መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ነው።
መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ነው።
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ ፡ በወልድ ፡ በመንፈስ ቅዱስ ስም!
በትምህተ ሥላሴ ክፍላችን ላይ እንዳየነው ከሶስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ፤ ከሶስቱ አካል አንዱ አካል መንፈስ ቅዱስ ነው። በዚህ እና በሌሎች ጽሁፎች ስለ መንፈስ ቅዱስ ብቻ የምንመለከት ሲሆን መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ወይስ ዝርው ኋይል?ስለመንፈስ ቅዱስ አምላክነት መፅሀፍ ምን ይላል?እና ስለ ጰራቅሊጦስ የምናይ ይሆናል። ለዛሬ ስለ መንፈስ ቅዱስ አካላዊነት መፅሀፋችንን በደንብ ገልጠን በጥልቀት እንመልከት(በጽሁፉ ብዙ ምልከታዎች ስለሰፈሩ ሊረዝም ይችላልና ረጋ ብላችሁ እንድታነቡት በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን)፦
የይሖዋ ምስክሮች (Jehovahwitnesses) ከክርስትና አስተምህሮ ከሚለዩባቸው በርካታ ነጥቦች መካከል ስለ መንፈስ ቅዱስ ያላቸው እምነት ነው። እንደእነርሱ እምነት" መንፈስ ቅዱስ ዝርው የአምላክ ኃይል (impersonal power)እንጂ አካላዊ አይደለም" የሚል ነው። ይህን እሳቤያቸውን በመንፈስ ቅዱስ ሚዛን እንመዝነው፦
ወደነጥባችን ከመግባታችን በፊት አካል ስንል ስንል በሰዎች ጭንቅላት ውስጥ የሚመጣውን ምስል እናጥራ። ከክርስትና ውጭ የኾኑ ወይንም ክርስትና ውስጥም ሁነው ሊሆን ይችላል ስለ እግዚአብሔር አካልነት ስንነጋገር አካል የሚለውን በጭንቅላታቸው የሚስሉት ስዕል ግዙፍ የኾነ ፣ የሚዳሰስ ፣ የሚጨበጥ ማንነትን ነው። ይህ ግን መፅሀፍ አይደገፈውም። አካል ማለት በአጭሩ እኔ ማለት የሚችል ፣ ማንነት ፣ ስሜት ፣ ፈቃድ ያለው ነው። እኒህን ሊያሟሉ የሚችሉት ደግሞ እግዚአብሔር ፣ መላእክት እና ሰው ናቸው። ሰው አካል አለው ስንል የሚዳበሰውን ፣ የሚጨበጠውን አይደለም ይሄ የስጋ ባህሪይ እንጂ የአካል ትርጉም አይደለም ሰው አካላዊ ነው ሲባል ከላይ ያልናቸው ነገሮች ስላሉት ነው። እግዚአብሔርም አካል አለው ስንል ግዙፍ የሆነ ስጋዊ ማንነት ኑሮት ሳይሆን ፈቃድ ፣ ስሜት ፣ "እኔ "ማለት ስለሚችል ነው። ስለ "አካል" ይህንን ካል እነዚህን መንፈስ ቅዱስ ያሟላል ወይ?የሚለውን እንይ፦
✞➊፦ #መንፈስ_ቅዱስ ማንነት ላለው በሚውሉ ተውላጠ ስሞች ተገልጿል ይኼ ደግሞ "እኔ" ማለት የሚችል ያደርገዋል ፦
ዮሐንስ 16
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ ግን👉 #እርሱ_የእውነት_መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።¹⁴ #እርሱ_ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና።
ኤፌሶን 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤¹⁴👉 #እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል።
✟➋፦ #መንፈስ_ቅዱስ የራሱ የኾነ ስሜት አለው፦
መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ነውና እኛ ለእርሱ ምላሽን እንሰጣለን እርሱም ለእኛ ምላሽን ይሰጣል፦
✔ መንፈስ ቅዱስን ይዋሻሉ፦
“ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለ፤ “ሐናንያ ሆይ፤ መንፈስ ቅዱስን ትዋሽና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን ልብህን ለምን ሞላው?”— ሐዋርያት 5፥3 (አዲሱመ.ት)
✔ መንፈስ ቅዱስን ይፈታተኑታል፦
