቸውን እንረዳለን።

 📚#ማሳያ_2፦

   ኢሳይያስ በተደጋጋሚ እግዚአብሔርን አንድ መሆኑን የመሰከረ ነብይ ነው፦

   ““በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር ባሉ መንግሥታት ሁሉ ላይ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርንም ፈጥረሃል።”

 — ኢሳይያስ 37፥16

  ““ከማሕፀን የሠራህ፣ የተቤዠህም፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሁሉን ነገር የፈጠርሁ፣ ብቻዬን ሰማያትን የዘረጋሁ፣ ምድርን ያንጣለልሁ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”

 — ኢሳይያስ 44፥24

 ነብዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔር አንድ መሆኑን ቢመሰክርልንም ሶስት አካላት መኖሩን ግን በተደጋጋሚ ያስረዳናል። " አብ አምላክ ፡ ወልድ አምላክ ፡ መንፈስ ቅዱስ አምላክ" መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጿል።

   የአብ አምላክነት የማያሻማ ስለሆነ የወልድንና የመንፈስ ቅዱስን አምላክነት ከኢሳይያስ መፅሀፍ በማሳየት የተነሳንበት ሀሳብ ልክ መሆኑን እናስረግጣለን።

  እግዚአብሔር ወልድ አምላክ ስለመሆኑ፦


 ✟ ➊ "የመጥምቁ ዮሀንስ መንገድ ጠራጊነት" 

 ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ መጀመሪያ ምዕራፍ ስለ መጥምቁ ዮሀንስ አመጣጥና አላማ ይነግረናል። የመጥምቁ ዮሀንስ አመጣጥ አላማ በወንጌሉ እንደተገለጸው የኢየሱስን መንገድ ለማስተካከል ሲሆን ነብዩ ኢሳይያስ እንደነገረን በማርቆስ ወንጌልም እንደተገለጸው ይሄ የሚስተካከለው መንገድ የጌታ የእግዚአብሔር ነው።

   “የዐዋጅ ነጋሪ ድምፅ እንዲህ ይላል፤ “የእግዚአብሔርን መንገድ፣ በምድረ በዳ አዘጋጁ፤ ለአምላካችን አውራ ጐዳና፣ በበረሓ አስተካክሉ።”

 — ኢሳይያስ 40፥3

   ማርቆስ 1 

¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

² በነቢዩ በኢሳይያስ፣ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ “እነሆ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፤

³ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በበረሓ የሚጮኽ ድምፅ’።”

⁴ ስለዚህ መጥምቁ ዮሐንስ በበረሓ እያጠመቀና ለኀጢአት ስርየት የንስሓ ጥምቀት እየሰበከ መጣ።

 …  

⁷ ስብከቱም፣ “እኔ ጐንበስ ብዬ የጫማውን ማሰሪያ መፍታት ከማይገባኝ፣ ከእኔ የሚበልጥ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤

⁸ እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል” የሚል ነበር።

  ከዚህ እንደምንረዳው ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን ነው።

 ✟ ➋ በልባችን ልንቀድሰው የሚገባን እግዚአብሔር ብቻ ስለመሆኑ ፦

  ኢሳይያስ 8 

¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

¹² “እነዚህ ሰዎች፣ ‘አድማ’ ብለው የሚጠሩትን፣ ማንኛውንም ነገር፣ ‘አድማ’ አትበሉ፤ እነርሱ የሚፈሩትን አትፍሩ፤ አትሸበሩለትም።

¹³ 👉ልትቀድሱ የሚገባው የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ብቻ ነው፤ ልትፈሩት የሚገባው እርሱን ነው፤ ልትንቀጠቀጡለት የሚገባውም እርሱ ነው።

   ኢሳይያስ ልንቀድሰው የሚገባን እግዚአብሔርን ብቻ መሆኑን ሲነግረን ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ ኢየሱስን በልባችሁ ቀድሱት ይለናል፦

  1ኛ ጴጥሮስ 3 

¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

¹⁴ ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራ ቢደርስባችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ “ዛቻቸውን አትፍሩ፤ አትታወኩም።”

¹⁵ ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ 👉በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤

  በልባችን ልንቀድሰው የሚገባን እግዚአብሔርን ብቻ ከሆነ ፡ ኢየሱስን በልባችን ልንቀድሰው የሚገባን ከሆነ ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው ማለት ነው።

 ✟ ➌ የማዕዘን ድንጋይ

  “እርሱም መቅደስ ይሆናል፤ ለሁለቱ የእስራኤል ቤት ግን የሚያደናቅፍ ድንጋይ የሚያሰናክልም ዐለት ይሆንባቸዋል፤ ለኢየሩሳሌም ሕዝብም ወጥመድና አሽክላ ይሆናል።”

 — ኢሳይያስ 8፥14 (አዲሱ መ.ት)

  ኢሳይያስ በዚህ ጥቅስ የሚያደናቅፍ እና የሚያሰናክል ብሎ የገለፀው እግዚአብሔርን ሲሆን በሌላ ቦታ ደግሞ ለኢየሱስ ሲያውለው እናያለን፦


  “ስለዚህ ልዑል እግዚእብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ የተፈተነ ድንጋይ፣ የመሠረት ድንጋይ፣ ለጽኑ መሠረት የሚሆን የከበረ የማእዘን ድንጋይ፣ በጽዮን አስቀምጣለሁ፤ በእርሱም የሚያምን አያፍርም።”

