ክፍ. ፩ የኢየሰስ አምላክነት ከአድስ ኪዳን(ዮሐ. ፩:፩)

 

     አንድ አምላክ በሚሆን በአብ : በወልድ : በመንፈስ ቅዱስ ስም!

.
   ሰላም ለእናንተ ተወዳጅ የቻናናችን ቤተሰቦች እንድምን አላችሁ? ባለፉት ክፍላት የኢሱስን አምላክነት የሚያስረዱ የብሉይ ኪዳን ማስረጃዎችን ማየታችን ይታወሳል። ከዛሬ ጀምረን ደግሞ ከአድስ ኪዳን የኢየሱስን አምላክነት የሚያስረዱ ጥቅሶችን እንመለከታለን።

   ይህንን ተከታታይ ክፍል ለማቅረብ ስንሞክር መፅሀፍ ቅዱስን ያጠና ሰዎ "እኒህ ሰዎች ያማቸዋል እንዴ?" ብሎ ሊገረም ይችላል ምክንያቱም በአድስ ኪዳን የኢየሱስ አምላክነት በሚገባ የተገለፀበት በመሆኑ "ምኑን አንስተው ምኑን ይጥሉታል" ብሎ መገረሙ ስለማይቀር ነው። እኛ ግን የኢየሱስን አምላክነት ለመረዳት ሙሉ መፅሀፍ ቅዱሱን እንድታነቡ እየመከርን በዚህ በምናቀርባቸው ፅሁፎች ግን አምላክነቱን የሚያሳዩ ጥቅሶችና የተለያዩ ተቃዋሚ ቤተእምነቶች በዛ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ እየመለስን የምናቀርብ ይሆናል።

    የምንጀምረውም ከአራቱ ወንጌላት መካከል የኢየሱስን አምላክነት በማወጅ ከሚጀምረው ከዮሐንስ ወንጌል በመጀመር ነው። ሶስቱን ተመሳሳይነት ያላቸውን (Synoptic Gospel) የሚለባሉትን ለይደር በሌላ ርዕስ ለማሰስ እናስቀምጣቸው እና የዮሐንስ ወንጌልን እንመለከታለን።ለዛሬ የመረጥነውም ጥቅስ በነገረ መለኮት ሊቃውንት ዘንድ እንደመግቢያ ከሚታየውን ከዮሀንስ ወንጌል 1:1-18 ውስጥ የሚገኘውን ቁጥር 1  ነው።

   ዮሐንስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።

   ሶስቱ ወንጌላት ( ቅዱስ ማቴዎስ ፣ ቅዱስ ማርቆስ እና ቅዱስ ሉቃስ) የፅሁፋቸውን መጀመሪያ ከተዋሕዶ በኋላ በማተኮር ሲያቀርቡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን የኢየሰስን ቅድመ ተዋሕዶ በማቅረብ ይጀምራል ይህም የኢየሱስ አምላክነት በማወጅ ነው።

   ወንጌላዊው በአንድት ጥቅስ የኢየሱስን አምላክነት በሚገባ የገለፀ ሲሆግ ስለ ቃል(ኢየሱስ) የተናገራቸውን ሀሳቦች ጠቅለል አድርገን  በነጥብ ስናስቀምጣቸው፦

  #ነጥብ 1፦ ስለ ቅድምናው (preexistence)

