አፅናኙ ማነው? ክፍ. 1
በአብ ስም በወልድ ስም በመንፈስ ቅዱስ ስም አንድ አምላክ አሜን!
ክፍል አንድ
አጽናኙ ማነው? መንፈስ ቅዱስ ወይስ መሐመድ
=>>>በክፍል አንድ እና ሁለት ላይ በተለቀቁት የነገረ መንፈስ ቅዱስ ትምህሮቶች ላይ መንፈስ ቅዱስ የራሱ የሆነ ፍጹም አካል ያለው [መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ነው ] ፣ከአብና ከወልድ ጋር በባህርይ አንድ የሆነ አምላክ መሆኑን ከቅዱሳት መጽሐፍት ምስክርነት ጋል ተገልጿል። [ የመንፈስ ቅዱስ አምላክነት። ]
በዚህ ጽሁፍ ደግሞ ሙስሊሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ መንፈስ ቅዱስ የተነገረውን ቃል ስለ መሐመድ ነው ብለው ስለ ሚሞግቱበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሀሳብ እንመለከታለን።
=>>>ሙስሊሞች ዘወትር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሚያነሱት ትችት "መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ መጽሐፍ አይደለም፣ ተበርዟል" ይላሉ። በአንጻሩ ደግሞ ከመሐመድ በፊት ስለ መሐመድ የሚናገር ኢስላማዊ ማስረጃ ማግኘት ስላልቻሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መሐመድን በመፈለግ ተጠምደዋል። መለኮታዊ መጽሐፍ አይደለም ብለው ከሚተቹት መጽሐፍ ውስጥ ስለ መሐመድ የተነገረ ትንቢት አለ ብሎ ማሰብ የራስ ሀሳብን ለማጽናት ከራስ ሀሳብ ጋር መጋጨት ነው።
=>>>ሙስሊሞች ስለ መሐመድ ይናገራል ብለው ከሚያቀርቧቸው ጥቅሶች አንዱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መንፈስ ቅዱስ የተናገረው ነው። ቃሉ እንዲህ ይላል:-
(የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14)
----------
15-16፤ ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤17፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።
" አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።"
(የዮሐንስ ወንጌል 14:26)
" ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል"(የዮሐንስ ወንጌል 15:26)
" እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።"
(የዮሐንስ ወንጌል 16:7)
" እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤"
(የዮሐንስ ወንጌል 16:8)
=>>>በዚህ ጽሁፍ "አጽናኝ" የተባለው መሐመድ ሊሆን የማይችልባቸውን መክንያቶች ከአጠቃላይ ከጥቅሱ አውድና ከራሳቸው ከእስልምና አስተምህሮ አንጻር እንመለከታለን። በቀጣይ ጽሁፍ ደግሞ አጽናኝ የተባለው መንፈስ ቅዱስ አይደለም በማለት ሙስሊሞች ለሚያቀርቧቸው ሙግቶች ምላሾችን እንመለከታለን።
=>>>አጽናኙ መሐመድ ከሆነ:-
1. በዮሐ14÷26 "አብ በስሜ የሚለከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ" በማለት አጽናኝ የተባለው መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ በስሙ ጠርቶት ተናግሯል። መንፈስ ቅዱስ የሚለውን በግሪኩ