 — ኢሳይያስ 28፥16


  ይህንን ትንቢት ከኢሳይያስ በተጨማሪ ቅዱስ ጳውሎስም ለኢየሱስ አድርጎ ሲገልፀው እናያለን፦

   1ኛ ጴጥሮስ 2 

¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

⁶ ምክንያቱም በመጽሐፍ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤ 👉“እነሆ፤ የተመረጠና ክቡር የማእዘን ድንጋይ፣ በጽዮን አኖራለሁ፤ በእርሱም የሚያምን፣ ከቶ አያፍርም።”

⁷ እንግዲህ ለእናንተ ለምታምኑት ይህ ድንጋይ ክቡር ነው፤ ለማያምኑት ግን፣ “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ።”

⁸ ደግሞም፣👉 “ ሰዎችን የሚያሰናክል፣ የሚጥላቸውም ዐለት ሆነ።” የሚሰናከሉት ቃሉን ባለመታዘዛቸው ነው፤ የተመደቡት ለዚህ ነውና።

  ከኢሳይያስም ሆነ ከቅዱስ ጴጥሮስ እንደምንረዳው 👉 ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው።ለልባም ሰው እኒህ ሶስቱ በቂ ናቸው። ፅሁፍ ላለማብዛት ስለ እግዚአብሔር ወልድ በዚህ ይብቃን።

  ✞ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አምላክ ስለመሆኑ፦

 ➊  መዝሙር 78 

¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

¹⁷ እነርሱ ግን በምድረ በዳ በልዑል ላይ በማመፅ፣ በእርሱ ላይ ኀጢአት መሥራታቸውን ቀጠሉ።

¹⁸ እጅግ የተመኙትን ምግብ በመጠየቅ፣ እግዚአብሔርን በልባቸው ተፈታተኑት።

¹⁹ እንዲህም ብለው በእግዚአብሔር ላይ ተናገሩ፤ “እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድ ማሰናዳት ይችላልን?

  ዳዊት እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር ያወጣቸው እግዚአብሔርን በበረሃ እንደተፈታተኑት ሲነግረን፡ የዕብራውያን ፀሀፊ ደግሞ እግዚአብሔር በአንድነት ውስጥ ሶስትነት ያለው መሆኑን ስለተገነዘበ "መንፈስ ቅዱስን ተፈታተኑት" በማለት ይገልፅልናል፦

   ዕብራውያን 3 

¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

⁷ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል፣ “ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣

⁸ በምድረ በዳ በፈተና ቀን፣ በዐመፅ እንዳደረጋችሁት፣ ልባችሁን አታደንድኑ።

⁹ አባቶቻችሁ በዚያ ተፈታተኑኝ፤ መረመሩኝ፤ ያደረግሁትንም ሁሉ ለአርባ ዓመት አዩ።

 ➋  ከተነሳንበት ጥቅስ ዝቅ ብለን ቁጥር 9ን እንመለከት ፦

  “👉 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “👉 ወደዚህ ሕዝብ ሂድ፤ “ ‘መስማትን ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም’ ብለህ ንገራቸው።”

 — ኢሳይያስ 6፥9

  ይህንን ተናጋሪው በኢሳይያስ መፅሀፍ እግዚአብሔር መሆኑ ሲገለፅ የሐዋርያት ስራ ፀሀፊ ተናጋሪው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ይነግረናል፦ 

  ሐዋርያት 28 

¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

²⁵ እርስ በርሳቸውም አልተስማሙም፤ ጳውሎስም እንዲህ የሚል የመጨረሻ ቃል ከተናገራቸው በኋላ ሄዱ፤ “👉 መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ አማካይነት ለአባቶቻችሁ በትክክል እንዲህ ብሎ ተናግሮአል፤

²⁶ “ ‘👉 ወደዚህ ሕዝብ ሂድ፤ እንዲህም በላቸው፤ “መስማትን ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትን ታያላችሁ፤ ነገር ግን አትመለከቱም።”

 ከዚህ እንደምንረዳው መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው።

  ከኢሳይያስ መፅሀፍ በመነሳት ሶስት መለኮታዊ አካል መኖሩን ከተረዳን እግዚአብሔር ደግሞ አንድ መሆኑን ከተገነዘብን እግዚአብሔር በአንድነት ውስጥ ሶስትነቱ እንዳለ እንረዳለን ማለት ነው።

   ሱራፌል ሶስት ጊዜ "ቅዱስ ፡ ቅዱስ ፡ ቅዱስ" ብለው ማመስገናቸው ሶስቱንም አካላት አብ ፡ ወልድና መንፈስ ቅዱስን የሚያመለክት ነው።


 " ነብያት እግዚአብሔር አንድም ሶስትም አይደለም " ብለው ለሚሞግቱ ተቃዋሚዎች ይህንን አይተው ይማሩ ዘንድ ፡ ሌሎችም ይማሩበት ዘንድ share ያድርጉ 🙏። እግዚአብሔር እንደፈቀደ ከሌሎች የነብያት መፅሀፍትም ማስረጃዎችን ስለምናቀርብ እናንተም እንናያመልጣችሁ ገፁን አይራቁ

   13/07/2012 ተጻፈ

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

    ወለወላዲቱ ድንግል!

    ወለመስቀሉ ክቡር! 

    ይቆየን!

Comments

Popular posts from this blog

ዕቅበተ እምነት

ወላዲተ አምላክ

መልስ ለወሒድ ዑመር