ምስጢረ ስጋዌ መግቢያ
ምስጢረ ስጋዌ መግቢያ
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ ፡ በወልድ ፡ በመንፈስ ቅዱስ!
የቤተክርስቲያናችን ምሰሶ ከሆኑት ከአምስቱ አዕማደ ምስጢራት መካከል በሁለተኛነት የምናገኘው ፤ የአምላክን ሰው የመሆን ነገር የምንነጋገርበት #ሚስጥረ_ሥጋዌ ይባላል።
በባለፈው ስለ ምስጢረ ሥላሴ በተነጋገርነበት ፕሮግራማችን ላይ ምስጢረ ሥላሴ ለምን ምስጢር ተባለ? የሚለውን መመልከታችን ይታወሳል የሥላሴ አስተመህሮ ምስጢር መባሉ በእኛ ውስን አዕምሮ ተመራምረን ልንደርስበት የማንችል መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ ሁሉ ምስጢረ ሥጋዌም ምስጢር መባሉ የአምላክን ሰው የመሆን ምስጢር በፍጡር አዕምሯችን መርምረን ልንደርስበት የማንችል መሆኑን ያመለክተናል።
በዚህ አምዳችን ላይ በኢየሱስ አምላክነት ዙሪያ መፅሀፍ ምን እንደሚያስተምር ፣ መናፍቃንም በአምላክነቱ ዙሪያ የሚያነሷቸውን ክሶች የምንመለከት ይሆናል።
የአምላክን ሰው የመሆን ነገር ስንነጋገር አዕምሯችን ውስጥ ከሚመጡት ጥያቄዎች መካከል " ሰው መሆን ለምን አስፈለገው?" የሚለው የመጀመሪያው ነው። ይህ እራሱን የቻለ ሰፊ በነገረ ድኽነት ትምህርት የምናገኘው ርዕስ ቢሆንም ለያዝነው ርዕስ መንደርደሪያ ይሆነን ዘንድ በአጭሩ እንመልከት፦
✟ ኢየሱስ ለምን ሰው ሆነ?
በጠራ ክብር የተፈጠረው አዳም የጠራው ክብሩን ትእዛዝ ተላልፎ ባጎደፈው ጊዜ ያንን የጎደፈ ክብሩን የሚያነፃለት ያስፈልገው ነበር። ያንን ማድረግ ደግሞ ለነብያቱም ሆነ ለኦሪት መስዋዕት አልተቻላቸውም። ነብያቱ ከአዳም የመጣው ጥንተ አብሶ አለባቸውና እንኳን ከአምላክ ፊት ቆመው ይህንን መርገም ሊያጠፉ ይቅርና ለራሳቸውም ድኽነትን ይጠባበቁ የነበሩ ናቸው። የኦሪት መስዋዕትም ሰዎች በፈቃደ ስጋቸው ተነሳስተው የሚሰሩትን ኃጢአት ከማንፃት ባለፈ በአዳም ምክንያት ወደ ዓለም ከገባውን መርገም ሊያስጥል የሚችል አልነበረም። ስለዚህ መፅሀፍ እንደሚለን ንፁሃ ባህሪይ የሆነው ጌታ እራሱ የጠፋውን በግ ይፈልገው ፣ ወደቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ ከሰማይ ወረደ ፡ ከድንግል ተወለደ!።
ማቴዎስ 18
¹¹ የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቶአልና።¹² ምን ይመስላችኋል? ለአንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩት ከእነርሱም አንዱ ቢባዝን፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ትቶ ሄዶም የባዘነውን አይፈልግምን?¹³ ቢያገኘውም፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ካልባዘኑቱ ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሱ ደስ ይለዋል።
እዚህ ላይ ሙስሊም ወንድሞች ፦
" እግዚአብሔር እውነት ሁሉን ቻይና የፍቅር አምላክ ከሆነ አዳምን በበደለ ጊዜ ለምን ይቅር አላለውም?" በማለት ይጠይቃሉ። መጠራጠር ባይኖረው መልካም ጥያቄ ነበር፦
እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ(ኤልሻዳይ) እና የፍቅር አምላክ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም ይኽንን መፅሀፍ አስረግጦ ይነግረናል። "እና ለምን ይቅር አላለውም?" የሚለውን ስንመለከት ፦
እግዚአብሔር ለአዳም የመጀመሪያይቱን "አትብላ" የምትለውን ትእዛዝ በሰጠው ጊዜ ከትእዛዙ በተጓዳኝ ፍርዱንም አስቀምጦለት ነበር። ያችን ትእዛዝ በተላለፈ ጊዜ ያ ፍርድ እንደሚፈረድበት ተነግሮት ነበር።
ዘፍጥረት 2
¹⁶ እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤¹⁷ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤👉 ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።
እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ እንደሆነ ሁሉ የፍትህ አምላክ መሆኑንም መፅሀፍ ይናገራል፦
“👉 በውኑ እግዚአብሔር ፍርድን #ያጣምማልን? ሁሉንም የሚችል አምላክ ጽድቅን ያጣምማልን?”— ኢዮብ 8፥3
“አቤቱ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፥ ፍርድህም ቅን ነው።”— መዝሙር 119፥137