“ጴጥሮስም፣ “የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ እንዴት እንዲህ ተስማማችሁ?እነሆ፤ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች ተመልሰው እግራቸው ደጃፍ ላይ ነው፤ አንቺንም ይዘው ይወጣሉ” አላት።” — ሐዋርያት 5፥9 (አዲሱመ.ት)
✔መንፈስ ቅዱስን ይቃወሙታል ፦
““እናንት ልባችሁና ጆሮአችሁ ያልተገረዘ፣ አንገተ ደንዳኖች ልክ እንደ አባቶቻችሁ መንፈስ ቅዱስን ሁል ጊዜ ትቃወማላችሁ።”— ሐዋርያት 7፥51 (አዲሱመ.ት)
✔ መንፈስ ቅዱስን ያሳዝኑታል፦
“ለቤዛ ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝኑ።” — ኤፌሶን 4፥30 (አዲሱመ.ት)
✔ መንፈስ ቅዱስን ይሰድቡታል፦
“ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ የዘላለም ኀጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም።”” — ማርቆስ 3፥29 (አዲሱመ.ት)
👆 እኒህ መሰደብ ፣ ማዘን ፣ ተቃውሞ መቀበል ፤ መፈታተን ፣ መዋሸት ስሜት ላለው አካል የሚስማሙ ናቸው። መንፈስ ቅዱስን ከተፈታተን ወይንም ከተሳደብን መንፈስ ቅዱስ አካል አለው ማለት ነው።
✟➌፦ መንፈስ ቅዱስ የራሱ ፈቃድ አለው፦
“እነዚህ ሁሉ የዚያው የአንዱ መንፈስ ስጦታዎች ሲሆኑ፣ ለእያንዳንዱ ሰው እርሱ ራሱ #እንደ_ፈቀደ ይሰጠዋል።”— 1ኛ ቆሮንቶስ 12፥11 (አዲሱመ.ት)
ከዚህም በተጨማሪ የራሱ ፈቃድ አለው ማለት የራሱን ውሳኔ መወሰን ወይንም የራሱን እርምጃ መውሰድ ይችላል ማለት ነው፦
“ከእነዚህ አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳ ንጭንባችሁ፣👉 #ለመንፈስ_ቅዱስም_ለእኛም መልካም መስሎ ታይቶናል፤ ይኸውም፦”— ሐዋርያት 15፥28 (አዲሱመ.ት)
👆 መንፈስ ቅዱስ አንድን አካል አካላዊ ነው የሚያስብሉትን ነገሮች እንደሚያሟላ በዚህ መልኩ ካየን እርሱ አካላዊ እንጂ ዝርው አለመሆኑን መረዳት እንችላለን ማለት ነው። ግን በደንብ ለማስረገጥ አካላዊ ማንነት ያለው ብቻ የሚተገብራቸውን ሌሎች ማሳያዎችንም እንመልከት፦
📌✞ መንፈስ ቅዱስ ይመሰክራል፦
“እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፥ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።” — ሐዋርያት 5፥32
“መንፈስ ቅዱስም ደግሞ ስለዚህ ይመሰክርልናል፤ ከዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው ይላል ጌታ፤ በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ ብሎ ከተናገረ በኋላ፥”— ዕብራውያን 10፥15-16
እስኪ እራሳችሁን ጠይቁ ❓ አካላዊ ያልሆነ ሊመሰክር ይችላልን❓🤔
📌✞ መንፈስ ቅዱስ ያስተምረናል ፦
“መንፈስ ቅዱስ በዚያች ሰዓት ልትናገሩ የሚገባችሁን ያስተምራችኋልና።” — ሉቃስ 12፥12
“መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም።”— 1ኛ ቆሮንቶስ 2፥13
ተወዳጆች በእያንዳንዱ ጥቅስ እራሳችሁን ጠይቁ እስኪ አካል የሌለው እኔ ማለት የማይችል ያስተምራልን❓
📍✞ መንፈስ ቅዱስ ትንቢትን ይገልጻል ፦
“በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር።” — ሉቃስ 2፥26
“በእነርሱ ውስጥ የነበረው የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ እንዲሁም ከመከራው በኋላ ስለሚሆነው ክብር አስቀድሞ በመናገር ያመለከታቸው ጊዜ መቼና እንዴት እንደሚፈጸም ይመረምሩ ነበር።” — 1ኛ ጴጥሮስ 1፥11 (አዲሱመ.ት)
📌🔗 መንፈስ ቅዱስ #ይናገራል ፦