Πνεῦμα Ἅγιον(Pneuma Hagion) ሲለው Holy Spirit/ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው። ይህ ደግሞ በሌሎች ቦታዎች መንፈስ ቅዱስ በሚል ከተቀመጠው ጋር ተመሣሣይ ነው። ማቴ28÷19 አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ በትክክል በስሙ ጠርቶት ሳለ ለመሐመድ የተነገረ ነው የሚለው ፈጽሞ ሊያስኬድ አይችልም።
2. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃሉን የነገራቸው ለደቀ መዛሙርቱ ነው። ስለዚህ "አጽናኝ" ይሰጣቹሃል ተብሎ የተገባላቸው ቃል ኪዳን ለደቀ መዛሙርቱ ሊፈጸምላቸው ግድ ነው። መሐመድ ደግሞ የተነሳው ደቀ መዛሙርቱ ከዚህ አለም ከተለዩ ከ 600 አመት በኃላ ነው። መሐመድ በምንም መልኩ ለደቀ መዛሙርቱ የተነገረውን ቃል ኪዳን ሊፈጽም አይችልም። መንፈስ ቅዱስ ግን በበአለ ሀምሳ በሐዋርያት ላይ በመውረዱ የተገባላቸው ቃል ተፈጽሞላቸዋል። ሐዋ1÷1-4 አጽናኙ የተባለው መሐመድ ነው የሚለው የማያስኬድ ሙግት ነው።
3. በዮሐ14÷17 ላይ ስለ አጽናኙ ማንነት ሲቀጽል "አለም የማያየውና የማያቀው የእውነት መንፈስ ነው" ይላል። በዚህ ጥቅስ ላይ ከመሐመድ ማንነት ጋር የማይሄድ ሀሳብ በግልጽ ተቀምጧል። ይህም "አለም የማያየውና የማያቀው የእውነት መንፈስ ነው" የሚለው ነው። ቁርአንም ሆነ ሙስሊሞች መሐመድ ሰው እንደነበረ፣ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች ሁሉ እንዳዩት፣ ስጋና አጥንት የሌለው መንፈስ እንዳልሆነ የማይክዱት ሐቅ ነው። በትምህርተ ሥላሴ ግን መንፈስ ቅዱስ የማይታይና የማይዳሰስ ረቂቅ አካል ያለው ስለሆነ ከክርስትናው አስተምሮ ጋር የሚስማማ ነው። ታዲያ "አጽናኙ" መንፈስ ነው የሚለውን እንዴት ተቀብለው ነው ለመሐመድ ነው የተነገረው የሚሉት? ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ማለት ይሄ ነው።
4. በዮሐ14÷17 "ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።" በሚል ስለ አጽናኙ የተነገረ ቃል አለ። ጌታችን ለደቀመዛሙርቱ አጽናኙ በውስጣቸው እንደሚሆን ይናገራል። ከላይ እንደ ተገለጸውና ሙስሊሞችም እንደሚያምኑት መሐመድ የሚታይና የሚዳሰስ አካል የነበረው ሰው ነበረ። ይህ ከሆነ ልክ እንደ መንፈስ በውስጣቸው እንዴት ሊኖር ይችላል? ሙስሊሞትች ኸረ ከቅዠታቹ ንቁ!
5. በዮሐ15÷26 ላይ አጽናኙ "ከአብ የሚወጣ" እንደሆነ ይናገራል። ሙስሊሞች አጽናኙ መሐመድ ነው ካሉ መሐመድ ከአብ የወጣ ነው እያሉ መሆኑን አላስተዋሉትም። በክርስትናው አስተምሮ መንፈስ ቅዱስ ከአብ የወጣ(የሰረጸ) ነው፣ ስለዚህ ከአስተምሮው ጋር ይስማማል። በተጨማሪም "ከአብ ዘንድ የምልክላቹ" ብሎ አጽኑኙ ከአብ ዘንድ የሚኖር እንደሆነ ይናገራል። መሐመድ ከአብ ዘንድ የኖረ ነውን? በፍጹም አይደለም። ስለዚህ መሐመድ ነው የሚለው ሙግት ፈጽሞ አያስኬድም።
6. ዮሐ14÷15 ላይ አጽናኙ "ለዘለላም ከእናንተ ጋር የሚኖር" ተብሎ ተነግሮለታል። መሐመድ እንኳን ለዘላለም ሊኖር ይቅርና በ 570 ዓ.ም ተወልዶ በ 630 ዓ.ም የሞተ ሰው ነው። እንኳን ለዘላለም ሊኖር ለአለም የተላከ ነብይ ነው ተብሎ በ 62 አመቱ ከአረብ ምድር ማለፍ ሳይችል ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።