  #ነጥብ 2፦ የራሱ የሆነ ማንነት(ከአብ የተለየ) ያለው መሆኑን ይነግረናል በመቀጠልም

  #ነጥብ 3፦ ስለ እግዚአብሄርነቱ ይገልፃል

  እኒህን ሶስት ሀሳቦች ሰፋ ባለ ትንታኔ የሚቀርቡ ቢሆንም አጠር አድርገን በቂ በሚሆን ማስረጃ ለማቅረብ እንሞክራለን።

✅ #ነጥብ 1፦ #ስለ_ቅድምናው፦

     “በመጀመሪያ ቃል ነበረ” — ዮሐንስ 1፥1

   ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሀንስ ቅድሚያ ሰጥቶ ያቀረበው ነገር ቢኖር የቃልን ቅድምና ነው። ይህ የወንጌል መግቢያ የስነ - መለኮት ሊቃውንት ከዘፍጥረት መግቢያ ጋር ያነፃፅሩታል። እኒህን ሁለት መፅሀፍት የሚያመሳስላቸው ሁለቱም ሲጀምሩ " በመጀመሪያ " ብለው በመጀመራቸው ብቻ አይደለም ሁለቱም ስለብርሃን እና ጨለማ እያነፃፀሩ ያቀርባሉ። ሙሴ ስለ ፍጥረት መጀመሪያ ፣ በምድር የነበረውን ጨለማ ስላጠፋው ብርሃን ሲያቀርብ ፤ ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ከፍጥረት በፊት ስለነበረው ፣ፍጥረትም በእርሱ ስለሆኑት ስለ ዘላለማዊው አምላክ ፣ ስለ አማናዊው ብርሃን ይነግረናል። አንዳንድ ወገኖች "በመጀመሪያ" የሚለውን ይይዙና "ኢየሱስ መጀመሪያ አለው ፣ መጀመሪያ ካለው ደግሞ ፍጡር ነው።" በማለት ሙግት ያቀርባሉ። ባይረዱት እንጂ ቅዱስ ዮሀንስ በፅሁፉ የተጠቀማቸው የግሪክ ቃላት የኢየሱስን ቅድምና የሚያስረዱ ናቸው።

  "በመጀመሪያ ቃል ነበረ" የሚለው በግሪኩ "Ἐν ἀρχῇ ἦν ὁ Λόγος" የሚለው ነው። በዚህ ሀረግ ውስጥ "ነበረ" በማለት የተተረጎመው የግሪክ ቃል ኤን(ἦν,En)የሚለውን ሲሆን "መጀመሪያው የማይታወቅ መጀመሪያ " የሚለውንም ሀሳብ የሚያሳይ ነው።  ይህ ማለት በእኛ አእምሮ መርምረን ልንደርስበት የማንችለውን ፣ ከ time & space ውጭ ያለውን ጊዜ የሚያመለክት ነው። ከጅምሩም ዘመናት የእርሱ ስራ ናቸውና እርሱ በዘመን (ጊዜ) ሊለካ አይችልም። ይኼ ሆነ ማለት "መቼ?" በሚለው የጊዜ ስፍር አይሰፈርም ማለት ነው።  ቅዱስ ዮሐንስ ኢየሱስን በዚህ ቃል መግለፁ በዘመናችን ኢየሱስ ከዘመናት በኋላ የተገኘ ነው የሚሉ የተቃዋሚዎችን ሀሳብ የሚያፈርስ ነው።

   ከዚህ በተጨማሪ "በመጀመሪያ" ተብሎ በዛው ላይ የተተረጎመው ቃል  አርኬ(ἀρχῇ,arche) የሚል ነው። ይህንን ቃል ወንጌላዊው በራዕይ መፅሀፉ ላይ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊነት ለመግለጽ ተጠቅሞበታል፦

“አለኝም፦ ተፈጽሞአል። አልፋና ዖሜጋ፥ መጀመሪያው(ἀρχῇ) ና መጨረሻው እኔ ነኝ። ለተጠማ ከሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ።” — ራእይ 21፥6

  በዚህ ጥቅስ "አርኬ" የሚለው ቃል የእግዚአብሔርን ዘላለማዊነት እንዳሳየ ሁሉ በዮሀ1:1 ላይም የሚያመለክተው ይህንኑ ነው።

✅  ነጥብ 2፦ የራሱ የሆነ ማንነት ያለው ስለመሆኑ

    ወንጌላዊው ዮሀንስ ስለ ቃል ቅድምና ከተናገረ በኋላ የቃልን እራሱን የቻለ እኔ ባይነት ይነግረናል።

   “ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥” — ዮሐንስ 1፥1

    አንዳንድ ተቃዋሚዎች  "ወንጌላዊው ቃል እያለ የጠቀሰው ከልብ የሚወጣውን የንግግር ቃል ነው ፣ ይኼ ቃል ደግሞ አካላዊ አይደለም " ይላሉ።

    ይኽ ሙግታቸው ስህተት መሆኑን በቀላል ማሳያወች እንመልከት ፦

1ኛ፦ እነርሱ እንደሚሉት "ቃል" በመባል የተገለፀው የአብ ንግግርት ወይንም ዝርው ንግግር ቢሆን ኖሮ ወንጌላዊው በርካታ ትርጉሞች ያሉትን "ሎጎስ" የሚለውን ቃል ከመጠቀም ይልቅ ቀጥተኛ የሆነውን ፣ እርሱም ወንጌሉን ሲፅፍ ከአንደበት የሚወጣን ቃል የመግለፅ የተጠቀመበትን  ሬማ (ῥήματι : Rhema) የሚለውን ቃል በተጠቀመ ነበር።