“መንፈስም ፊልጶስን፣ “ሂድ፤ ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው።”— ሐዋርያት 8፥29 (አዲሱመ.ት)
“ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል፣ “ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣”— ዕብራውያን 3፥7 (አዲሱመ.ት)
“ከዚያም፣ “ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ ሆነው የሚሞቱ ብፁዓን ናቸው ብለህ ጻፍ” የሚል ድምፅ ከሰማይ ሰማሁ። መንፈስም፣ “አዎ፣ ሥራቸው ስለሚከተላቸው ከድካማቸው ያርፋሉ” ይላል።” — ራእይ 14፥13 (አዲሱመ.ት)
በተጨማሪም እኒህን ጥቅሶች ይመልከቱ 👉 ማር 13:11፣የሐ.ስራ1:16፣ 10:19፣11:12፣ 13:2፣ 1ጢሞ 4:1።
አካል የሌለው ነገር ይናገራልን❓ መልስ ለሕሊና
#ምልከታችንን #እንቀጥል ፦
የመንፈስ ቅዱስን አካላዊነት የምንረዳበት ሌላው ነገር ደግሞ አካላዊ ከሆነ ነገር ጋር በአንድነት መቅረቡ ነው፦
“ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ 👉 በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤”— ማቴዎስ 28፥19 (አዲሱመ.ት)
ይህ ጥቅስ ብቻ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ መሆኑን ያስረዳናል። "በአብ ፡ በወልድ ፡ በመንፈስ ቅዱስ" ሲል በሶስቱም ስሞች መጀመሪያ ላይ "the (tou)"የሚል definite article ያለ ሲሆን ስሞቹን ደግሞ "and (kaí)"የሚል ቃል ይለያያቸዋል ይኼ ደግሞ በስድስተኛው የግራንቪል ሻርፕ የግራመር ህግ መሰረት አብን ፡ ወልድን እና መንፈስ ቅዱስን የተለያዩ አካላት ያደርጋቸዋል። ከዛም በተጨማሪ አብ አካላዊ ከሆነ ፡ ወልድ አካላዊ ከሆነ መንፈስ ቅዱስም አካላዊ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም።
እኒህንም ጨምሯቸው ፦
“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን።”— 2ኛ ቆሮንቶስ 13፥14 (አዲሱመ.ት)
“እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ ካወቃቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝ በደሙ ለተረጩትና በመንፈስ አማካይነት ለተቀደሱት፤ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።”— 1ኛ ጴጥሮስ 1፥2 (አዲሱመ.ት)
⚡ ምልከታችንን እንቀጥል፦
ኢየሱስ ክርስቶስ በበዓለ ሐምሳ ለሐዋርያቱ መንፈስ ቅዱስ እንደሚወርድላቸው የተናገረበትን ደግሞ እንይ፦
“እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር👉 #ሌላ_አጽናኝ ይሰጣችኋል፤”— ዮሐንስ 14፥16 (አዲሱመ.ት)
ተወዳጆች "ሌላ" የምትለውን ቃል ልብ በሉልኝ። በግሪክ ወደ እንግሊዝኛ "another " ተብለው ሊተረጎሙ የሚችሉ ሁለት ቃላት አሉ። እነርሱም állos & héteros ሲሆኑ በዚህ ጥቅስ ውስጥ የገባው állos የሚለው ነው። የዚህን ቃል አገልግሎቱን ስንመለከት 'another of the #SAME_kind' ሲሆን héteros ደግሞ 'another of the #Different_kind። állos ተመሳሳይ አይነት ለሆነ ሁኖ #ለተለየ_አካል የሚያገለግል በመሆኑ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ መሆኑን ያሳደናል ማለት ነው። ከዚህም በተጨማሪ "#አፅናኝ" ለማለት የገባው የግሪክ ቃል parákkētos ሲሆን ይኸው ቃል በ 1ኛ ዮሐንስ 2:1ላይ ለኢየሱስ ክርስቶስም አገልግሏል። መንፈስ ቅዱስ አካላዊ አይደለም ካልን ኢየሱስም አካላዊ አይደለም ማለት ነው። ይህ ነው እንግዲህ የሀሰተኞች መጨረሻ!