እግዚአብሔር የፍትህ አምላክ እንደመሆኑ በተናገው መሰረት ፈፀመው። ፍርድን የማያጣምም ፡ ቅን ፈራጅ የሆነን አምላክ ለምን አልማራቸውም ብሎ መክሰስ እግዚአብሔር ቃሉን ማጠፍ ነበረበት እንደማለት ነው ይኼ ደግሞ የማይሆን ነው። አዳም መርጦ እጁን ከእሳት ከቷልና የሞት ሞትን ሞተ።
በአዳም ሞት ዙሪያ ሙስሊሞች " መፅሀፉ የሚለው በበላህ ጊዜ ሞትን ትሞታለህ ነው ግን አዳም በበላበት ጊዜ አልሞተም ስለዚህ መፅሀፍ ተሳስቷል" የሚል በሚዛን ቢለካ ገለባ የሆነ ክስን ይከሳሉ።
እዚህ ላይ ሙስሊም ወንድሞች ያልተረዱት ነገር ቢኖር የ " ሞት" እሳቤ በመፅሀፍ ቅዱስ ምን አይነት እንደሆነ ነው።
ሞት በመዝገበ ቃላት ትርጓሜው ነፍስ ከስጋ መለየት እንደሆነ ቅቡል ነው። በመፅሀፍ ቅዱስ ግን ከዚህ ትርጉም ሰፋ ያለ ሀሳብን ይይዛል። በመፅሀፍ ቅዱስ ሞት በሁለት አይነት ሀሳቦች ይከፈላል።
➊፦ የመጀመሪያው የመዝገበ ቃላት አይነት ሀሳብ ሲሆን ይህንን ሞት " ሞተ ስጋ" ወይንም " የስጋ ሞት" እንለዋለን። ይኼ ሞት ነፍስ ከስጋ የምትለይበት አይነት ነው።
ለምሳሌ ይኽን በኢየሱስ ሞት መመልከት እንችላለን። ኢየሱስ ሞተ ስጋን በሞተ ጊዜ ነፍሱ ወደ ሲኦል ፣ ስጋው ደግሞ ወደ መቃብር ወርዶ ነበር።
➋፦ ሁለተኛው የሞት አይነት ደግሞ " የመንፈስ ሞት" የምንለው ነው። ይኼ ሞት እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ስንለይ የምንሞተው ሞት ነው። የእኒህን ሁለት ሀሳቦች ልዩነት ለመረዳት አንዲት ሁለቱንም ሀሳቦች የያዘች ጥቅስ እንጥቀስ፦
ማቴዎስ 8
²¹ ከደቀ መዛሙርቱም ሌላው፦ ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ እንድሄድ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ አለው።²² ኢየሱስም፦ ተከተለኝ፥ #ሙታናቸውንም_እንዲቀብሩ_ሙታንን_ተዋቸው አለው።
👆 በዚህ በኢየሱስ ንግግር የሁለቱን ሀሳቦች ልዩነት በግልፅ መመልከት ይቻላል። በመጀመሪያ "ሙታናቸውን" በሚለው ቃል ውስጥ የምናገኘው ነፍሱ ከስጋው የተለየችው የደቀመዛሙርቱ አባት ሲሆን ፤ በሁለተኛነት " ሙታን" የተባሉት ግን በአካለ ግዝፈት ያሉ ፣ ነፍሳቸው ከስጋቸው ያልተለየችውን ቀባሪዎች የሚያመለክት ነው። እኒህ ሰዎች ስለምን ሙታን ተባሉ? ካልን ከእግዚአብሔር ተለይተዋልና ሙታን ተባሉ።
ለሁለተኛው ሀሳብ አንዲት ማስረጃን እንጨምር፦
“በበደላችሁና በኃጢአታችሁ👉 #ሙታን_ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው።”— ኤፌሶን 2፥1-2
ብርሃነ አለም ቅዱስ ጳውሎስ የኤፌሶንን ሰዎች "ሙታን ነበራችሁ" ይላቸዋል የዚህም ምክንያቱ " በደላቸውና ኃጢአታቸው " ነበ።ከዚህ እንደምንረዳው በኃጢአታቸው ምክንያት ከእግዚአብሔር ስለተለዩ ሙታን ተባሉ ማለት ነው።
ወደተነሳንበት ነጥብ ስንመለስ ባየነው መሰረት አዳም ቅጠሏን በበላ ጊዜ የሞተው የመንፈስ ሞትን እንጂ የስጋ ሞትን አይደለም ማለት ነው።። በበላ ጊዜ የመንፈስ ሞትን በመሞቱ ጸጋው ሲገፈፍ እናያለን፦
“የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፥ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ፤ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።”— ዘፍጥረት 3፥7
በዚህ መልኩ ጥያቄያቸው ምላሽን ያገኛል ማለት ነው።
በእውነቱ ግን ይኼ የድህነት ስራ የእግዚአብሔርንፍቅር ከፍርዱ ጋር እኩል የተገለጠበት ግብር ነው ። እግዚአብሔር እንደ ቅን ፈራጅነቱ አዳምን በቃሉ መሰረት ሲቀጣው እንደ ፍቅርነቱ ደግሞ ሌሎቹን ለይኩን በማለት ሲፈጥር አዳምን ግን አክብሮ ያበጃጀው ፣ በአርያውና በአምሳሉ የፈጠረው ነውና ይጠፋ ዘንድ ስላልወደደ የድህነቱን ተስፋ በበደለ ጊዜ ነበር የሰጠው፦
“በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።”— ዘፍጥረት 3፥15
የዲያቢሎስ ዘር በተባሉ በኢየሱስ ዘመን በነበሩ የሰይጣን የግብር ልጅ በነበሩ እና በሴቷ ዘር መካከል ጠላትን እንደሚያደርግ እርሱም እራሱን እንደሚቀጠቅጠው ለአዳም የተስፋ ቃል የሰጥቶታል። ይኼ የተስፋ ቃል እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ መሆኑን የሚያሳየን ነው። ይኽም የተስፋ ቃል ሲፈፀም ጌታ ኢየሱስ ከሴቷ ዘር ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ፣ በዕፀ መስቀሉ ተሰቅሎ ድል ነስቶታል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
29/09/2012 ተጻፈ
የtelegram ቻናላችንን ይቀላቀሉ
Comments
Post a Comment