    ለምሳሌ ፦
    “መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን(Rhema) እንዴት ታምናላችሁ?”— ዮሐንስ 5፥47

   “ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን(Rhema) ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም።”— ዮሐንስ 12፥47

2ኛ፦ "ቃል" እየተባለ የተገለፀው አካላዊ ነው ብለን እንድንደመድም የሚያደርገን አንዱ እና ዋናው ነገር ይህ "ቃል" ዘንድ በሚል መስተዋድድ መገለፁ ነው።

   በአማርኛው መፅሀፍ ቅዱስ "ዘንድ" እየተባሉ የተተረጎሙ በርካታ የግሪክ ቃላት ሲኖሩ በዚህ ጥቅስ ግን "ዘንድ" በሚል የተተረጎመው የግሪክ ቃል ፕሮስ(πρὸς:pros) ሲሆን የዚህ ቃል አገልግሎት በመፅሀፍ ቅዱስ አካላዊ ግንኙነትን የሚያመለክት ነው፦

    With God (pros ton theon). Though existing eternally with God the Logos was in perfect fellowship with God. Pros with the accusative presents a plane of equality and intimacy, face to face with each other. (Word Pictures In The  New Testament. A.T Robertson Volume V :pp 19)

   ለምሳሌ እንመልከት፦

  “ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ(pros) ጠበቃ አለን፤👉 እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።”— 1ኛ ዮሐንስ 2፥1
 
   “ጢሞቴዎስም የመጣ እንደ ሆነ በእናንተ ዘንድ(pros) ያለ ፍርሃት እንዲኖር ተጠንቀቁ፤ እንደ እኔ ደግሞ የጌታን ሥራ ይሠራልና፤ እንግዲህ ማንም አይናቀው።” — 1ኛ ቆሮንቶስ 16፥10
  
በርካታ ምሳሌዎች ያሉ ቢሆንም ላለማስረዘም እኒህ በቂ ይመስሉኛል። በእነዚህ በሁለቱም ጥቅሶች እንደምንመለከተው "pros" የሚለው ቃል አካላዊ ግንኙነትን የሚያመለክት ነው። በዚሁ ሂሳብ " ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ("pros) ነበር" የሚለው ቃል እየተባለ የሚገለፅ አካል መኖሩን ፡ ያም አካል ከአብ ዘንድ በአካላዊ ግንኙነት የነበረ መሆኑን ያመለክተናል።


3ኛ፦ በቁጥር ሶስት ላይ ይህ ቃል " እርሱ" በሚል ሶስተኛ መደብ አመልካች በሆነ ቃል ተገልጿል። ተቃዋሚዎች እንደሚሉት ቃል የተባለው የአብ የንግርት ቃል ቢሆን ኖሮ ማንነት ያለውን አካል ለመግለፅ የምንጠቀምበትን የግሪክ ቃል አውቶስ(αὐτός : autos) ባልተገለፀ ፣ እርሱ ባልተባለ ነበር።

4ኛ፦ ቃል አካላዊ መሆኑን የምንረዳበት ተጨማሪ መረጃ ደግሞ "ቃልም እግዚአብሔር ነበረ" የሚለው ጥቅስ ነው። በዚህ ጥቅስ ወንጌላዊው "ቃል" እያለ ይጠራው የነበረው እራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ያበስረናል። "ቃል" የተባለው ዝርው ፡ አካላዊ ያልሆነ ቢሆን ኖሮ እንዴት "እግዚአብሔር ነበረ" ሊባል ይችላል?