እንዲህ የመንፈስ ቅዱስን አካላዊነት በተረዳ መልኩ ካየን መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ኃይል ነውን?የሚለውን እንይ፦
"መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ሳይሆን ዝርው የሆነ የአምላክ ኃይል ነው " የምንል ከሆነ የሚከተሉት ጥቅሶች ትርጉም አልባ የሚሆኑ ይሆናል ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስና ኃይል የተለያዩ መሆናቸውን ሊያስረዳ በሚችል መልኩ በአንድ ጥቅስ ውስጥ ተጠቅሰዋልና ነው፦
➊፦ “ኢየሱስም *በ*መንፈስ_ኀይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ዝናውም በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ ወጣ።” — ሉቃስ 4፥14 (አዲሱመ.ት)
ተወዳጆች "በ" የምትለውን ፊደል ልብ በሉልኝ ፊደሏ ኃይሉ የሚመነጨው ከመንፈስ ቅዱስ እንደሆነ በግልጽ ትነግረናለች ። መንፈስ ቅዱስ የአምላክ ኃይል ነው የሚሉትን ሰዎች ባዶ አመክንዮ ለመረዳት ግን መንፈስ በሚለው ቦታ ኃይልን እንጠካ እና ምን ያህል ትርጉም አልባ እንደሆነ ተመልከቱት ፦
“ኢየሱስም👉 በኃይል ኀይል 👈😯 ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ዝናውም በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ ወጣ።” — ሉቃስ 4፥14 (አዲሱመ.ት)(ትርጉምይሰጣል❓)
➋፦“ እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስ #በመንፈስ_ቅዱስና_በኀይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ።” — ሐዋርያት 10፥38 (አዲሱመ.ት)
(እግዚአብሔር ኢየሱስ በኃይልና በኃይል ቀባው 😯 ያስኬድ ይሆን❓)
➌፦“ይህም የሆነው በመንፈስ ቅዱስ ኀይል፣ በምልክቶችና በታምራት ነበር። በዚህም ሁኔታ ከኢየሩሳሌም እስከ እልዋሪቆን ዙሪያ ድረስ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ ሰብኬአለሁ።” — ሮሜ 15፥19 (አዲሱመ.ት)
(ይህም የሆነው በኃይል ኃይል 😯 ፣ በምልክቶችና በታምራት ነበር)
ሌሎችንም እናንተ ተመልከቱ፦ ሮሜ 15:13፣ ሥራ 1:8፣ 2 ቆሮ 13:14፣ ገላ 4:29።
ማጠቃለያ፦
መንፈስ ቅዱስ ከሶስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ፡ ከሶስቱ አካል አንዱ አካል የሆነ እንጂ ዝርው(ኢ-አካላዊ)የሆነ የአምላክ ኃይል አይደለም። እንዲህ ብለው ለሚያምኑ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምህረቱን ይላክላቸው ጸሎታችን ነው!
16/08/2012 ተጻፈ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ክፍል ሁለት [ የመንፈስ ቅዱስ አምላክነት ]
___________________✝
ለማንኛውም አስተያየት፦
[ ዐቃቢያነ እምነት ዘኦርቶዶክስ ]
ለቴግራም ቻናላችን፦
[ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ]
Comments
Post a Comment