7. በዮሐ16÷7 ላይ "እኔ ብሔድ ግን እሱን እልክላቹሃለው" በማለት መንፈስ ቅዱስን የሚልከው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይናገራል። በሙስሊሞች አስተምህሮ ደግሞ ነቢዩ መሐመድን የላከው ኢሳ ነው የሚለው የማይታሰብ ነው። ሙስሊሞች ስለ መሐመድ ማስረጃ ሲፈልጉ ኢየሱስ ነብያትን የሚልክ ነው ብለው እየመሰከሩ እንደሆነ አልገባቸውም።
8. ክርስቶስ የነገራቸውን ትምህርት የሚያሳስብ
በአብና በክርስቶስ የተላከው መንፈስ ቅዱስ በወረደባቸው ሰዎች ውስጥ ሆኖ ጌታ ኢየሱስ የነገራቸውን ነገር ማሳሰብ ዋንኛው ሥራው ነው፡፡ ለዚህም "አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል" የሚለው ቃል ምስክር ነው (ዮሐ፡14÷26)፡፡ በሌላም ሥፍራ ይኸው መንፈስ ስለ ክርስቶስ እንደሚመሰክር ተፅፏል፡፡ ስለሆነም መንፈስ ቅዱስ የተላከላቸው የጌታ ደቀመዛሙርትና ክርስቲያኖች ሁሉ ይህንኑ የጌታ ነገር ማሳሰብ ዋንኛ ዓላማቸው ነበር፡፡ "ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል" (ዮሐ፡20÷31) በማለት የእግዚአብሔር ልጅነቱን መሰከሩ፡፡ "መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን" (1ቆሮ፡1÷22) እያሉም የስብከታቸው ማዕከል ቤዛነቱ መሆኑን አስታወቁ፡፡ ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ማወቅ የሰማይ አባቱ የሚገልጠው ዕውቀት ከመሆንም ባሻገር የእምነታችን መሰረት እንደሆነ አሳስቧልና (ማቴ፡16÷15-19)፡፡ ያለ እርሱ ቤዛነትም የዘላለም ሕይወት እንደማይገኝ "ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል" ብሏልና (ዮሐ፡3÷14-15)፡፡
መሐመድ ግን መንፈስ ቅዱስ ወይም ሌላ አጽናኝ ተብሎ የተገለጠው እርሱ ባለመሆኑ እነዚህን የጌታ ማሳሰቢያዎች ሽምጥጥ አድርጎ ክዷል፡፡ እንዲያውም የእስልምና አስተምህሮ የተገነባው እነዚህን የክርስትና እምነትና አስተምህሮዎች በማስተባበል ላይ ነው፡፡
9. ቃሉ የሚናገረው አጽናኙ የሚወጣው ከአብ ነው። አብ የሚለው ስም በግሪኩም፣ በእንግሊዘኛውም፣ በግእዙም አባት የሚለውን የሚገልጽ ነው። አጽናኙ ከአባት ዘንድ የሚላክ መሆኑን ደግሞ ቃሉ ይነግረናል። አባት የሚለውን ደግሞ ሙስሊሞች አይቀበሉም። ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ ልጅ ነው ሲባሉ ግራ መጋባታቸው የሚታይ ሐቅ ነው። ይህ በሆነበት ሁኔታ መሐመድ ከአባት ዘንድ ነው የተላከው ሲሉ ከአላህ ማንነት ጋር እየተጋጩ ነው።
=>>>በሚቀጥለው ጽሁፍ ሙስሊሞች አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ለማለት የሚያቀርቧቸውን ሙግቶች እንመለከታቸዋለን።
ክፍል አራት [ አፅናኙ መንፈስ ቅዱስ ነው። ]
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ለማንኛውም አስተያየት፦
[ ዐቃቢያነ እምነት ዘኦርቶዶክስ ]
ለቴሌግራም ቻናላችን፦
[ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ]
Comments
Post a Comment