   ከአራቱ ማስረጃዎች በተጨማሪም ወንጌላዊው ሲፅፍ "ቃል(The word) " እያለ እንጂ "ቃሉም (His word)" እያለ እንዳልፃፈ ልብ ልንል ይገባል።

    "ቃል" በማለት ወንጌላዊው የገለፀው አካላዊ መሆኑን ለመረዳት ህሊና ላለው ሰው ይሄ ከበቂ በላይ ነው።

✅ ነጥብ_3፦ ስለ እግዚአብሔርነቱ

  "ቃልም እግዚአብሔር ነበረ : The word was God"

    ቅዱስ ዮሐንስ ስለዚህ ኢየሱስ ማንነት በመጀመሪያ ዘላለማዊ መሆኑን ፣ ቀጥሎ ደግሞ ከአብ የተለየ የራሱ የሆነ ማንነት ያለው መሆኑን ካስረዳን በኋላ ይኽ አካል "እግዚአብሔር ነበረ" በማለት የኢየሱስን መለኮታዊነት ያስረዳናል።

   እንደ ይሖዋ ምስክሮች ያሉ ቤተ እምነቶች ይህንን ጥቅስ " The word was God" ሳይሆን መባል ያለበት " The word was a god" ነው በማለት ይሞግታሉ። ለዚህ ሙግታቸው እንደምክንያት የሚያቀርቡት ደግሞ በግሪኩ article the (ὁ) የለችም በማለት ነው። ይሄ ሙግታቸው ግን እንኳን ሙሉ መፅሀፍ ቅዱሱን ያማከተ መሆኑ ይቅርና ከዛው ከዮሀንስ ወንጌል ምዕ.1 ለራሱ አያልፍም።

  የይሖዋ ምስክሮች ነን የሚሉት ቤተ እምነቶች ይህንን ሙግታቸውን በፍትሐዊ መንገድ ካስቀጠሉት በዛው ምዕራፍ ቁጥር 4 ላይ "በእርሱም ህይወት ነበረች ; in him was life" የሚለውን "a life" እያሉ መተርጎም ይጠበቅባቸዋል ምክንያቱም በዚህም ጥቅስ article the የለም።

    ከዚህ የባሰው ግን definite article "the(ὁ : ho) የለችምና "a god" ነው መባል ያለበት ካሉ በመፅሀፍ በርካታ ቦታዎች ላይ ቴዎስ(θεός ፡ theós) የሚለው ስም ያለ አርቲክል the መጥቷል። ለምሳሌ 2 ቆሮ 5 :19 ላይ θεός ከሚለው ካል በፊት ὁ የለችም በእነርሱ ሂሳብ ያም ክፍል God ሳይሆን መባል የነበረበት a god ነው ይኼ ደግሞ የለየለት እብደት ነው ምክንያቱም ጥቅሱ ስለ እግዚአብሔር አብ የሚናገር ነውና።

   ቅዱስ ዮሀንስ ለምን article "the" ን አላስገባም የሚለውን ስንመለከት ፦ ዮሀንስ ወንጌሉን " theos en ho logos" ከማለት ይልቅ " ho theos en ho logos" ቢል ኖሮ በቀጥታ የሰባልዮሳዊያንን ( Sabellianism) አስተምህሮ በደገፈ ነበር ምክንያቱም "theos" እና "logos" ቦታ መቀያየር ይችሉ ነበር ማለትም እንደዛ አለ ማለት "  ho logos en ho theos " ማለት ይቻል ነበር ይኼ ማለት ደግሞ  "እግዚአብሔርም ቃል ነበረ ; the God was the Word"  የሚል ይሆናል። እንዲህ አለ ማለት ደግሞ "ቃል" የተባለው አካልና "እግዚአብሔር አብ" አንድ አካል ናቸው ወደሚል ኑፋቄ ይመራል ይኼ ደግሞ ከላይ ከአብ የተለየ አካል እንዳለው ከተናገረ በኋለ መልሶ አንድ አካል ማድረግ እራስን ማጋጨት ነው። ስለዚህም ቅዱስ ዮሐንስ የሰባልዮስን አስተምህሮ ሲያፈርስ article the ን አወጣ።

   እኒህ በአንድ ጥቅስ ውስጥ የሚገኙ ሶስት ሀረጎቸ ቁጥር ሶስትን ሳንጠቅስ ለራሱ የኢየሱስን አምላክነት በበቂ ሁኔታ ያቀርቡልናል።

       ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ክፍል ሁለት [ የዮሐንስ ወ. 8:58 ]
ክፍል ሶስት [ የዮሐንስ ወ. 10:30 ]
ክፍል አራት [ የዮሐንስ ወ. 20:28 ]

ለማንኛውም አስተያየት ➞
[ ዐቃቢያነ እምነት ዘኦርቶዶክስ ]

ለቴሌግራም ቻናላችን፦
[ ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ]
     

Comments

Popular posts from this blog

ዕቅበተ እምነት

ወላዲተ አምላክ

መልስ ለወሒድ ዑመር